የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ሸገር ሲቲ እና ሃዋሳ ከተሞች በሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ፋብሪካዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሴቶችን መብቶች አያያዝ በተመለከተ ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። ውይይቱ ኢሰመኮ በኅዳር ወር 2017 ዓ.ም. በአዳማ እና ሃዋሳ ከተሞች በሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥር ባሉ 5 ፋብሪካዎች ባከናወነው ሁለተኛ ዙር የምክረ ሐሳቦች አተገባበር ክትትል እንዲሁም በታኅሣሥ ወር 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሥር እና በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ በሚገኙ 8 ፋብሪካዎች ባደረገው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ግኝቶች ላይ ያተኮረ ነው።
በውይይቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኦሮሚያ እና የሲዳማ ክልሎች ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች፣ የጤና እና የኢንቨስትመንት ቢሮዎች፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በአዳማ እና ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተደረገው ሁለተኛ ዙር የምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ክትትል ሠራተኞች የማኅበራዊ ዋስትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጋቸው፤ የምክረ ሐሳብ አፈጻጸም ክትትል በተደረገባቸው ሁሉም ፋብሪካዎች የሠራተኞች ማኅበራት መደራጀታቸው፤ ከወሊድ በኋላ አብዛኞቹ ሴቶች ወደ ሥራ እንዲመለሱ መደረጋቸው፤ ሴት ሠራተኞች ከወሲባዊና ሥነ ተዋልዶ ጤና እንዲሁም ከሕይወት ክህሎት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን እንዲያገኙ መደረጉ እና በተለይም በአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የአንድ ማእከል አገልግሎት የቢሮ ግንባታ መጀመሩ በምክረ ሐሳብ አፈጻጸም ክትትሉ የተለዩ አበረታች እርምጃዎች መሆናቸው በውይይቱ ተገልጿል። በሌላ በኩል በሴት ሠራተኞች ላይ የጤና ጉዳት የሚያስከትሉ ሥራዎችን ለመለየት የሚያስችሉ አሠራሮች አለመዘርጋታቸው እንዲሁም ለነፍሰ ጡሮችና እመጫቶች የሚደረገው ድጋፍ በቂ አለመሆኑ በውይይት መድረኩ በአሳሳቢነት ከቀረቡ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች መካከል ናቸው።

ኢሰመኮ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሥር እና በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ በሚገኙ 8 ፋብሪካዎች ባደረገው የሰብአዊ መብቶች ክትትል የተለዩ ግኝቶችም ለውይይት የቀረቡ ሲሆን፤ በሁሉም ፋብሪካዎች የአደጋ መከላከያ እና የጤና መጠበቂያ መሣሪያዎች እና ቁሳቁሶች በበቂ ሁኔታ አለመሟላታቸውና አጠቃቀማቸውን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ የሌላቸው ሠራተኞች መኖራቸው፤ ለነፍሰጡሮች እና እመጫቶች ጎጂ የሆኑ የሥራ መደቦች አለመለየታቸው፤ 4 ፋብሪካዎች የጸረ ጾታዊ ትንኮሳ ፖሊሲ (Anti-Sexual Harassment Policy) የሌላቸው መሆኑ እንዲሁም የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና መስጫ ማእከላት በወጥነት በሁሉም ፋብሪካዎች የተሟሉ አለመሆናቸው በአሳሳቢነት ከቀረቡ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች መካከል ናቸው።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በተከናወኑት ክትትሎች የተለዩት ግኝቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮችና ፋብሪካዎች ውስጥ የሚሠሩ ሴቶችን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ የሚያሳዩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የማሻሻያ እርምጃዎችን ለመውሰድ መነሻ እንደሚሆኗቸው ገልጸዋል። በተለይም የክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎችን እንዲሠሩ ሥልጣን በተሰጣቸው መንግሥታዊ ተቋማት ዘንድ የባለቤትነት ስሜት አለመኖር፣ የውጭ ሀገር ዜጋ የሆኑ የድርጅት ባለቤቶች ከፌዴራል ተቋማት ውጪ ያሉ ሌሎች ባለድርሻ አካላትን (local authorities) ሥልጣናቸውን አሳንሰው የማየት ችግር መኖሩን ገልጸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር እና በቅንጅት በመሥራት በሴት ሠራተኞች ላይ የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የሚቆሙበትን እና የአሠራር ችግሮች የሚፈቱበትን መንገድ መቀየስ እንዲሁም ተቀራርቦ በመነጋገር እና በመተማመን መፍትሔ ማበጀት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ “ሴት ሠራተኞች ሊከበሩላቸው የሚገቡ ሰብአዊ መብቶችን በተሟላ ሁኔታ ለማረጋገጥ መንግሥት ቀዳሚ ባለግዴታ በመሆኑ በዘርፉ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ የሚገባው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ፋብሪካዎችም ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው” ብለዋል። አክለውም በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በፋብሪካዎች የሴት ሠራተኞች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን ለማሻሻል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ እና በቅንጅት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።