የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ለሚያልፉ ሰዎች የሚሰጠው ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ጥራት እና ተደራሽነት ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ ውይይት ሚያዝያ 17 እና 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል። በዝግጅቱ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሚኒስቴር እና የክልል መሥሪያ ቤቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ማእከላት፣ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበራት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ውይይቱ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ለሚያልፉ ሰዎች የሚሰጠውን ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ለማጠናከር ለሚቀረጸው ሀገራዊ የድርጊት መርኃ-ግብር የአገልግሎቱን ጥራትና ተደራሽነት፣ ደካማና ጠንካራ ጎኖች እንዲሁም ለወደፊት በተለያዩ ተቋማት መሠራት ያለባቸውን ሥራዎች ለመለየትና ለመተንተን የሚያስችል ግብአት ለመሰብሰብ እና ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ ያለመ ነው።

ለሁለት ቀናት በዘለቀው ዝግጅት በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ለሚያልፉ ሰዎች የሚሰጠውን ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ተደራሽነት እና ጥራት በተመለከተ ኢሰመኮ በሠራው ጥናት የተለዩ ግኝቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በተጨማሪም ነጻ የሕግ ድጋፍ መርኃ-ግብር ያላቸው የተለያዩ ተቋማት የአገልግሎታቸውን ተደራሽነት፣ ጥራት ደረጃ እና መልካም ተሞክሮ እንዲሁም የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶችና እነዚህን ሁኔታዎች ለማሻሻል በቀረቡ ምክረ-ሐሳቦች ላይ ጽሑፍ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በተመሳሳይ በሀገሪቱ ያለውን ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ላይ ለውጥ ለማምጣት፣ ነጻ የሕግ ድጋፍ አሰጣጥ ሥርዓትን ለማስተባበር፣ ሀብት ለማሰባሰብ እና የአገልግሎቱን ዘላቂነት ለማረጋገጥ መሠራት ያለባቸውን ተግባራትና እነዚህን ለመፈጸም ኃላፊነት ሊወስዱ የሚገባቸውን ተቋማት፤ ተግባራቱ የሚፈጸሙበትን የጊዜ ሰሌዳ የሚለይ የድርጊት መርሐ-ግብር በቡድን ውይይት ተጠናቅሯል።

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር ዶ/ር ሚዛኔ አባተ የውይይት መድረኩ መክፈቻ ላይ፣ ነጻ የሕግ ድጋፍ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች እና በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ላይ የተደነገገውን ፍትሕ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። አክለውም በተለይ እ.ኤ.አ. ከ2009 እስከ 2019 የነጻ የሕግ ድጋፍ በተለያዩ ተቋማት እንዲቀጥል ኢሰመኮ የነበረውን አስተዋጽዖ ያስታወሱ ሲሆን አገልግሎቱ በአብዛኛው በፕሮጀክትና በለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ ላይ የተመረኮዘ መሆኑን፣ በክልሎች እና በፌዴራል ደረጃ በሚሰጡት አገልግሎቶች መካከል ልዩነቶች መኖራቸውን፣ በተለይ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ያለው አገልግሎት ውስን መሆኑን እንዲሁም ሁሉን አቀፍና ለሁሉም ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጋላጭ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ አለመሆኑን እንደክፍተት ጠቁመዋል። ከፍተኛ ዳይሬክተሩ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቱ በተደራጀና ውጤታማ በሆነ መልኩ በዘላቂነት እንዲቀጥል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ባጠቃላይ በሀገሪቱ ያለው ነጻ የሕግ አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ላይ ውይይት መጀመሩና ይህንን ለማሻሻል ኮሚሽኑ ተነሳሽነት መውሰዱ አበረታች መሆኑን ጠቁመው በተዘጋጀው የድርጊት መርሐ-ግብር መሠረት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።