የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ኮሚሽኑ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል  ከአስተዳደራዊ መዋቅር እና ከድንበር መካለል ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ወደ ግጭት እያመሩ ለብዙ ሰዎች ሞት፤ የአካል ጉዳት፤ መፈናቀልና ንብረት ውድመት እያስከተሉ በመሆናቸው ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈለግላቸው ጥሪ ማድረጉን አስታውሰው በክልሉ መንግሥት የሚደረጉ ጥረቶች አበረታች ቢሆኑም ከችግሩ ስፋትና ውስብስብነት አንጻር የፌዴራል መንግሥት እገዛና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እንዳሉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኮሚሽኑ ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ክልሉን በተመለከተ ያካተታቸው መረጃዎች እና ምክረ ሃሳቦች ይህንኑ ነጥብ የሚያጠናክሩ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ኮሚሽነሩ፣ “የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት በጋራ እና ተቀናጅቶ በመሥራት እና ነዋሪዎችን በማሳተፍ ለመዋቅር እና ለድንበር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፤ ጥያቄ አቅራቢዎችም ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ብቻ ማቅረብ አለባቸው” በማለት በድጋሚ ለሁሉም ወገኖች ጥሪ አስተላልፈዋል።

ኢሰመኮ በክልሉ የተፈጠሩ አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ከሁሉም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የክልል እና የፌዴራል መንግሥት አካላት ጋር የሚያደርገውን ምክክር እና ክትትል እንደሚያጠናክር ተገልጿል።