የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ እና ውጪ በሚገኙ እና የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መሪዎች መሆናቸውን በሚገልጹ አካላት መካከል ከተከሰተው አለመግባባት ጋር ተያይዞ በክልሉ ለወራት የዘለቀውና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አሳሳቢነቱ እየጨመረ የመጣው ውጥረት በክልሉ አጠቃላይ ሰላም እና የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ ያለውን አንድምታ እየተከታተለ ይገኛል።

በተለይም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንት መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. በከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች ላይ ጊዜያዊ እገዳ ማስተላለፋቸውን እንዲሁም የህወሓት ተወካይ መሆናቸውን የሚገልጹት አካላት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የጊዜያዊ አስተዳደሩን የመንግሥት ተቋማት ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ተከትሎ ከክልሉ ነዋሪዎች ዕለታዊ እንቅስቃሴ ባሻገር በሰዎች ሰብአዊ መብቶች ላይ አደጋ እና ሥጋት ፈጥረዋል። ለምሳሌ ከመቐለ ከተማ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አዲ ጉዶም ከተማ መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም. የከተማዋን አስተዳደር ከመቆጣጠር ጋር በተያያዘ በተነሳ ግርግርና ሁከት 4 ሰዎች አካላዊ ጉዳት ስለመድረሱ እንዲሁም ከንቲባውን ጨምሮ 4 ሰዎች ለእስራት ተዳርገው ከቀናት በኋላ የተለቀቁ ስለመሆኑ ኢሰመኮ በደረሰው መረጃ መሠረት ጉዳዩን በማጣራት ላይ ይገኛል። በተመሳሳይ በሳሃርቲ ሳምረ ወረዳ መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም. የወረዳው የጸጥታ ኃላፊና የትግራይ ነጻነት ፓርቲ አባል የሆኑ ሌላ ግለሰብ ታስረው ከቀናት በኋላ ሊለቀቁ መቻላቸውን ኢሰመኮ ማረጋገጥ ችሏል። በተጨማሪም በመቐለና በአዲግራት ከተሞች የአስተዳዳሪዎች ለውጥ መካሄዱ ያለውን አለመግባባት በማባባስ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ሥጋት ጨምሮታል።

ይህ አለመግባባት እና ውጥረት በፕሪቶሪያ የተፈረመውን የዘላቂ ተኩስ አቁምና የሰላም ስምምነት ተከትሎ በክልሉ የሰፈነውን አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ወደ ኋላ ሊመልስ የሚችል እንዲሁም የፕሪቶሪያ ስምምነት በተሟላ መልኩ እንዳይፈጸም ተግዳሮት የሚፈጥር እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሥጋት የሚፈጥር ነው። በመሆኑም ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ችግሩን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ እንዲሁም የፖለቲካ ልዩነቶች በምክክርና በመግባባት ሕግን መሠረት በማድረግ እንዲፈቱ ኢሰመኮ ጥሪውን ያቀርባል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ፖለቲካዊ አለመግባባቶች በሰብአዊ መብቶች ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርሱ አፋጣኝ ሰላማዊ መፍትሔዎችን መውሰድ የሚያስፈልግ መሆኑን አሳስበው ኢሰመኮ ከመደበኛው የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራው ጎን ለጎን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማነጋገር እና ምክረ ሐሳቦችን በመስጠት የተፈጠረው ችግር በውይይት እንዲፈታ ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል።