የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተጠልለው ከቆዩ በኋላ በደቡባዊ እና ሰሜን ምዕራብ ዞኖች ወደሚገኙ የቀድሞ መኖሪያ አካባቢዎቻቸው እንዲመለሱ የተደረጉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በተመለከተ ከነሐሴ 19 እስከ ጷጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ክትትል በማከናወን ያዘጋጀውን ባለ 11 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል። ክትትሉ የተደረገው ኢሰመኮ ከዚህ ቀደም በክልሉ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በተመለከተ ክትትሎችን በማከናወን በተለያዩ ጊዜያት መግለጫዎችን እና ሪፖርቶችን ይፋ ሲያደርግ እንዲሁም ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ በሚያገኙበት ሁኔታ ላይ የሚያደርገውን ክትትልና ውትወታ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሲገልጽ በቆየው መሠረት ነው።
ክትትሉ የተከናወነው ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ሕጎች እና ሰነዶችን በተለይም ኢትዮጵያ ያጸደቀችውን የአፍሪካ ኅብረት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና ድጋፍ ስምምነትን (የካምፓላ ስምምነት) እንዲሁም የኢትዮጵያ የዘላቂ መፍትሔዎች ኢንሼቲቭ መርሖችን መሠረት በማድረግ ነው። መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ ከተመላሾች ጋር 11 የቡድን ውይይቶች፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር 28 ቃለ መጠይቆችና የተናጠል ውይይቶች፣ እንዲሁም ተመላሾች በሚገኙባቸው ጊዜያዊ ማቆያዎች የአካል ምልከታዎች የተደረጉ ሲሆን፤ የክትትሉን ቀዳሚ ግኝቶች መነሻ በማድረግ ኢሰመኮ ኅዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም. በመቐለ ከተማ ባዘጋጀው የባለድርሻ አካላት ምክክር መድረክ ተጨማሪ ግብአቶች ተሰብስበዋል።
ክትትሉ ቁልፍ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን የለየ ሲሆን፣ በደቡባዊ ዞን በተለይም ወደ ራያ አላማጣ ወረዳ እና አላማጣ ከተማ እንዲመለሱ የተደረጉ ተፈናቃዮች የደኅንነት ሥጋት ያለባቸው በመሆኑ ወደ ቤታቸው ተመልሰው ገብተው ለመኖር አለመቻላቸው፤ እንዲሁም በሰሜን ምዕራብ ዞን ወደ ጸለምት፣ ላዕላይ ጸለምት እና ማይፀብሪ ከተማ አካባቢዎች እንዲመለሱ የተደረጉ ተፈናቃዮች የደኅንነት ሥጋት ያለባቸው በመሆኑ ለዳግም መፈናቀል መዳረጋቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል። ክትትል በተደረገባቸው አካባቢዎች አብዛኛዎቹ ተመላሾች ወደ ሥራቸው ያልተመለሱ መሆኑ፣ በሌሎች ሥራዎች ተሰማርተው ኑሯቸውን ለመምራት የሚፈልጉ ተመላሾችም በጸጥታ ችግር ምክንያት በነጻነት ተንቀሳቅሰው ለመሥራት አለመቻላቸው፣ ምግብ እና ሌሎች መሠረታዊ አቅርቦቶችን በበቂ ሁኔታ የማያገኙ በመሆኑ ተመላሾች ለምግብ እጦት እና ተያያዥ ችግሮች መዳረጋቸው በሪፖርቱ ከተገለጹ ተጨማሪ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች መካከል ናቸው።
ተፈናቃዮች እንዲመለሱ በተደረጉባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የጤናና የትምህርት ተቋማት በጦርነት የወደሙ እና የተዘረፉ በመሆኑ እንዲሁም ከጦርነቱ በኋላ የሲቪል አስተዳደር መዋቅር ባለመዘርጋቱ ምክንያት ተመላሾች የቀበሌ መታወቂያን ጨምሮ አስፈላጊ አገልግሎቶችን ማግኘት የማይችሉ መሆናቸው ለዘርፈ ብዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳጋለጣቸው ሪፖርቱ ያመለክታል።
ኢሰመኮ የክትትሉን ግኝቶች መሠረት በማድረግ ምክረ ሐሳቦችን ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ያቀረበ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል፦ ተመላሾች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ደኅንነታቸው በተሟላ ሁኔታ በዘላቂነት ተጠብቆ የሚኖሩበትን ሁኔታ ዕውን ለማድረግ በተለይም በውይይት እና ዕርቅ ሰላምን የማረጋገጥ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው፤ ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት መልሶ በማቋቋም እንዲሁም አስፈላጊ ግብዓቶችን እና የሰው ኃይል በማሟላት የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች የማኅበራዊ አገልግሎት ተቋማት በአፋጣኝ የተሟላ አገልግሎት እንዲጀምሩ እንዲደረግ፤ ተመላሾች ትተዋቸው የሄዷቸውን ቤት እና ሌሎች ንብረቶች መልሰው የሚያገኙበትን እንዲሁም ለሕይወታቸው የሕግና ፍትሕ ዋስትና የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሲቪል አስተዳደር እንዲዘረጋ እና የፍትሕ ተቋማት አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ እንዲደረግ የሚሉ ይገኙበታል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ተመላሾች ደኅንነታቸውና ክብራቸው ተጠብቆ ወደ ቀድሞ ኑሯቸው ተመልሰው መኖር የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር እና ይህ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እስኪሆን ሁሉም ባለድርሻዎች የተመላሾችን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ለማሻሻል በቅንጅትና በትብብር እንዲሠሩ በተለይም አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ችግር በአፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ እንዲደረግ አሳስበዋል። በቀጣይ የሚከናወኑ ተፈናቃዮችን ወደቀድሞ ቀያቸው የመመለስ ተግባራት የሰብአዊ መብቶችን መስፈርቶች መሠረት ያደረጉ መሆናቸው ሊረጋገጥ እንደሚገባ አስታውሰው፣ ኢሰመኮ በጉዳዩ ላይ የሚያደርገውን ክትትል እና ውትወታ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።