የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ
ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተሻሻለው የማቋቋሚያ አዋጁ አንቀጽ 6 መሠረት በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል የማድረግ ሥልጣን እና ኃላፊነት ተሰጥቶታል። በዚህም መሠረት ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚገኙ ስድስት ዞኖች (ጋሞ፣ ወላይታ፣ ጎፋ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ እና ደቡብ ኦሞ) እንዲሁም አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ አማሮ፣ ባስኬቶ፣ ዲራሼ እና አሌ) በሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ የሰብአዊ መብቶችን ሁኔታ በሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የሚከታተል የባለሞያዎች ቡድን ወደ ስፍራው አሰማርቷል።

ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ለመተባበር እና ኃላፊነቱን ለመወጣት ከቦርዱ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙ ይታወሳል። የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ቡድኖች በሚሰማሩባቸው አካባቢዎች በሕዝበ ውሳኔ የድምፅ መስጫ ዕለት እና ከዚያ በኋላ ባሉት ቀናት በሕዝበ ውሳኔ ጣቢያዎች በመገኘት ምልከታ ያደርጋሉ፤ ድምፅ የሚሰጡ ሰዎችን፣ የሕዝበ ውሳኔ አስተባባሪዎችን፣ የጸጥታ አካላትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ታዛቢዎችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ሚና በመመልከት ክትትል በሚያደርጉባቸው የሰብአዊ መብቶች ላይ መረጃዎችን ያሰባስባሉ።

ማንኛውም ሰው እና ተቋማት በሙሉ ኮሚሽኑ ላሰማራቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ቡድን አባላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀርባል፡፡ ኮሚሽኑ ከሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ጋር ተያይዞ ሰዎች ለሚገጥሟቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በነጻ የስልክ መስመር 7307 ላይ በመደወልም መረጃ እና ጥቆማዎችን ማድረስ እንደሚችሉ መግለጹ ይታወቃል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፣ ሕዝበ ውሳኔ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚስተናገዱበት እና ዜጎች በሕዝባዊ ጉዳዮች የመሳተፍ መብታቸውን የሚተገብሩበት አንደኛው ሂደት መሆኑን አስታውሰዋል። አክለውም “ኮሚሽኑ በሀገራዊው ምርጫ ባደረገው ክትትል ግኝቶች መሠረት ሰዎች የፈለጉትን የፖለቲካ አመለካከት በነጻነት የመያዝ እና የመግለጽ እንዲሁም ሚስጥራዊነቱ በተጠበቀ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት የመምረጥ መብቶቻቸውን እንዲተገብሩ ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ፤ ዜጎች  ያለምንም መድሎ፣ ጫና እና ጣልቃ ገብነቶች በነጻነት ድምፅ መስጠት እንዲችሉ ሁሉም አካላት ግዴታቸውን እንዲወጡ” ጥሪ አቅርበዋል፡፡