የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፉት 6 ወራት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኙ ወረዳዎች ፖሊስ ጣቢዎች የነበረውን የተጠርጣሪ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ላይ ባደረገው ክትትል የተገኙ ውጤቶችና ምክረ ሃሳቦች አፈጻጸም ዙሪያ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ኃላፊዎች፣ መምሪያና ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤቶች አዛዦች እና ምርመራ ክፍል ኃላፊዎች ጋር ሰኔ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በሆሞሻ ከተማ ውይይት አድርጓል።

በውይይት መድረኩ የተደረገ ገለጻ የክትትል ውጤቱ የተጠርጣሪ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ያመላከተ ሲሆን፣ ምክረ ሃሳቦችን ከመፈጸም አኳያ መሻሻሎች ቢኖሩም በተወሰኑ የፖሊስ አመራሮች በኩል ውስንነቶች መኖራቸው ተገልጿል።

የውይይቱ አካል የነበሩት የክልሉ የተለያዩ የፍትሕ ተቋማት ተወካዮች በበኩላቸው ሰብአዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበሩ ሥራ በዋነኝነት የመንግሥት ኃላፊነት ቢሆንም ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ብለዋል። ተሳታፊዎቹ አክለውም በክትትሉ ወቅት የተስተዋሉ ከሕግ አግባብ ውጪ የሚፈጸሙ እስሮች እንዲቆሙ፣ የእስረኞች አካላዊ ደኅንነት መብታቸው እንዲጠበቅ፣ ተጠርጣሪዎች ከ48 ሰዓት በላይ ጣቢያዎች ውስጥ እንዳይቆዩ እና ሌሎች በአያያዝ ዙሪያ የታዩት ክፍተቶችን በመጪው ዓመት ለመቅረፍና ከኢሰመኮ ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

በየወረዳዎቹ በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች የተደረጉ የክትትል ሥራዎች ግኝቶችና ምክረ ሃሳቦችን ያቀረቡት የኢሰመኮ አሶሳ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጉርሜሳ በፉጣ፣ “በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ሰዎች ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የመሆናቸው እድል በጣም ሰፊ በመሆኑ የፍትሕ አካላቱ የተያዙ ሰዎችን መብቶች ከማክበር፣ ከማስከበርና ከማስጠበቅ አኳያ የመጀመሪያው ባለግዴታዎች መሆናቸውን አውቀው፣ ለተጠርጣሪዎች መብቶች አጠባበቅ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። አክለውም ኢሰመኮ በበኩሉ የተስተዋሉ ጉድለቶችን ለመሙላት የክትትል ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ ተቋማቱን እንደሚደግፍ ተናግረዋል።

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ይህን መሰል ውይይቶች በየወቅቱ እንዲደረጉና ወደፊት በሚታዩ የአሠራር ክፈተቶች ላይ ወቅታዊ ማስተካከያዎችን ለመውሰድ ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደሆነ ተሳታፊዎች አስተያየት ሰጥተዋል።