መግቢያ
- ይህ የሩብ ዓመት ሪፖርት በኢትዮጵያ የበጀት ዓመት አቆጣጠር መሠረት ከሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. እስከ መስከረም ወር 2017 ዓ.ም. መጀመሪያ ያለውን ጊዜ የሚመለከት ቢሆንም የተወሰኑት ሁኔታዎች ቀደም ባሉት ወራት የተከሰቱና የቀጣይነት ባሕርይ ያላቸው ናቸው። በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፣ ሥጋቶች እና አሳሳቢ ሁኔታዎች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ይህ የሩብ ዓመት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት በተለይ በግጭት ዐውድ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ በዋነኝነት ከፍተኛ በሆኑ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና አሳሳቢነታቸው በቀጠሉ ጉዳዮች ላይ ማሳያ በሆኑ ክስተቶች አጠቃላይ ምልከታ በመስጠት ለሰብአዊ መብቶች ሁኔታ መሻሻል ምክረ ሐሳቦችን የሚያቀርብ ነው።
- ሆኖም ሪፖርቱ በሩብ ዓመቱ ውስጥ በግጭት ዐውድ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች የደረሰውን ክስተትና ሁኔታ በሙሉ የሚሸፍን አይደለም። ይልቁንም በእነዚህ አካባቢዎች በነጻነት ተንቀሳቅሶ የተሟላ ክትትልና ምርመራ ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ፣ በተቻለ መጠን ክትትልና ምርመራ የተከናወነባቸውን ምሳሌያዊ ጉዳዮች ብቻ በመለየት ስለ ሰብአዊ መብቶች ሁኔታው አሳሳቢነት ለማሳየት የሚረዳ ሲሆን፣ በአፋጣኝ ሊወሰዱ ከሚገባቸው እርምጃዎች በተጨማሪ የተሟላ ምርመራ አስፈላጊነትንም የሚያመላክት ነው።
- ይህ ሪፖርት ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ በተለይ በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ከደረሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና አሳሳቢ ሆነው ከቀጠሉ ጉዳዮች መካከል ከሕግ ውጭ የሚፈጸም ግድያ፣ በግጭት ዐውድና አካባቢ የሚደርስ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ፣ የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ፣ በመዘዋወር መብትና በመጓጓዣ መንገዶች ላይ የሚፈጸም ሕገ-ወጥ ገደብ እና የሀገር ውስጥ መፈናቀል ይገኙበታል። ኢሰመኮ አስገድዶ መሰወረንና ሰዎች ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ አስሮ ማቆየትን በሚመለከት ራሱን የቻለ ዝርዝር መግለጫ ይፋ የሚያደርግ ይሆናል።
- ከሕግ ውጭ ግድያ፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ
- በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ በምሥራቅ ጉራጌ ዞን፣ ምሥራቅ መስቃን ወረዳ እና በማረቆ ልዩ ወረዳ አዋሳኝ ቀበሌዎች ላይ የሚነሱ ግጭቶችን ለማስቀረት የክልል፣ የዞን እና የወረዳ የአስተዳደርና ጸጥታ አካላት እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት የካቲት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕርቅ የማጽናት ሥነ-ሥርዓት ተከናውኖ፣ ለተጎጂዎችም ካሳ ተከፍሎ እንዲሁም በግጭቱ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችና የመንግሥት አመራሮችን ጭምር በቁጥጥር ሥር በማዋል ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸው የሚያበረታታ ቢሆንም፤ በሌላ በኩል በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ግለሰቦች/ቡድኖች በየጊዜው የሚያደርሱት ጥቃት በነዋሪዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት ማስከተሉን ቀጥሏል። ለምሳሌ ግንቦት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ገደማ በምሥራቅ ጉራጌ ዞን ምሥራቅ መስቃን ወረዳ ኢንሴኖ ከተማ ከገበያ በሚመለሱ ሰዎች ላይ የታጠቁ ሰዎች ባደረሱት ጥቃት ቢያንስ 3 ሰዎች የተገደሉና 1 ሰው ደግሞ የአካል ጉዳት የደረሰበት መሆኑን ኢሰመኮ ለመረዳት ችሏል። በተመሳሳይ መልኩ ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ በኢንሴኖ ከተማ የታጠቁ ሰዎች ባደረሱት ጥቃት 1 ሰው የተገደለ ሲሆን 3 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል። ነሐሴ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በማረቆ ልዩ ወረዳ ሆቤ ጃር ደምቦቃ በተባለ ቦታ 4 የአንድ ቤተሰብ አባላት የተገደሉ ሲሆን፣ ዲዳ ሀሊቦ በተባለ ቀበሌ 7 የሁለት ቤተሰብ አባላት ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ተገድለዋል።
- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በቡርጂ ዞን፣ ሶያማ ዙሪያ ወረዳ፣ በበኖ እና ቲሾ ቀበሌዎች በሚገናኙበት ወሰን የይዞታ መሬት ላይ ሚያዝያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. በተነሳ አለመግባባት መነሻነት በተቀሰቀሰ ግጭት 1 የቲሾ ቀበሌ ነዋሪ በተተኮሰበት ጥይት ሕይወቱ ያለፈ ሲሆን፤ ከሁለቱም ቀበሌዎች በግምት 5 ሰዎች በግጭቱ ምክንያት በተተኮሰባቸው ጥይት ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ይህ ሪፖርት በሚዘጋጅበት ወቅት በሶያማ ሆስፒታል ሕክምና እየተከታተሉ ይገኙ ነበር። በግጭቱ ምክንያት በግምት 5 መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
- ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ደቡብ ኦሞ ዞን፣ ማጎ ብሔራዊ ፓርክ ዙሪያ የሚገኙ የሙርሲ እና የቦዲ ማኅበረሰብ አባላት እንዲሁም በአሪ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ ማኅበረሰብ አባላት መካከል በተለያየ ጊዜ በእንስሳት ዝርፊያ፣ ኮንትሮባንድ ንግድና ጦር መሣሪያ ዝውውር ሳቢያ አለመግባባት ተፈጥሮ ወደ ግጭት በማምራቱ ብዛታቸው ለጊዜው በትክክል የማይታወቁ ሰዎች ተገድለዋል፤ የአካል ጉዳትም ደርሷል። በተጨማሪ በአካባቢው ለጉብኝት እና ለፊልም ሥራ ከተንቀሳቀሱ ሰዎች መካከል 1 የስፔን ዜግነት ያለው ሰው በተተኮሰበት ጥይት ሕይወቱ አልፏል።
- ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ “የጉማይዴ ልዩ ወረዳ አስመላሽ” ተብሎ የሚጠራው እና በጋርዱላ ዞን ሀይበና ቀበሌ በዋናነት የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ኃይል፣ ልዩ ወረዳ ይሰጠን በሚል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ኮንሶ ዞን፣ የሰገን ዙሪያ ወረዳ መቀመጫ የሆነችውን ሰገን ከተማን በመክበብ እና ተኩስ በመክፈት በፈጸመው ጥቃት የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት፣ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት እና ማዘጋጃ ቤት ሙሉ በሙሉ በእሳት ወድሟል። የሰገን ሆስፒታል እና ሌሎች የመንግሥት ተቋማት ላይ ዝርፊያና ከፊል ውድመት ደርሷል። በተጨማሪም ብዛታቸው ለጊዜው በትክክል ያልታወቀ የወረዳው የፖሊስ አባላት እና ነዋሪዎች በዚሁ ቡድን በተፈጸመባቸው ጥቃት መገደላቸውን ኢሰመኮ ተረድቷል። ይህን ተከትሎ የፌዴራል ፖሊስ እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ወደ ቦታው የተንቀሳቀሱ ሲሆን ይህ ሪፖርት በሚዘጋጅበት ወቅት አካባቢው በፌዴራል እና ክልል ጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች እና አስተዳደር አካላት ገልጸዋል።
- በጋምቤላ ክልል፣ የብሔረሰብ ማንነትን መሠረት አድርጎ በተለያየ ጊዜ የሚያገረሸው ግጭትና ጥቃት ቀጥሏል። መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት አካባቢ በጋምቤላ ክልል፣ ከጋምቤላ ከተማ ወደ ኑዌር ብሔረሰብ ዞን ሲጓዝ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ተርፋም ቀበሌ ሲደርስ በታጠቁ ቡድኖች በተፈጸመበት ጥቃት 3 ሰዎች ሲገደሉ በርካታ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል።
- መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በጋምቤላ ክልል፣ አኝዋ ብሔረሰብ ዞን፣ ጆር ወረዳ፣ ኡቱዎል 01 እና 02 ቀበሌዎች ውስጥ በታጠቁ ቡድኖች በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 47 ሰዎች ተገድለዋል፤ 16 ሰዎች ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል። በተጨማሪም 12 ሕፃናት በታጣቂዎች ከተወሰዱ በኋላ በመንግሥት አካላት በተደረገ ክትትል 10 ሕፃናት እንዲመለሱ ተደርጓል። ጥቃቱ በደረሰበት ዕለት ቢያንስ 700 የሣር መኖሪያ ቤቶች፣ 1 የጤና ኬላና 2 ትምህርት ቤቶች ተቃጥለዋል፤ እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቤት እንስሳትና የቀንድ ከብቶች በታጣቂዎች ተዘርፈው መወሰዳቸውን ነዋሪዎች አስረድተዋል።
- ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡00 ሰዓት አካባቢ በጋምቤላ ክልል ከኑዌር ብሔረሰብ ዞን ወደ ጋምቤላ ከተማ በመጓዝ ላይ በነበረ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ በታጠቁ ቡድኖች በተፈጸመ ጥቃት 7 ሰዎች ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ኢሰመኮ ከተጎጂዎች እና ከመንግሥት አካላት ባሰባሰባቸው መረጃዎች እና ማስረጃዎች ለማወቅ ችሏል።
- ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ከንጋቱ 11፡45 ሰዓት አካባቢ በጋምቤላ ክልል፣ ኢታንግ ልዩ ወረዳ ፑልኮት/መኮት ቀበሌ ውስጥ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጠቁ ሰዎች መካከል በተከሰተ ግጭት 8 ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል፤ 16 ሰዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል። በተመሳሳይ ጊዜ እና ቦታ ንብረትነታቸው የቀበሌው ነዋሪዎች በሆኑ ቢያንስ 10 የቀንድ ከብቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ተጎጂዎች አስረድተዋል።
- ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት አካባቢ በጋምቤላ ክልል፣ ጋምቤላ ወረዳ፣ ኡፓኛ ቀበሌ አኳቤሎ ተብሎ በሚጠራ ንኡስ ሰፈር ውስጥ በታጠቁ ቡድኖች በተፈጸመ ጥቃት አንድ የ12 ዓመት ታዳጊ ሲገደል፣ 2 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል።
- ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. በግምት ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት አካባቢ በጋምቤላ ክልል፣ ጋምቤላ ከተማ፣ 02 ቀበሌ ጓለት ማኅበር ተብሎ በሚጠራ የመዝናኛ ቤት ውስጥ በታጣቂዎች በተከፈተ ድንገተኛ ጥቃት በ9 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል።
- ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ በጋምቤላ ክልል፣ ጋምቤላ ከተማ፣ አዲስ ሰፈር ወይም ቴርጁኒ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር በታጣቂ ሰዎች 1 ሰው መገደሉ እና 2 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ታውቋል።
- ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 9፡00 ሰዓት አካባቢ በጋምቤላ ክልል፣ ጋምቤላ ከተማ፣ ኦሚኒንጋ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር 1 ሰው መገደሉን እና 4 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ለማወቅ ተችሏል።
- ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ገደማ በጋምቤላ ክልል፣ ጋምቤላ ወረዳ፣ ጀዊ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ አካባቢ በታጠቁ ቡድኖች በተፈጸመ ጥቃት 3 የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ተገድለው፣ 3 ሰዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል።
- በኦሮሚያ ክልል፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ አመያ ወረዳ ከኖ ቁሊጢ፣ አብየ ኮንሲ እና ቆታ ቀበሌዎች ልዩ ቦታው ቆታ (አርብ ገበያ) ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በማለት የሚጠራው ቡድን (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ታጣቂዎች መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በፈጸሙት ጥቃት የሰው ሕይወት ማለፉን ተከትሎ ሁኔታውን ለማረጋጋት የኦሮሚያ ጸረ-ሽምቅ ውጊያ ፖሊስ አባላት በቦታው ሲደርሱ በቦታው ከነበሩ የአማራ ታጣቂዎች ጋር በተደረገ የጥይት ተኩስ በግጭቱ ውስጥ ምንም ተሳትፎ ያልነበራቸው 3 የአካባቢው ነዋሪዎች ተገድለዋል። ከዚህ ግጭት ጋር ተያይዞ በተጠቀሱት ቀበሌዎች ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
- ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በግምት ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት አካባቢ በኦሮሚያ ክልል፣ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን፣ አቤ ዶንጎሮ ወረዳ፣ ጨሩ ቀበሌ በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ የተገለጸ የአማራ ታጣቂዎች ቡድን አባላት በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ በከፈቱት ተኩስ 22 ሰዎች ሲገደሉ በ4 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሷል። እንዲሁም 540 መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን እና በግምት 800 አካባቢ ከብቶች (በጎች እና ፍየሎችን ጨምሮ) በታጣቂ ቡድኑ መዘረፋቸውን ነዋሪዎች ያስረዳሉ።
- ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል፣ አርሲ ዞን፣ አሰኮ ወረዳ፣ ጠለፋ ጨፋ ቀበሌ ከቀኑ 11፡00 ሰዓት አካባቢ ሲሆን፣ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በማለት የሚጠራው ቡድን (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ታጣቂዎች ወደ ቀበሌው ገብተው የቀበሌው አስተዳደር ሲቪል ሠራተኞች እና ከመንግሥት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠቆሙ ነዋሪዎችን ለይተው በወሰዱት ጥቃት አቶ ገበየሁ ጸጋዬ፣ መምህር በላይነህ ደመሬ እና አቶ ገዛኸኝ መንግሥቱ የተባሉ ሰዎችን ገድለው፣ አቶ መብራቱ መንግሥቱ በተባሉት ሰው ላይ በእግራቸውና እጃቸው ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፤ ለጊዜው ብዛታቸው በትክክል ያልተረጋገጠ የነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶችን አቃጥለዋል። እንዲሁም ብዛታቸው ያልታወቀ ሰዎች ጥቃቱን በመሸሽ አካባቢውን ለቀው ወደ አሰኮ ከተማ አካባቢ ሠፍረው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል። ይህ ሪፖርት በተዘጋጀበት ወቅት የመንግሥት ኃይሎች ቀበሌውን እንደተቆጣጠሩ፣ ታጣቂዎቹ ቦታውን ለቀው እንደወጡ እና የወረዳው አስተዳደር ተጎጂዎችን አወያይቶ ወደ ቀያቸው እየመለሰ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።
- በኦሮሚያ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ አቦቴ ወረዳ፣ ኤጄሬ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ተስፋ ቦጃ የተባሉ ሰው “የኦነግ ሸኔ ሎጅስቲክ ነው’’ በሚል ጥርጣሬ ነሐሴ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. በሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ተይዘው ለ1 ቀን በከተማው በሚገኘው የወታደሮች ካምፕ ከታሰሩ በኋላ፣ በነጋታው ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ተገድለው አስከሬናቸው በመኖሪያ ቤታቸው አካባቢ ባለው አውራ መንገድ ላይ ተጥሎ ተገኝቷል።
- በኦሮሚያ ክልል፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ባሉት አንዳንድ ወረዳዎች ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በማለት በሚጠራው ቡድን (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ታጣቂዎች በሐምሌ እና በነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም. ብቻ ከ14 ያላነሱ ሰላማዊ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ግድያ ስለመፈጸሙ ከተለያዩ አካላት ከተሰበሰቡ መረጃዎች ለመገንዘብ ተችሏል።
- በኦሮሚያ ክልል፣ ምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ ጊዳ አያና ወረዳ አንዶዴ ዲቾ ቀበሌ ነሐሴ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. የ03 ቀበሌ ነዋሪዎች ወደ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለአምልኮ ሲሄዱ በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የአማራ ታጣቂዎች በተፈጸመባቸው ጥቃት 3 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።
- በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ የኤፍራታና ግድም ወረዳ አስተዳዳሪ ግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. እና የቀወት ወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት በመኖሪያ ቤታቸው ተገድለዋል።
- በአማራ ክልል፣ ምዕራብ ጎንደር ዞን፣ በቋራ ወረዳ ከግንቦት ወር መጀመሪያ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የአማራ እና የአገው ብሔረሰብ ተወላጆች በሚኖሩባቸው ቀበሌዎች ማለትም ይካዎ፣ አብተጋሆ፣ አጋም ውሃ፣ ገለሎ፣ ባምባ ውሃ እና ሌሎች ቀበሌዎች ላይ በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት የመንግሥት የሚሊሻ አባላት ትጥቃቸውን እንዲያስረክቧቸው ጥያቄ በማቅረባቸው እና የሚሊሻ አባላቱ የመንግሥትን ትጥቅ እንደማያስረክቡ በመናገራቸው ግጭቶች መነሳት መጀመራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። የግጭቱ መነሻ እና መባባስን በተመለከተ የአካባቢው ሰዎች እንደሚያስረዱት በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. የሚሊሻ አባላት ትጥቅ ለማስፈታት የመጡ ከ12 በላይ የሚሆኑ በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላትን በቁጥጥር ሥር አውለው ለመንግሥት ያስረክባሉ። በዚህ የተበሳጩ የታጠቀ ቡድኑ አባላት በአብተጋሆ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ሰዎችን፣ ሴቶች እና ሕፃናትን ጨምሮ፣ 23 ሲቪል ሰዎችን አፍነው ወደ ቴዎድሮስ ከተማ በመውሰድ የተወሰኑት ሲመለሱ ሌሎችን ገድለዋል። በዚህ ግጭት ምክንያት በሚሊሻ አባላት እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን አባላት መካከል ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የተቀሰቀሰው ግጭት ተባብሶ ሐምሌ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ወደ ማኅበረሰብ ግጭት ተሸጋግሮ ባይካዎ እና አጋም ውሃ ቀበሌዎች ከሁለቱም ብሔር ተወላጆች ብዛታቸው ያልታወቀ ሰዎች ሕይወት አልፏል። ከሟቾች መካከልም ግጭቱን ማምለጥ ያልቻሉ አረጋውያን፣ ሴቶች እና ሕፃናት የሚገኙበት መሆኑን እና በዚሁ ግጭት ቤቶች እና የሰብል ማሳ መቃጠላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
- ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ሌሊት በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት ከክልሉ አዊ ብሔረሰብ ዞን፣ ቲሊሊ ከተማ አሽፋ ቀበሌ እንደወጡ የመንግሥት የጸጥታ አካላት ወደ ቀበሌው በመግባት ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጠዋት ጀምሮ እስከ ቀኑ 8፡00 ሰዓት ድረስ ቤት ለቤት በመፈተሽ “ፋኖን ትደግፋላችሁ፤ ትቀልባላችሁ፤ ቤት ታከራያላችሁ” እንዲሁም “የፋኖ አባላት ናችሁ” ብለው የጠረጠሯቸውን 10 ሲቪል ሰዎች በጥይት መግደላቸው ታውቋል።
- ከአማራ ክልል፣ አዊ ብሔረሰብ ዞን፣ ቲሊሊ ከተማ በ8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ወንጀላ ቀበሌ ሰኔ 5 ለሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም. አጥቢያ ሌሊት ላይ በመንግሥት ጸጥታ አካላት እና በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት መካከል የተደረገውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ የ“ፋኖ”ታጣቂዎች ቀበሌውን ለቀው ከወጡ እና ጦርነቱ ከቆመ በኋላ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ወደ ቀበሌዋ በመግባት ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ ቤት ለቤት እየዞሩ “ፋኖን ትደግፋላችሁ፤ ትቀልባላችሁ” በማለት 5 ሰዎችን ከቤታቸው አስወጥተው የገደሉ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል። ከሟቾቹ መካከልም 1 የ75 ዓመት አረጋዊ እንደሚገኙበት ተገልጿል።
- ሰኔ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት አካባቢ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከአማራ ክልል ሞጣ ከተማ ወደ ቀራንዮ ከተማ መኪና አጅበው በመጓዝ ላይ እያሉ መንገድ ላይ በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት የደረሰባቸውን የደፈጣ ጥቃት ተከትሎ የሰራዊቱ አባላት ወደ ቀራኒዮ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ በመግባት የዕድራቸው አባል የሆኑ መነኩሴ ሞተው የቀብር ቦታ በመቆፈር ላይ የነበሩ 6 የከተማው ነዋሪዎችን እንዲሁም 1 የአብነት ተማሪን የገደሉ መሆኑን የዐይን ምስክሮች አስረድተዋል።
- ሰኔ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 8:00 ሰዓት አካባቢ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ ሜጫ ወረዳ ተነስተው ወደ ሰሜን ሜጫ ወረዳ ወተት አባይ ቀበሌ አቅጣጫ በመጓዝ ላይ እያሉ መከኒ ዋርካ ቀበሌ አልቃ በተባለ ቦታ ላይ በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በበቀል ስሜት በጉዟቸው ላይ ያገኟቸውን 10 አርሶ አደሮችን በጥይት የገደሉ፣ሌሎች 2 አርሶ አደሮችን ደግሞ ያቆሰሉ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል።
- ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. በግምት ከቀኑ 12፡00 ሰዓት አካባቢ በአማራ ክልል፣ ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ጅጋ ከተማ አስተዳደር፣ “ጎህ” በተባለ ካፌና ሬስቶራንት ውስጥ የነበሩ ሰዎችን ጨምሮ ቢያንስ 16 ሰዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦች፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና የመንግሥት አስተዳደር አካላት ገልጸዋል። አንድ የመንግሥት ኃላፊ የግድያውን መነሻ ምክንያት ሲያስረዱ “በዕለቱ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ከከተማ ውጭ ቆይተው ሲመለሱ በተተኮሰባቸው ጥይት 2 አባላት መቁሰላቸውን እና 1 ወታደር ተደብድቦ ጉድጓድ ውስጥ ወድቆ ማግኘታቸውን ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ‘ፋኖ ያለበትን አሳዩን’፤ ‘መረጃ ስጡን’፤ ‘ምን እንደተፈጠረ ተናገሩ’ በሚል በሬስቶራንት ውስጥ የነበሩ ሰዎች እና ተኩሱን ሰምተው በመሮጥ ላይ የነበሩ ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል” በማለት ገልጸዋል። ከሟቾች መካከል 2 አእምሮ ሕመም ያለባቸው ሰዎች እንዲሁም በሬስቶራንቱ ሲስተናገዱ የነበሩ የአቢሲኒያ ባንክ እና የአዋሽ ባንክ ሠራተኞች ይገኙበታል።
- በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችና በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት መካከል ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎጃም ዞን፣ አዴት ከተማ ላይ በተካሄደ የትጥቅ ግጭት አባትና ልጅን ጨምሮ በግጭቱ ተሳትፎ የሌላቸው ሰዎች ተገድለዋል። ከግጭቱ ጋር በተያያዘ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከ3 ወር በፊት ተይዘው ካምፕ ውስጥ ታስረው የነበሩ 3 የ“ፋኖ” አባላት በጸጥታ ኃይሉ ተገድለው አስከሬናቸው ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ተጥሎ መገኘቱን ኢሰመኮ ለማወቅ ችሏል። በተመሳሳይ በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት በበቀል ስሜት በቁጥጥር ሥር አውለዋቸው የነበሩትን የሚሊሻና የአድማ ብተና አባላት ሰኔ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደገደሏቸው ለማወቅ ተችሏል።
- በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ጣርማ በር ወረዳ፣ ከደብረ ሲና ከተማ ወጣ ብላ በምትገኝ ሾላ ሜዳ በተባለች ቦታ ሰኔ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላትን ለመክበብ ሲሄዱ ታጣቂዎቹ ቀድመው ይወጣሉ። ይህንን ተከትሎ የመንግሥት የጸጥታ አባላት በመንገድ ያገኟቸውን፣ ቤታቸው በር ላይ ቆመው የነበሩ እና ሻይ ቤቶች አካባቢ የተገኙ በድምሩ 15 ሲቪል ሰዎችን “ለፋኖ መረጃ ትሰጣላችሁ፣ ፋኖን ትደብቃላችሁ” በሚልና በመሰል ምክንያቶች ግድያ እንደፈጸሙባቸው የሟች ቤተሰቦች አስረድተዋል።
- ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ∙ም. በአማራ ክልል፣ ሰሜን ወሎ ዞን፣ ውርጌሳ ከተማ አካባቢ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት መካከል የትጥቅ ግጭት መካሄዱን ተከትሎ በአካባቢው ከነበረው የመንግሥት የጸጥታ ኃይል የተተኮሰ ከባድ መሣሪያ መኖሪያ ቤቶች ላይ ወድቆ በ4 የአንድ ቤተሰብ አባላት እና በሌላ 2 የቤተሰብ አባላት ላይ በድምሩ 6 ሰዎች ላይ 1 የሞት እና 5 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት አድርሷል። ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች ውስጥ 4ቱ ሕፃናት ሲሆኑ ቀሪ 2ቱ ደግሞ የሕፃናቱ ወላጆች ናቸው።
- በአማራ ክልል፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ አህመድ አሊ ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡00 ሰዓት አካባቢ መስጊድ ቆይተው ወደቤታቸው ሲመለሱ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች ተገድለዋል።
- ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት አካባቢ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች አቶ ይመር መስፍን የተባሉትን ሰው “ፋኖ ነህ፤ ልጆችህም ፋኖ ናቸው” በማለት ከአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎጃም ዞን፣ ሰሜን ሜጫ ወረዳ፣ ወተት አባይ ቀበሌ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አስወጥተው በባዶ እግራቸው ወደ አምቦ መስክ ቀበሌ ከወሰዷቸው በኋላ ገድለው አስከሬናቸውን ጥለውት የሄዱ መሆኑን፣ አስከሬኑም ሲታይ አካላቸው የተለያየ ቦታ ተወግቶና ተበሳስቶ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ መሆኑን እንደሚያሳይ ምስክሮች ገልጸዋል።
- ሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ∙ም. በአማራ ክልል፣ ጉባ ላፍቶ ወረዳ፣ ውድመን ቀበሌ ላይ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት መካከል በትጥቅ የታገዘ ግጭት መካሄዱን ተከትሎ በአካባቢው ከነበረው የመንግሥት የጸጥታ ኃይል በተተኮሰ ከባድ መሣሪያ ቢያንስ 7 ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል።
- በአማራ ክልል፣ ምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ እነብሴ ሳር ምድር ወረዳ፣ ዶማ በተባለ አካባቢ የነበረውን ግጭት ተከትሎ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ∙ም. 1 የ“ፋኖ” ታጣቂ አባል ቆስሎ 2 ወንድሞቹ ሊያነሱት ሲሄዱ 3ቱም ወንድማማቾች በመንግሥት የጸጥታ አባላት መገደላቸውን ኢሰመኮ የደረሰውን አቤቱታ መነሻ በማድረግ ባደረገው ማጣራት ማረጋገጥ ችሏል።
- ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል፣ ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ቋሪት ወረዳ፣ ገነት አቦ ከተማ ሲካሄድ የዋለው ውጊያ ከቆመ በኋላ የመንግሥት ጸጥታ አባላት ቤት ለቤት ፍተሻ እያካሄዱ በነበሩበት ወቅት አቶ ካሳ ምትኩ የተባሉ መስማት የተሳናቸውና የሚጥል በሽታ ተጠቂ የነበሩ ግለሰብን ከቤታቸው በር ላይ ከሕግ ውጭ ግድያ የፈጸሙባቸው መሆኑን ኢሰመኮ ለማረጋገጥ ችሏል። ከዚህ በተጨማሪ የመንግሥት የጸጥታ አባላት በዚሁ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ 2 ቤታቸው ውስጥ የነበሩ ሴቶችን በር እንዲከፍቱ ጠይቀዋቸው በፍርሀት ባለመክፈታቸው በመስኮት በኩል ጥይት ተኩሰው የአካል ጉዳት ያደረሱባቸው ስለመሆኑ ኢሰመኮ ካሰባሰባቸው መረጃዎች መረዳት ችሏል።
- በአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎጃም ዞን፣ ሰሜን ሜጫ ወረዳ፣ ወተት ዓባይ ቀበሌና በአካባቢው በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት መካከል ከነሐሴ 6 እስከ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ከተካሄደ ውጊያ ጋር በተያያዘ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በመንገድና ቤታቸው ውስጥ ያገኟቸውን በግጭቱ ተሳትፎ ያልነበራቸውን 7 ሰዎች እንደገደሉ ነዋሪዎች አስረድተዋል። ከሟቾች ውስጥ 1 በአካባቢው የማኅበረ ሥነ ልቦና ጉዳት እንዳለበት የሚታወቅ ሰው እና 1 የ17 ዓመት ልጅ ይገኙበታል። በተጨማሪ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ከንጋቱ 11፡30 ሰዓት አካባቢ ቄስ አወቀ መኮንን የተባሉ አረጋዊ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለማከናወን ወደ አቡነ ዘርዓብሩክ ቤተክርስቲያን በመጓዝ ላይ እያሉ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በጥይት እንደተገደሉ ለማወቅ ተችሏል።
- ነሐሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል፣ ደቡብ ጎንደር ዞን፣ እስቴ እና አንዳ ቤት ወረዳ አስተዳደር አመራሮች ለስብሰባ ወደ ደብረ ታቦር ከተማ በጉዞ ላይ እንዳሉ በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት ባደረሱት ጥቃት የሞትና የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ለመረዳት ተችሏል።
- ነሐሴ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል፣ ምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ደብረወርቅ ከተማ አካባቢ በመንግሥት ወታደሮች እና በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት መካከል የተደረገውን ውጊያ ተከትሎ አቶ ዘውዴ ጫኔ እና አቶ እንቻለው መኮንን የተባሉ አርሶ አደሮች ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከሚተኮሰው ከባድ መሣሪያ እራሳቸውን ለማዳን ሲሸሹ የመንግሥት የጸጥታ አባላት መንገድ ላይ ከያዟቸው በኋላ የ“ፋኖ ደጋፊ ናችሁ” በሚል በጥይት የገደሏቸው መሆኑን ማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን፣ የመንግሥት የጸጥታ አባላት የሟቾችን የእጅ ስልክ በመውሰድና ለቤተሰቦቻቸው በመደወል ጸያፍ ስድቦችን እንደሰደቧቸው እንዲሁም “እናጠፋችኋለን” ብለው እንደዛቱባቸው ምስክሮች ገልጸዋል።
- በአማራ ክልል፣ ባሕር ዳር ከተማ፣ አባይ ማዶ ዘንዘልማ በሚባለው አካባቢ በሚገኘው የገበያ ማእከል አካባቢ ሰሳ በረት በሚባል ቦታ 4 ወጣቶች እና አሽራፍ በሚባል አካባቢ 2 ወጣቶች በድምሩ 6 ወጣቶች ለጊዜው ባልታወቁ አካላት እጃቸውን የኋሊት ታስረው በጥይት እና በስለት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለው ነሐሴ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ተገኝተዋል።
- ነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ከምሽቱ ከ1፡00 እስከ 1፡30 ሰዓት ባለው ጊዜ በአማራ ክልል፣ ባሕር ዳር ከተማ፣ በተለምዶ ቀበሌ 5 በግ ተራ አካባቢ “ሜላት ካፌ” በመባል ከሚጠራው ስፍራ ጀምሮ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች (የአድማ ብተና ፖሊስ ዩኒፎርም የለበሱ) በከፈቱት እሩምታ ተኩስ በጎዳና አነስተኛ ሥራ እና በልመና ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሲቪል ሰዎች ላይ 2 የሞት እና 10 የአካል ጉዳት እንደደረሰ ለማረጋገጥ ተችሏል። ሟቾች 1 ዐይነ ሥውር የ11ኛ ክፍል ተማሪ እና ድንች ቅቅል ጎዳና ላይ በመሸጥ የምትተዳደር 1 ሴት ሲሆኑ ከቆሰሉት መካከል ደግሞ 1 ዐይነ ሥውር የ11ኛ ክፍል ተማሪ እና 1 የሟቿ ሴት ሕፃን ልጅ እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል።
- ነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ጠዋት በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል የነበረውን የትጥቅ ግጭት ተከትሎ በአማራ ክልል፣ ሰሜን ወሎ ዞን፣ ራያ ቆቦ ከተማ ዙሪያ የቆቦ ከተማ እና የዋጃ ከተማ ነዋሪ የሆኑ 4 ወጣቶች ባልታወቁ ሰዎች ተገድለው የተገኙ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
- በአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎጃም ዞን፣ ባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ፣ ይነሳ እና ይባብ ቀበሌ የሚገኙ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች (የአድማ ብተና ፖሊስ አባላት እና ሚሊሻ) በአካባቢው ምንም ግጭት ሳይኖር በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል ሲሉ ነዋሪዎች አስረድተዋል። ለምሳሌ ነሐሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. ይባብ ቀበሌ ከቀኑ 9፡30 ሰዓት ላይ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ወ/ሮ መብራቴ መኳንንት (61 ዓመት፣ አርሶ አደር እና 10 ሰዎች ያሉበት ቤተሰብ አስተዳደሪ) እና ወ/ሮ ነጻነት ምትኩ (25 ዓመት፣ አርሶ አደር) ከቤተክርስቲያን ተመልሰው መኖሪያ ቤታቸው ሲደርሱ በጥይት የገደሏቸው ሲሆን፣ የሟች ልጅ የሆኑትን ወ/ሮ ውብእህል ተባባል (25 ዓመት፣ አርሶ አደር) ደግሞ በተጠቀሰው ጊዜና ቦታ የቀኝ እጃቸውን በጥይት በመምታት የአካል ጉዳት አድርሰውባቸዋል። ነሐሴ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ይባብ ቀበሌ ጭንጫር ጎጥ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ አቶ ወርቁ ስሜ የተባሉትን የ74 ዓመት አርሶ አደር በመኖሪያ ቤታቸው ቡና በመጠጣት ላይ እያሉ የአድማ ብተና ፖሊስ አባላት ወደ መኖሪያ ቤታቸው በኃይል በመግባት ግለሰቡና ቤተሰቦቻቸው ላይ ድብደባ ከፈጸሙ በኋላ፣ ግለሰቡን በመኪና ጭነው ወደ ካምፓቸው ወስደው ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ላይ መልሰው ወደ መኖሪያ ቤታቸው አካባቢ በማምጣት ከመኪና ላይ ገፍትረው አስፓልት መንገድ ላይ በመጣል በ3 ጥይቶች ተኩሰው ገድለዋቸዋል። ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ይባብ ቀበሌ ከጠዋቱ 2፡30 ሰዓት ላይ አቶ ታደለ እውነቴ (42 ዓመት፣ አርሶ አደርና 4 ሰዎች ያሉበት ቤተሰብ አስተዳዳሪ) የበቆሎ ማሳ ለማሳረም የቀን ሠራተኞችን መንገድ ዳር ቆመው በመጠባበቅ ላይ እያሉ የአድማ ብተና ፖሊስ አባላት ጭንቅላታቸውን በ2 ጥይቶች መተው ገድለዋቸዋል። ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ይነሳ ቀበሌ ድንጅማ በተባለ አካባቢ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ላይ አቶ ላቀ ቢተው (46 ዓመት፣ አርሶ አደር እና 7 ሰዎች ያሉበት ቤተሰብ አስተዳዳሪ) ከብቶቻቸውን ወደ ቤታቸው እየነዱ በመሄድ ላይ እያሉ የአድማ ብተና ፖሊስ አባላት 2 እግራቸውን በጥይት በመምታት የአካል ጉዳት ያደረሱባቸው ሲሆን በኢሰመኮ ክትትል ወቅት ሕክምናቸውን በፈለገ ሕይወት ሆስፒታል በመከታተል ላይ ይገኙ ነበር። ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ይነሳ ቀበሌ አማስሬ በተባለ አካባቢ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ላይ አቶ ወርቁ ሞት ባይኖር (የ70 ዓመት አረጋዊና 7 ሰዎች ያሉበት ቤተሰብ አስተዳዳሪ) የጫት ማሳቸውን በማረም ላይ እያሉ በአድማ ብተና ፖሊስ 2 እግራቸውን በጥይት ተመተው ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በኢሰመኮ ክትትል ወቅት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ጊዮን ሆስፒታል ሕክምናቸውን በመከታተል ላይ ይገኙ ነበር።
- በአማራ ክልል፣ ማእከላዊ ጎንደር ዞን፣ አለፋ ወረዳ፣ ሻውራ ከተማ ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት እስከ ቀኑ 7፡30 ሰዓት ድረስ በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል በተደረገው ከባድ ውጊያ ከ10 በላይ ሲቪል ሰዎች ከየትኛው ወገን እንደተተኮሰ ባልታወቀ ተባራሪ ጥይት እንዲሁም ግጭቱ ከቆመና ታጣቂዎች ለቀው ከወጡ በኋላ “ታጣቂዎችን ትደግፋላችሁ”፣ “መረጃ ትሰጣላችሁ” በሚል የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት በመሄድና መንገድ ላይ ያገኟቸውን ሰዎች እንደገደሉ ነዋሪዎችና የተጎጂ ቤተሰቦች አስረድተዋል።
- ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ከምሽቱ 3:00 ሰዓት ላይ በአማራ ክልል፣ ጎንደር ከተማ፣ ማራኪ ክፍለ ከተማ፣ ቀበሌ 16 ልደታ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ማንነታቸው ያልታወቀ የታጠቁ ቡድኖች ወ/ሮ መብራት ኪዳነ ማርያም ወደ ተባሉ ግለሰብ መኖሪያ ቤት በኃይል በመግባት በአምላክ አብርሃም ከተባለች የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ልጃቸው ጋር በጥይት ደብድበው ገድለዋቸዋል። በእናትና ልጅ ላይ የተፈጸመው ግድያ ምን አልባት ጥቃት ፈጻሚዎቹ “የእገታ ሙከራ” ሲያደርጉ ተጎጂዎች ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ወይም ራሳቸውን በመከላከላቸው ምክንያት በአጋቾቹ በተወሰደ እርምጃ ሊሆን እንደሚችል የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
- ነሐሴ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል፣ ጎንደር ከተማ፣ ቀበሌ 03 ከጠዋቱ 3፡30 ሰዓት ላይ ሕፃን ኖላዊት ዘገየ የተባለች የ2 ዓመት ታዳጊ በወላጆቿ መኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥ በመጫወት ላይ እያለች ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች የታገተች መሆኑን፤ የሕፃኗ ወላጅ አባትም ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ስልክ ተደውሎ ለሕፃኗ ማስለቀቂያ 1 ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ የተጠየቁ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል። ይሁን እንጂ የሕፃኗ ወላጅ አባት በሹፍርና ሙያ ተቀጥረው የሚሠሩ በመሆኑ የተጠየቀውን ገንዝብ ለመክፈል እንደማይችሉ በመግለጽ ከአጋቾች ጋር በስልክ በመደራደር 300,000 ብር ለመክፈል ይስማማሉ። ሆኖም የሕፃኗ ቤተሰቦች ከተለያዩ ሰዎችና ዘመዶቻቸው በመለመን የተጠየቀውን ገንዘብ አሰባስበው ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ ሸዋ ዳቦ ከተባለ አካባቢ በመሄድ በባጃጅ ገንዘቡን ለአጋቾች በመላክ ልጃቸውን እንዲሰጧቸው ሲጠይቁ “መኖሪያ ቤታችሁ ታገኟታላችሁ” የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸው ወደ መኖሪያ ቤታቸው በመመለስ ላይ እያሉ ሕፃኗ መኖሪያ ቤታቸው አካባቢ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድላ ተጥላ ተገኝታለች። ይህንን ተከትሎ የከተማው ነዋሪዎች ወደ አደባባይ በመውጣት ማእከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት አካባቢ በመሰባሰብ ድርጊቱን በማውገዝ በጎንደር ከተማ እየተፈፀመ ያለው እገታ እንዲቆም ድምጻቸውን በሰላማዊ ሰልፍ አሰምተዋል። የመንግሥት ጸጥታ አካላት ሰልፈኞቹን ለመበተን በተኮሱት ጥይት ቢያንስ 3 ሰልፈኞችን የገደሉ ሲሆን ከ11 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት የደረሰ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። የጎንደር ከተማ አስተዳደር ጸጥታ ምክር ቤት ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ሕፃን ኖላዊት ዘገየ እንዲሁም ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ደግሞ ወ/ሮ መብራት ኪዳነ ማርያም እና ልጃቸው በአምላክ አብርሃም ላይ የግድያ ወንጀል በአጋቾች የተፈጸመ መሆኑን አረጋግጧል። መንግሥት በእገታ፣ በግድያና በዘረፋ ወንጀል የተጠረጠሩ 49 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ያዋለ ሲሆን የሕፃን ኖላዊት ዘገየን ሞት ተከትሎ ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በሲቪል ሰዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በማጣራት እና እርምጃ በመውሰድ ውጤቱን ለሕዝብ እንደሚያሳውቅ ምክር ቤቱ ገልጿል። ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ባወጣው መግለጫ የሥነ-ምግባር ብልሽት ያለባቸው፣ ኃላፊነታቸውን ከመወጣት ይልቅ የእገታው አባሪና ተባባሪ በመሆን የተጠረጠሩ 14 የጸጥታ አካላት ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን ገልጿል።
- ጳጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል፣ ጎንደር ከተማ አስተዳደር፣ አዘዞ ጸዳ ክፍለ ከተማ፣ ጸዳ ቀበሌ ጤና ጣቢያ አካባቢ 1 የመንግሥት የጸጥታ አባል ተገድሎ መገኘቱን ተከትሎ ከቀኑ 5፡00 ሰዓት እስከ 6:00 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጸዳ ካምፓስ የነበሩ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከተለያዩ አካባቢዎች ለገበያ ወደ ተሰበሰቡ ሰዎች ጥይት በመተኮስ 3 ሰዎችን እንዲሁም አስፓልት መንገድ ላይ ያገኟቸውን 8 ወጣቶች በአጠቃላይ ቢያንስ 11 ሲቪል ሰዎችን የገደሉ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል።
- መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም. በአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ደባርቅ ከተማ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጣቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት መካከል ከጠዋት እስከ እኩለ ቀን ድረስ ከተካሄደው የትጥቅ ግጭት ጋር በተያያዘ ዒላማቸውን ባልጠበቁ ተኩሶች እና በተባራሪ ጥይቶች ቢያንስ 20 ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉ ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎች እና የዐይን ምስክሮች አስረድተዋል። 9 ሰዎች ደግሞ ከቤታቸው እየተወሰዱ በመንግሥት የጸጥታ አካላት እንደተገደሉ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ከእነዚህ ውስጥ ከገጠር ወደ ደባርቅ ከተማ መጥተው አልጋ ይዘው የነበሩ 5 መምህራን ይገኙበታል። በተጨማሪ ዒላማቸውን ባልጠበቁ ተኩሶች እና በተባራሪ ጥይቶች 36 ሲቪል ሰዎች ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ደባርቅ አጠቃላይ ሆስፒታል ገብተው የሕክምና አገልግሎት ያገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 1 የ3 ዓመት ሕፃንን ጨምሮ 2 ሰዎች እንደሞቱ ለማወቅ ተችሏል።
- በከተሞች የሚፈጸሙ የቦምብ ጥቃቶች
- ነሐሴ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 9፡50 ሰዓት፣ ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ረፋድ ላይ፣ ነሐሴ 9 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. እና ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት 1፡00 ሰዓት ገደማ በአማራ ክልል፣ ባሕር ዳር ከተማ በተለያዩ ቦታዎች በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት እንዲሁም ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች የተፈጸሙ የቦንብ ፍንዳታዎች በነዋሪዎች ላይ የደኅንነት ሥጋት ከመደቀናቸው ባሻገር ለጊዜው ብዛታቸው ባልታወቁ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል። ነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ገደማ በአንድ የመንግሥት መኪና ላይ በደረሰ የቦንብ ፍንዳታ የመኪናው ሾፌር ከቆሰለ በኋላ ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ሕይወቱ ያለፈ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል። በሌሎችም የክልሉ ከተሞች ተመሳሳይ የቦምብ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ስለመሆኑ ኢሰመኮ ለመገንዘብ ችሏል።
- የዘፈቀደ፣ ሕገወጥ፣ ጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት
- ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ አዋሽ አርባን ጨምሮ በተለያዩ መደበኛ እና መደበኛ ባልሆኑ ማቆያዎች በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩት አብዛኛዎቹ ተጠርጣሪዎች ከእስር የተለቀቁ እና ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተደረገ መሆኑ አበረታች ቢሆንም፣ በአስቸኳይ ጊዜ ወቅት የሕግ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥልጣን የሌላቸው የጸጥታ አካላት ጭምር ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውለው የነበረ በመሆኑ በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩ በርካታ ሰዎች ብሔርን መሠረት ያደረገ ስድብ፣ በቂ ብርሃን በማያስገባ ጨለማ ቤት መያዝ፣ ድብደባን ጨምሮ የተለያዩ የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸሙባቸው እና ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የተዳረጉ መሆኑን ተጎጂዎች ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ለበርካታ ወራት በእስር ቆይተው የተለቀቁ ግለሰቦች በእስር ለቆዩበት ጊዜ አሁን ድረስ መረጃ ለማቅረብ ባለመቻላቸው ወደ ሥራቸውና ማኅበራዊ ሕይወታቸው ለመመለስ ከፍተኛ ችግር ያጋጠማቸው መሆኑን አክለው አስረድተዋል።
- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተፈጻሚነት ጊዜ ያበቃ ቢሆንም “ሸኔ”ን እና “ፋኖ”ን ይደግፋሉ የተባሉ ሰዎች ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ፖሊስ ጣቢያዎች “ወቅታዊ ጉዳይ”/“ሀላ የሮ” በሚል ከቀናት እስከ ወራት እስር በኋላ በርካቶች ቢለቀቁም ሌሎች አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ። ለምሳሌ ኅዳር 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል፣ ሸገር ከተማ፣ መልካ ኖኖ ክፍለ ከተማ፣ አሸዋ ሜዳ ፖሊስ ጣቢያ በቁጥጥር ሥር ውለው የሚገኙት አቶ ሳሙኤል ሌሊሳ “ከሸኔ ጋር በተያያዘ የሚፈለግ ነው” በሚል ይህ ሪፖርት እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእስር ላይ ይገኛሉ። አቶ ያደታ ጀቤሳ ቀልቤሳን ጨምሮ 18 ሰዎች ከኅዳር 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከየሥራ ገበታቸውና መኖሪያ አካባቢያቸው በቁጥጥር ሥር ውለው ይህ ሪፖርት እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በከተማው መልካ ኖኖ ክፍለ ከተማ በእስር ላይ ይገኛሉ። ለኢሰመኮ በቀረበው አቤቱታ መሠረት ከተጠርጣሪዎቹ መካከል 4ቱ በኦሮሚያ ክልል፣ ሸገር ከተማ፣ ለመልካ ኖኖ ወረዳ ፍርድ ቤት አካልን ነጻ የማውጣት ክስ አቅርበው ፍርድ ቤቱ ከእስር እንዲፈቱ ትእዛዝ የሰጠ ቢሆንም አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል። በተመሳሳይ አቶ ቢቂላ ጉርሜሳ፣ አቶ ለሜሳ ባጫ እና አቶ ገመቹ ዘላለም የተባሉ ግለሰቦች የካቲት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. “ለሸኔ ሎጂስቲክስ ታቀርባላችሁ” በሚል እና “ወንጀሉ የተፈጸመበት ሆሮ ጉድሩ አካባቢ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እስከሚሻሻል” በሚል በአደራ እስረኝነት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በቁጥጥር ሥር ውለው ይገኛሉ።
- ምንም እንኳን ለ10 ወራት የቆየው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ያበቃ ቢሆንም እና በጊዜያዊ ማቆያ ቦታዎች የተደራሽነትና የጸጥታ ችግር በመኖሩ ክትትል ለማድረግ ባይቻልም በአማራ ክልል፣ በተለይም በወልዲያ፣ እንጅባራ፣ ጋይንት፣ ደብረ ማርቆስ እና ባሕር ዳር ከተሞች በሚገኙ የተለያዩ ማረሚያ ቤቶች፣ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ ወታደራዊ ካምፖችና ሌሎች ማቆያ ቦታዎች ሰዎች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ታስረው እንደሚገኙ፣ አንዳንዶች በሕገ ወጥ ወይም በዘፈቀደ እስር ቆይተው የሚለቀቁ እንዳሉ መረጃዎች ያስረዳሉ። ለምሳሌ በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ሊቦ ከምከም ወረዳ፣ አዲስ ዘመን ከተማ፣ ቀበሌ 03 ነዋሪ የሆኑትን አቶ አይቸው ፈረደ እና አቶ ይሰጣል ሻረው የተባሉ ሰዎች ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ላይ በሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ተይዘው ፎገራ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት በአደራ ታስረው ቆይተው አቶ ይሰጣል መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም. አቶ አይቸው ደግሞ መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም. ተለቀዋል። ሰዎቹ የታሰሩት የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወንድም በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት ታግቶ የተወሰደ በመሆኑ እና ግለሰቦቹ የአጋቾቹ ዘመዶች ናቸው በሚል ምክንያት እንደ መያዣ የታሰሩ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል። ግለሰቦቹ እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ እስከተለቀቁበት ጊዜ ድረስ ፍርድ ቤት ያልቀረቡና ክስ ያልተመሠረተባቸው መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል።
- በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጉራጌ ዞን፣ ወልቂጤ እና አበሽጌ ወረዳዎች እንዲሁም በዳልጋ ከተማ በኦሮሚያ እና በማእከላዊ ኢትዮጵያ አካባቢ ባሉ ግጭቶች ተሳትፈዋል እና በግጭቱ ለተሳተፉ ሰዎች ድጋፍ አድርገዋል በሚል ጥርጣሬ ከሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩ 71 ወንዶችና እና “በጫካ ለሚገኙ ባለቤቶቻቸው ስንቅ ያቀብላሉ” እንዲሁም “ባለቤቶቻቸው በቁጥጥር ሥር እስኪውሉ ድረስ በእነሱ ምትክ” በሚል በቁጥጥር ሥር የዋሉ 11 ሴቶች እስከ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ከ20 ቀናት በላይ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእስር እንዲቆዩ ተደርገዋል።
- ተስፋዬ ሽፈራው አዳል የተባሉትን ጨምሮ 12 ሰዎች ከጳጉሜን 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ “የብሔር ግጭት አስነስታችኋል” በሚል ምክንያት በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋምቤላ ቅርንጫፍ ተይዘው በጊዜ ቀጠሮ ጋምቤላ ከተማ ዙሪያ ማረሚያ ቤት ከገቡ በኋላ ያለመደበኛ ክስ እና የፍርድ ቤት ቀጠሮ ለ12 ወራት ያህል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ተይዘው ከቆዩ በኋላ ነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም. በጋምቤላ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋስትና ተፈቅዶላቸው ከማረሚያ ቤት ሊለቀቁ ችለዋል።
- እገታ
- በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከተራዘሙ የትጥቅ ግጭቶች ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የሕግ ማስከበር እና የመንግሥት መዋቅር መላላት ሳቢያ የሚፈጸሙ እገታዎች ተባብሰውና ተስፋፍተው የቀጠሉ መሆናቸውን አስመልክቶ ኢሰመኮ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። በዚህም መግለጫ እንደተብራራው እገታዎቹ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በታጣቂ ኃይሎች፣ ለዘረፋ በተደራጁ ቡድኖች እንዲሁም በአንዳንድ የመንግሥት የጸጥታ አካላት አባላት የሚፈጸሙ መሆናቸውን የኢሰመኮ የክትትል እና ምርመራ ሥራዎች አረጋግጠዋል። አጋቾች ሰላማዊ ሰዎችን በአብዛኛው በጉዞ (ትራንስፖርት) ላይ እያሉ አንዳንዴም ከመኖሪያ ቤታቸው ወይም ከሥራ ቦታቸው አግተው ወዳልታወቀ ቦታ በመውሰድ ከፍተኛ የማስለቀቂያ ገንዘብ ክፍያ እንደሚጠይቁ፤ ገንዘብ መክፈል ያልቻሉ በርካታ ታጋቾች ግድያን ጨምሮ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንደሚፈጸምባቸው፤ እገታው በአብዛኛው እንደ ገቢ ማስገኛ የተወሰደ መሆኑን፤ በተደጋጋሚ፣ በተንሰራፋና በተደራጀ መልኩ እንደሚፈጸም፤ አልፎ አልፎም እንደ በቀል፣ ለፖለቲካ ዓላማ ወይም የታገተ ሌላ ሰውን ለማስለቀቅ በሚል በአጸፋ መልኩ እንደሚፈጸም፤ ታጋች ሴቶች ለአስገድዶ መደፈር እና ለተለያየ ጾታዊ ጥቃት እንደሚዳረጉ ተገልጿል።
- የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) የቴሌቪዥን ክፍል ጋዜጠኛ የሆኑት ቃልኪዳን ግርማው ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ከመኖሪያ ቤታቸው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተይዘው ከተወሰዱ በኋላ ያሉበት እንደማይታወቅ ቤተሰቦቻቸው አስረድተዋል። ነሐሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ደግሞ በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት የአሚኮ ምክትል ሥራ አስፈጸሚ የሆኑት አቶ አንተነህ መንግሥቴን እና የአሚኮ የስትራቴጂክ ልማት ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ደምሳቸው ፈንታን ወደ ሥራ ቦታ በመንቀሳቀስ ላይ እያሉ አግተው እንደወሰዷቸው እና ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደለቀቋቸው ለማወቅ ተችሏል። በተመሳሳይ በነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ቀወት ወረዳ 1 የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ እና 3 የካሜራ ባለሙያዎች ማንነታቸው ባልታወቀ አካላት ታግተው ከ13 ቀናት በኋላ ነሐሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. መለቀቃቸውን ለመረዳት ተችሏል።
- የሀገር ውስጥ መፈናቀል
- መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በጋምቤላ ክልል ጆር ወረዳ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ሳቢያ ከኡቱዎል 01፣ ኡቱዎል 02፣ ከአለሚ፣ ሌሮ፣ ኡራሃ እና ቶው ቀበሌዎች በርካታ ነዋሪዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው 2,000 የሚጠጉ ሰዎች በኡንጎጊ ከተማ አሌላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው ሲኖሩ እንደነበረ እና አብዛኛው ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያ ቀያቸው በመመለሳቸው ከ350 እስከ 400 የሚደረሱ ተፈናቃዮች በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ በተሠራ ድንኳን እየኖሩ መሆኑን ኢሰመኮ ባሰባሰበው መረጃዎች መረዳት ችሏል።
- በነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም. በጋምቤላ ክልል ጎግ፣ ጆር፣ ላሬ እና ዋንቱዋ ወረዳዎች በሚገኙ ቀበሌዎች በተከሰተ የጎርፍ መጥለቅለቅ በርካታ ነዋሪዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን እና ወደ ሌላ ደረቃማ ስፍራ እንዲሰፍሩ መደረጉን ኢሰመኮ የአካባቢው ነዋሪዎችን እና የመንግሥት አካላትን በማነጋገር መረዳት ችሏል።
- በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን በቋራ ወረዳ በሚሊሻ አባላት እና በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት መካከል ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የተቀሰቀሰው የትጥቅ ግጭት ተባብሶ ሐምሌ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ወደ ማኅበረሰብ ግጭት በመሸጋገሩ ባይካዎ እና አጋም ውሃ ቀበሌዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች ተፈናቅለው የአገው ተወላጆች በደለጎ ከተማ እና የአማራ ተወላጆች ፋርሽ ውሃ ከተማ ተጠልለው ይገኛሉ።
- የመዘዋወር ነጻነትና ትራንስፖርት ላይ የተጣሉ ሕገወጥ ገደቦች
- በአማራ ክልል፣ ከሰኔ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት መንገዶች ተዘግተው ቆይተው ከሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለትራንስፖርት ክፍት ተደርገው ነበር። ሆኖም እንደገና ከነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በዚሁ የ“ፋኖ” ቡድን በተላለፈ ጥሪ በጎጃም አካባቢ ያሉ መስመሮች በሙሉ ዝግ በመሆናቸው ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ታግደው ቆይተው ከ10 ቀናት በኋላ ከነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከታጠቀው ቡድን በተሰጠ መግለጫ መንገዶች ክፍት ሆነው እንቅስቃሴ ጀምሯል። በዚሁ ጥሪ መሠረት የሰባታሚት መስመርን ጨምሮ በባሕር ዳር ከተማ በከፊል መስመሮች ዝግ ሆነው ሰንብተዋል። በተጨማሪ ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ጀምሮ በማኅበራዊ ሚዲያ በተላለፈ ጥሪ ባሕር ዳር ከተማ ሙሉ በሙሉ ዝግ ሆኖ ቆይቶ ከነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በተወሰነ ደረጃ እንቅስቃሴ ጀምሯል። በተመሳሳይ በሸዋ፣ በወሎ እና በጎንደር የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት ባስተላለፉት ጥሪ ከነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በሸዋ፣ በወሎ እና በጎንደር ከከተሞች ውጭ ያሉ አብዛኞቹ መስመሮች ለተሽከርካሪዎች ዝግ ሆነው ቆይተው ከነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ተመልሰው ተከፍተዋል። በእነዚህ የእንቅስቃሴ ገደቦች ምክንያት ሰዎች ወደ ሕክምና መሄድ፣ ከቦታ ቦታ በነጻነት ተንቀሳቅሰው ምርታቸውን መሸጥ ወይም መሸመት ባለመቻላቸው ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል።
- በሌላ በኩል በጋምቤላ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ሲከሰት በነበረው የማኅበረሰብ ግጭት ምክንያት ወደ ኑዌር ብሔረሰብ ዞን ከተሞች የሚደረግ የሕዝብ መጓጓዣ/የትራንስፖርት አገልግሎት በሰኔ እና ከፊል ሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም. በመቋረጡ ነዋሪዎች ለከፋ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ተዳርገው የቆዩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት በመፈጠሩ ወደዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የሚደረገው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩን ኢሰመኮ ለማወቅ ችሏል።
- ምክረ ሐሳቦች
- ኢሰመኮ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸምና በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ከቀጠሉ የትጥቅ ግጭቶች ጋር በተያያዘ ይፋ ባደረጋቸው መግለጫዎችና የክትትል ሪፖርቶች የተካተቱና በከፊል ወይም በሙሉ ተፈጻሚ ያልሆኑ ምክረ ሐሳቦች እንዲፈጸሙ በድጋሚ እያሳሰበ በተለይም፦
- በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በቁርጠኝነት እንዲሠሩ፤ በማናቸውም የግጭት ሂደት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰትን ከመፈጸም እንዲቆጠቡ፤ በግጭቱ የሚፈጸሙ ጥሰቶችን በይፋ እንዲያወግዙ እና ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ፤ እንዲሁም በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ሰብአዊ መብቶችን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ፤ በሲቪል ሰዎች ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠቡ፤
- በአማራ ክልል በቀጠለው የትጥቅ ግጭት ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች የመዘዋወር ነጻነትና መጓጓዣ ላይ የሚያደርጉትን ተገቢ ያልሆኑ ገደቦችን ጨምሮ ኅብረተሰቡን ከሚያማርሩ እና ነጻነትን ከሚገድቡ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ፤
- መንግሥት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በመካሄድ ላይ በሚገኙት የትጥቅ ግጭቶች፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰት የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ ኃላፊዎችን እና አባላትን እንዲሁም የታጣቂ ቡድኖች አባላት ተጠያቂ ለማድረግ ተአማኒ እና የሰብአዊ መብቶች ደረጃን የሚያሟላ የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት እንዲጀመር፤ እንዲሁም በግጭቶቹ በሰው ሕይወት፣ በአካል፣ በሥነ-ልቦና እና በንብረት ላይ ያደረሱትን ጉዳት በማጣራት ተጎጂዎች እንዲካሱ እና መልሰው እንዲቋቋሙ እንዲያደርግ፤
- ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም እንዲሁም “ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ” በሚል ከተያዙት በርካታ ታሳሪዎች ውስጥ አብዛኞቹ ቢለቀቁም አሁንም በርካቶች መደበኛው የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ከሚፈቅደው ሂደት ውጪ በሕገወጥ እና በዘፈቀደ እስር ላይ ይገኛሉ። በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ለተራዘመ ቅድመ ክስ እስር መዳረግ የሰብአዊ መብቶች መርሖችን የሚጥስ በመሆኑ ተአማኒ ክስ ያልቀረበባቸው ታሳሪዎች እንዲሁም በማስገደድ የተሰወሩና ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የታሰሩ ሰዎች ሁሉ በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ ወይም ጉዳያቸው በመደበኛው የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት እንዲታይ፣ የመንግሥት የጸጥታና የአስተዳደር አካላት በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ግለሰቦችን በመደበኛ ማቆያዎች ብቻ እንዲይዙና የተያዙ ሰዎች ያሉበት ቦታና ሁኔታ ለቤተሰቦቻቸው እንዲገለጽ፤
- መንግሥት በጸጥታ አካላት አባላት፣ በታጠቁ ቡድኖች እና በ3ኛ ወገኖች የሚፈጸሙ እገታዎችን ለመከላከል እንዲሁም የአጥፊዎችን ተጠያቂነት እና የተጎጂዎችን ፍትሕ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ ውጤታማ እርምጃዎችን እንዲወስድ፤
- የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋምቤላ ቅርንጫፍ፣ የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ፍትሕ ቢሮና ጠቅላይ ፍርድ ቤት በማረሚያ ቤት ውስጥ ፍትሕ ሳያገኙ ለረጅም ጊዜያት የቆዩ/የሚቆዩ የጊዜ ቀጠሮ እስረኞች እና ተከሳሾች በተገቢው አጭር ጊዜ ውስጥ ፍትሕ እንዲያገኙ እንዲያደርጉ፤
- በጋምቤላ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የታየውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት ከሕዝቡ እና ሌሎች አካላት ጋር የሚያደርጋቸውን ውይይቶች አጠናክሮ እንዲቀጥል፤ እንዲሁም
- በተለያዩ ቦታዎች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች በቂ የሆነ እና አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲቀርብ፣ ሁሉም ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻች እንዲሁም ለመፈናቀል ምክንያት የሆነው የጸጥታ ሥጋት ሰላማዊና ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ጥሪ ያቀርባል።