የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በአዲስ አበባ ከተማ የሚከበሩ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት እንዲሁም በመዲናዋ የሚደረጉ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ጉባኤዎች እና ሌሎች ተመሳሳይ ኹነቶች ጋር በተያያዘ በርካታ በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከጎዳና ላይ እንዲነሱ በማድረግ ለተለያየ የጊዜ መጠን በአንድ ማቆያ ስፍራ እንዲቆዩ ስለሚደረጉበት ሁኔታና ስለሰብአዊ መብቶች አያያዝ በተለያየ ጊዜ እና በተለይም ከጥር 9 እስከ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ክትትል አከናውኗል፡፡

የክትትሉ ዐላማ የድርጊቱን አፈጻጸም ለማጣራትና በሕፃናቱ ላይ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን እና አያያዝን ለመለየት፣ በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት የሚነሱበትን አሠራር እና ሂደት ከሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎች እና መርሆች አንጻር ለመፈተሽ እና ተገቢ ምክረ-ሐሳቦችን ለማቅረብ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ክትትሉ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትን፣ ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸውን የዓለም አቀፍ የሕፃናት መብቶች ስምምነት እና የአፍሪካ ሕፃናት መብቶች እና ደኅንነት ቻርተርን እንዲሁም የሕፃናት መብቶችን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ መርሆችን መሠረት በማድረግ ተከናውኗል።

ክትትሉ መነሻ ያደረገው ለኮሚሽኑ የቀረቡ ልዩ ልዩ አቤቱታዎችን እና በኮሚሽኑ የተከናወኑ የክትትል ምልከታዎችን ሲሆን፤ በቃለ-መጠይቅ፣ ከሠነዶች እና ከመስክ ምልከታ መረጃ እና ማስረጃዎችን አሰባስቧል፡፡ በዚሁ መሠረት ከጎዳና ላይ ተነስተው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የተሐድሶ  ማእከል ተይዘው ይገኙ የነበሩ ዕድሜያቸው ከ8-16 ዓመት የሆኑ ሕፃናት ጋር በተደረጉ 10 ቃለ-መጠይቆች፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የከተማ መስተዳድር ቢሮዎች እና የተሐድሶ  ማእከል ሠራተኞችና ኃላፊዎች ጋር እንዲሁም ከጎዳና ላይ የተነሱ ሕፃናትን የሚቀበሉ የሲቪል ማኅበራት ጋር በተደረጉ 15 ቃለ መጠይቆች፣ ሕፃናት ከጎዳና ላይ ተነስተው በተያዙበት የተሐድሶ  ማእከል በተደረገ የመስክ ምልከታ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሠነዶችን መሠረት በማድረግ ለክትትሉ አስፈላጊ የሆነ መረጃ እና ማስረጃ ተጠናቅሯል፡፡

ይህን ጉዳይ የሚመለከተው የከተማ መስተዳድሩ መመሪያ ሕፃናትን ጨምሮ በጎዳና ላይ ያሉ ሰዎች በፈቃደኝነት ብቻ ከጎዳና ላይ ተነስተው የተሟሉ አገልግሎቶች ወደሚያገኙበት ማእከል ሊወሰዱ እንደሚችሉ ቢያስቀምጥም፤ የከተማ መስተዳድሩና የጸጥታ አባላቶቹ በጎዳና ላይ የሚገኙ ሕፃናትን በኃይል፣ በዘፈቀደና ሕጋዊ ባልሆነ አሠራር በአፈሳ መልክ በማንሳት አብዛኛዎቹ ሕፃናት ለተለያየ ጊዜ መጠን በማቆያ ጣቢያ እንዲቆዩ እየተደረገ የሚለቀቁ መሆኑን፣ በማቆያ ጣቢያውም የተሟላ አገልግሎት አለመኖሩን ኮሚሽኑ በክትትሉ ተመልክቷል፡፡

የኢሰመኮ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ በጎዳና ላይ ላሉ ሕፃናት ዘላቂ መፍትሔ የመቀየስ አስፈላጊነትን እና አስቸኳይነቱን አበክረው ገልጸው፤ “ሕፃናትን ከጎዳና ላይ ማንሳትና ተገቢውን አገልግሎቶች መስጠት በፈቃደኝነትና አስፈላጊ ሁኔታዎችን ሁሉ በማመቻቸት የሚተገበር እንጂ፤ በኃይል፣ በዘፈቀደ እና ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ሊፈጸም ስለማይገባ ይህን ዓይነት የኃይል፣ የዘፈቀደና ሕገ-ወጥ አሠራር ሊወገድ ይገባል” ብለዋል፡፡

ስለ ኮሚሽኑ ክትትል፣ ግኝቶችና ምክረ-ሐሳቦች ዝርዝሩን ከዚህ በታች ይመልከቱ፡፡

ስለ ጎዳና ሕፃናት አጭር ገለጻ እና የሕግ ማዕቀፍ

  1. ለዚህ ክትትል ዐላማ በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት ማለት የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መብቶች ኮሚቴ (የሕፃናት መብቶች ኮሚቴ/ኮሚቴው) በአጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 21 የሰጠው ትርጓሜ ታሳቢ የተደረገ ሲሆን፤ በዚህ መሠረት በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት ብቻቸውንም ሆነ ከእኩዮቻቸው ወይም ከቤተሰብ ጋር ለመኖር እና/ወይም ለመሥራት በጎዳና ላይ ጥገኛ የሆኑ ሕፃናት ልጆች እንዲሁም ከሕዝባዊ ስፍራዎች ጋር ጠንካራ ትስስር የፈጠሩ እና ጎዳና በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው እና በማንነታቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳረፈባቸውን ሰፊ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የሚያካትት ነው፡፡[1]

2. እንደ ሀገራት ነባራዊ ሁኔታ ሕፃናትን ወደ ጎዳና እንዲወጡ የሚያደርጓቸው የተለያዩ ዓይነት ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን በኢትዮጵያ ድህነት፣ ድርቅ፣ ጦርነት እና ግጭት፣ የሕዝብ ፍልሰት፣ በወላጆች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች እና የወላጅ ወይም የአሳዳጊ ሞት፣ የሕፃናት በተለያዩ ሱሶች መያዝ በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ የቤት ውስጥ ጥቃቶች እና መድልዎ ከዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ ናቸው።[2]

3. በኢትዮጵያ ውስጥ በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናትን መጠን እና አይነት በተመለከተ የተደራጀ፣ የተሰባጠረ እና ወቅታዊ አሃዛዊ መረጃ ማግኘት ባይቻልም አንዳድ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት ወደ 150,000 የሚሆኑ ሕፃናት በጎዳና እንደሚገኙ እና ወደ 60,000 የሚሆኑት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ እንደሆነ ይገመታል፡፡

4. የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በ2018 ዓ.ም. ያደረገው ጥናት በጎዳና ላይ የሚኖሩ  ሕፃናትን፣ ሕፃናትን ይዘው በጎዳና ላይ የወጡ እናቶችን፣ ወጣቶችን እና አረጋውያንን እንደሚያካትት ይገልጻል፡፡ ጥናቱ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ 10 ክፍለ ከተሞችን የሸፈነ ሲሆን በወቅቱ በአጠቃላይ ጎዳና ላይ ከሚኖሩ ሰዎች መካከል ሕፃናት 18%፣ አረጋውያን 17%፣ ቤተሰብ የሚረዳቸው እና ከቤተሰብ እርዳታ ውጪ በልመና የሚተዳደሩ 15% እና አካል ጉዳተኞ 10% እንደነበሩ ያሳያል፡፡

5. በጎዳና ላይ የሚኖሩ ሕፃናት ከፊሎቹ በልመና የሚተዳደሩ ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተሠማርተው በአብዛኛው አነስተኛ ገቢ በሚያስገኙ እንደ ጫማ መጥረግ እና የጎዳና ላይ ሽያጭ በመሥራት ራሳቸውን ለማስተዳደር ይጥራሉ፡፡

6. የዓለም አቀፉ የሕፃናት መብቶች ስምምነት አንቀጽ 37 ማንኛውም ሕፃን በሕገ-ወጥ ወይም በዘፈቀደ አሠራር ነጻነቱን እንደማይገፈፍ፣ ማንኛውም ሕፃን የሚያዘው፣ በቁጥጥር ሥር የሚውለው እና የሚታሰረው በሕግ መሠረት ብቻ እና ይህም እንደ መጨረሻ አማራጭ እና ለአጭር ጊዜ ብቻ ተፈጻሚ መሆን እንዳለበት፣ ነጻነቱን የተነፈገ ሕፃን ደግሞ ዕድሜው የሚጠይቃቸውን ፍላጎቶች ግምት ውስጥ በማስገባት በክብርና በርህራሄ እንዲሁም ለአካለ መጠን ከደረሱ ሰዎች ተለይቶ መያዝ እንዳለበት እና ፍርድ ቤት ወይም ሌላ ሥልጣን ባለው ነጻና ገለልተኛ በሆነ ባለሥልጣን ፊት ቀርቦ ነጻነቱን የተነፈገበትን ጉዳይ ሕጋዊነት የመጠየቅና በጉዳዩ ላይም ፈጣን ውሳኔ የማግኘት መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡

7. በተጨማሪም የሕፃናት መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 21 ላይም በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናትን ኃይል በተሞላበት ሁኔታ ማፈስ ወይም ከጎዳና እንዲነሱ ማስገደድን የከለከለ ሲሆን ፖለቲካዊ፣ ሕዝባዊ፣ ወይም ስፖርታዊ ክንዋኔዎች ቢኖሩም እንኳን ሀገራት ክልከላውን መጣስ እንደሌለባቸውም አስቀምጧል፡፡ እንዲሁም መንግሥት በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናትን ወይም ቤተሰቦቻቸውን ማፈስ ወይም በዘፈቀደ ማንሳት የሚፈቅዱ ወይም የሚደግፉ ማንኛውም ሕጎችን እና ፖሊሲዎችን ማስወገድ እንዳለበት ተቀምጧል፡፡ ሕፃናቱን ያለፈቃዳቸው በግብታዊነት ከጎዳና ላይ የማፈስ ወይም የማንሳት ተግባርን በአፋጣኝ የማስቆም/የማስወገድ ግዴታም በመንግሥት ላይ ተጥሎበታል፡፡ በመሆኑም ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በተገናኘ የሚደረጉ ምንም ዓይነት የቁጥጥር እርምጃዎች በሕግ የተደገፉ፤ በግለሰብ ደረጃ የሚፈጸሙ፤ ተመጣጣኝ እና እንደመጨረሻ አማራጭ ብቻ የሚወሰዱ መሆን አለባቸው፡፡ እነዚህ እርምጃዎች ሕፃናትን በግለሰብ ደረጃ ሳይለዩ በጅምላ የሚያሳፍሱ ወይም የሚያነሱ ሊሆኑ አይገባም። እንዲሁም እዚህ ሥራ ላይ የሚሰማሩ የፖሊስ አባላት እና የጸጥታ አካላት በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት መብቶችን በማይነካ መልኩ ግዴታቸውን መወጣት እና ተገቢ እርምጃዎችን ማስፈጸም እንዲችሉ አስፈላጊው ስልጠና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡[3]

8. የሕፃናት መብቶች ኮሚቴ በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የሚያልፉ ሕፃናትን 
አስመልክቶ በሰጠው አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 24 ክፍል 3 (6) ሥር የሕፃናትን ነጻነት ስለመንፈግ በሰጠው ትርጉም ሕፃናትን በማናቸውም ዓይነት የግል፣ የሕዝብ ወይም የመንግሥት ተቋማት ስፍራዎች ይዞ በማቆየት እንደ ፍላጎታቸው እንዳይወጡ እና እንዳይገቡ በማድረግ የመንቀሳቀስ መብታቸውን መገደብ የነጻነት መብታቸውን መንፈግ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ አንጻር በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናትን በተለያዩ ምክንያቶች ከጎዳና ላይ ማንሳት፤ በአንድ የተለየ ቦታ ተይዘው እንዲቆዩ በማድረግ የመንቀሳቀስ መብታቸውን መገደብ ወይም ካሉበት እንዳይወጡ መከልከል የሕፃናቱን የነጻነት መብት መንፈግ ነው፡፡[4] በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት ከሌሎች ሕፃናት በተለየ ከሚኖሩበት ወይም ከሚውሉበት የጎዳና አካባቢ/ቦታ ጋር ልዩ ትስስር የሚኖራቸው በመሆኑ የእነዚህን ሕፃናት የነጻነት መብት መጣስ ሕፃናቱን ለተደራራቢ የመብት ጥስት ይዳርጋል፡፡ ይህም ማለት በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት ለመኖር እና ሥራዎችን ለማከናወን፣ ለመጫወት፣ ለማረፍ፣ ለመዝናናት፣ ከሌሎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ያሉበት የጎዳና ቦታ/አካባቢ ዋነኛ መናኸሪያቸው ስለሆነ የነጻነት መብታቸው መነፈግ ሌሎች መብቶቻቸውንም አብሮ ይጥሳል፡፡[5]

9. የሕፃናት መብቶች ኮሚቴ በአጠቃላይ ትንታኔው በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናትን በግዳጅ ማፈስ ወይም ከጎዳና ላይ በዘፈቀደ እንዲነሱ ማስገደድ ሊወገድ የሚገባው አሠራር ወይም ፖሊሲ ሲሆን ማናቸውም ዓይነት ፖለቲካዊ፣ ሕዝባዊ፣ ወይም ስፖርታዊ ክንዋኔዎች ቢኖሩም እንኳን ሀገራት ይህን ዓይነት ፖሊሲ ወይም አሠራር ተፈጻሚ ማድረግ እንደሌለባቸው በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ በተጨማሪም መንግሥት በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናትን ወይም ቤተሰቦቻቸውን ማፈስን ወይም በዘፈቀደ ማንሳትን የሚፈቅዱ ወይም የሚያመቻቹ ሕጎችን ፖሊሲዎችን እና ደንቦችን በሙሉ ማስወገድ እንዳለበት ያሳስባል፡፡ እንዲሁም ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በተገናኘ የሚደረጉ ምንም ዓይነት የቁጥጥር እርምጃዎች በሕግ የተደገፉ፤ በጅምላ ሳይሆን በግለሰቦች ደረጃ የሚፈጸሙ፤ ተመጣጣኝ እና እንደመጨረሻ አማራጭ ብቻ የሚወሰዱ መሆን እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡[6]

10. በተለይም መንግሥታት ወደ ጎዳና የሚወጡ ሕፃናት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን፣ በማኅበረሰቡ የሚደርስባቸውን አድልዎ እና መገለል እንዲሁም የሚፈጸምባቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በመገንዘብ በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት የሚደርስባቸውን ተደራራቢ የመብት ጥሰቶች በዘለቄታ ለማስቀረት በዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሕፃናት የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶችን እና መርሆችን መሠረት ያደረገ እና ሰብአዊ መብት ተኮር የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለባቸው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ ቁ. 16/12 እና የሕፃናት መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 21 አበክረው ያሳሰቡ ቢሆንም ይህን ጉዳይ የሚመለከት የሕፃናት መብቶች እና መርሆችን መሠረት ያደረገ ሁሉን-አቀፍ የረጅም ጊዜ ዕቅዶችና እና ስልቶች እስከ አሁን ድረስ በመንግሥት ተግባራዊ ያልተደረጉ ሲሆን ይህን እርምጃ መውሰድ አሁንም ከመንግሥት የሚጠበቅ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡

11. መንግሥት የሕፃናት መብት ተኮር የሆነ ሁሉን አቀፍ የረጅም ጊዜ ስልታዊ ዕቅድ በመንደፍ በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት መብቶች በተሻለ ሁኔታ እንዴት ማስከበር እንዳለበት ለመወሰን ሕፃናቱን የተመለከተ ሙሉ እና ወቅታዊ መረጃ በመሰብሰብ በአካባቢ፣ በጾታ፣ በአካል ጉዳት ዓይነት እና በዕድሜ አሰባጥሮ የማደራጀት፣ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን እና ፖሊሲዎችን መሠረት ያደረገ እና በጥናት ላይ የተመሠረተ ቅድመ-ትንታኔን ማካሄድ፣ በጎዳና ላይ ላሉ ሕፃናት ለሚቀየሰው መፍትሔ አስፈላጊውን የበጀት ድልድል ማድረግ ይኖርበታል።

12. እንዲሁም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ጎዳና ላይ ባሉ ሕፃናት ወይም በወላጆቻቸው ወይም በቤተሰባቸው ላይ አድልዎ የሚያደርጉ ሕጎችን በአፋጣኝ የማስወገድ ተግባራትን ሊያከናውን እንደሚገባ በሕፃናት መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ ላይ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም በኮሚቴው አስተያየትና ምክረ-ሐሳብ መሠረት ሕፃናትን እና ቤተሰቦቻቸውን ከጎዳና ላይ በዘፈቀደ እንዲነሱ ወይም እንዲታፈሱ የሚፈቅዱ ወይም የሚያመቻቹ ማናቸውንም የሕግ ድንጋጌዎችን መሰረዝ ወይም አሠራሮችን የማስቀረት፣ የሕፃናት መብቶችን መሠረት ያደረገ የሕፃናት ጥበቃ በተለይም በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናትን የሚመለከት ሕግ የማውጣት ወይም የማሻሻል እርምጃዎችን መንግሥት መውሰድ ይጠበቅበታል።[7]

13. በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት የራሳቸውን ሕይወት በሚመለከት በሚወሰዱ ውሳኔዎች እና ተገቢ ስልቶችን በመንደፍ እና በመተግበር ሂደቶች፣ እንዲሁም በሚካሄዱ ጥናቶች፣ በመረጃ አሰባሰብና ትንተና እንዲሳተፉ ማድረግ ሌላው የመንግሥት ቁልፍ ሚና እና ግዴታ ነው። በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናትን እንደጥፋተኛ፣ ችግረኛ ወይም ተጎጂ ከመፈረጅ በዘለለ የሰብአዊ መብቶች ባለቤቶች/ባለመብቶች መሆናቸውን ዕውቅና በመስጠት ማማከርና ለሚሰጡት ሐሳብ ዋጋ መስጠት፣ ከእነርሱ ጋር አብሮ መሥራት አስፈላጊ ነው።[8]

14. በአጠቃላይም በሕግ እና በፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ ሁለንተናዊ የሕፃናት ጥበቃ ሥርዓቶችን ማበጀት፣ ማጎልበት እና ማጠናከር መንግሥት ላይ ከተጣሉ ኃላፊነቶች መካከል ናቸው። እንዲሁም ሕፃናት ልጆች ወደ ጎዳና ሕይወት እንዳይወጡ ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ስልታዊ ዕቅዶችን በመቅረጽ ተግባራዊ እርምጃዎችን የመውሰድ በተለይም የዕርዳታ መዋቅሮችን በመዘርጋት፣ ጊዜያዊ የማረፊያ፣ የመንከባከቢያ እና የመኖሪያ ተቋማትን በመገንባት፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መልሶ ማገናኘት፣ የበጎ ፈቃደኛ አሳዳጊዎች (ጉዲፈቻ) ማመቻቸት ወይም ሌላ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ የእንክብካቤ እና ተዛማጅ አገልግሎቶችን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለሕፃናቱ ለመስጠት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸትም ከመንግሥት ይጠበቃል።

ክትትል ግኝቶች

15. ከነሐሴ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ ክትትል እስከ ተከናወነበት ጥር ወር 2015 ዓ.ም. ድረስ ብቻ በአዲስ አበባ ከተማ ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 14,000 ሰዎች ከጎዳና ላይ በኃይል በፖሊስ ተነስተዋል። በተለይም በ2015 ዓ.ም. በጥር ወር በተከበረው የጥምቀት በዐል ወቅት በግምት 1,000 ሕፃናትን ጨምሮ አጠቃላይ ቁጥራቸው ከ6,000 እስከ 7,000 የሚደርሱ ሰዎች በፖሊስ እና የጸጥታ ኃይሎች ከጎዳና ላይ ታፍሰው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የተሐድሶ ማእከል ውስጥ ለተለያየ ጊዜ መጠን ተይዘው መቆየታቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ የዚህ ዓይነቱ አፈሳ በተለይ በአደባባይ በሚከበሩ በዓላት ወቅት በተደጋጋሚ እንደሚፈጸምም ለማወቅ ተችሏል፡፡

16. በጥምቀት በዓል ምክንያት ከጎዳና ላይ ታፍሶ በተሐድሶ ማእከሉ ውስጥ ተይዞ የነበረ አንድ የ12 ዓመት ዕድሜ ያለው ሕፃን ለኢሰመኮ ሁኔታውን ሲገልጽ “በጎዳና ላይ መኖር ከጀመርኩ ብዙ ጊዜ የሆነኝ ሲሆን በተለያዩ ሱሶች እና በድህነት ምክንያት ወደ ጎዳና ለመውጣት ችያለሁ፤ የጥምቀት በዓል ከመከበሩ 2 ቀናት ቀደም ብሎ ከልደታ ሰፈር ፖሊስ ይዞ ወደ ማእከሉ ያመጣኝ ሲሆን ከጎዳና የምንነሳበትን ምክንያት የማይነግሩን ቢሆንም በዓላት በሚከበሩበት ጊዜ ከበዓሉ ቀን በፊት ሁልጊዜ ወደ ማእከሉ በመኪና ያመጡናል” ሲል ተናግሯል፡፡

17. በተመሳሳይም በዚሁ ዓመት በከተማዋ የተከበሩ እንደ መስቀል እና የኢሬቻ ክብረ በዓላትን እንዲሁም በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢ ያለውን ወቅታዊ የሰላም እና ደኅንነት ሥጋት ምክንያት በማድረግ ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ሕፃናት ከጎዳና ላይ ታፍሰው እንደነበር ለመረዳት ተችሏል፡፡

18. ኮሚሽኑ ለክትትል ሥራ በማእከሉ በተገኘበት ወቅት ዕድሜያቸው በግምት ከ4-18 ዓመት የሆኑ ሕፃናትን ጨምሮ በአንድ መኪና ብዛታቸው ከ70-100 የሚሆኑ ሰዎች በ5 መኪኖች ተጭነው ወደ ማእከሉ እየተፈተሹ ሲገቡ ለማየት ችሏል፡፡ ይህን ዓይነት አፈሳ በሚከናወንበት ወቅት በአማካኝ ከ500 እስከ 1,000 የሚደርሱ ሰዎች ከጎዳና ላይ እንደሚነሱና የከተማው መስተዳድር በክፍለ ከተማ ደረጃ ከፖሊስና የጸጥታ አባላት ጋር ተቀናጅተው የሚከናወን ተግባር መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል።

19. የተለያዩ ኹነቶችን እና በዓላትን ጠብቆ የሚደረገው ሕፃናትን ከጎዳና ላይ የማንሳት ተግባር እና አሠራር በሕግና በፓሊሲ ሰነዶች ላይ ያልሰፈረ እና አሠራሩ አስተዳደራዊ የሥልጣን እርከንን ተከትሎ ከበላይ ኃላፊዎች በስልክ ብቻ በሚተላለፍ ትእዛዝ የሚፈጸምና ይህም እንደ አሠራር የታወቀና የተለመደ መሆኑን ኮሚሽኑ ካነጋገራቸው የመረጃ ምንጮች ለማወቅ ተችሏል:: ሂደቱም በዋነኝነት የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር፣ የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮን የሚያሳትፍ እንደሆነም ጨምሮ ለመረዳት ተችሏል፡፡

20. ሕፃናቱ ከጎዳና ላይ ከመነሳታቸው በፊት ልየታ የማይደረግ በመሆኑ እና አብዛኛውን ጊዜ ልየታን፣ መረጃ መሰብሰብን፣ መመዝገብን እና የመሳሰሉት ሥራዎችን መንግሥት የሚያከናውነው አስቀድሞ ሳይሆን ማእከል ከገቡ በኋላ በመሆኑ ልዩ ፍላጎት እና ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው የአእምሮ ሕሙማን እና ሌሎች የጤና እክል ያለባቸው ሕፃናት ጭምር ከጎዳና ላይ ታፍሰው እንደሚነሱ እና ለተደራራቢ የመብቶች ጥሰት ተጋላጭ እንደሆኑ ኮሚሽኑ በክትትሉ ለመረዳት ችሏል፡፡

21. የአቃቂ ቃሊቲ የተሐድሶ ማእከልም በአንድ ጊዜ ለማስተናገድ ከሚችለው አቅም በላይ ሕፃናቱን ጨምሮ እጅግ በርካታ ሰዎች በጅምላ ወደ ማእከሉ እንዲገቡ የሚደረግ በመሆኑ በተለይ ለሕፃናት ምቹ እና የተሟላ አገልግሎት መስጠት አልቻለም፡፡ በተጨማሪም ጠዋት 12፡00 ሰዓት እና ማታ 12፡00 ሰዓት መጸዳጃ ቤት ለመጠቀም መውጣት ከሚፈቀደው ውጪ ሕፃናቱ ቀን ላይ ከክፍሎቻቸው መውጣት ስለማይፈቀድላቸው በክፍሎቻቸው ውስጥ በሚገኙ የፕላስቲክ እቃዎች ሽንት ለመሽናት እንደሚገደዱ፣ ለመጸዳዳት ወደ ውጪ ለመውጣት ሲሞክሩ ረብሻችኋል በሚል በማዕከሉ በሚገኙ ተቆጣጣሪዎች ድብደባ እንደሚፈጸምባቸው አስረድተዋል፡፡ ኢሰመኮም በምልከታው ወቅት በማእከሉ ውሰጥ የሕፃናቱ እንቅስቃሴ የተገደበ መሆኑን ተመልክቷል፡፡

22. በተጨማሪም ኮሚሽኑ በማእከሉ በተገኘበት ወቅት ወደ መጡበት ክልል የሚመለሱ ናቸው በሚል ተለይተው በጠባብ ክፍሎች ውስጥ ተጨናንቀው ከተቀመጡ 240 ሕፃናት በስተቀር ሌሎች ሕፃናት ለአካለ መጠን ከደረሱ ሰዎች ጋር በአንድ ላይ ተቀላቅለው እንደተያዙም ተመልክቷል፡፡ በማእከሉ ውስጥ ሴቶች ለብቻቸው የመኝታ ክፍል ያላቸው ቢሆንም ክፍሎቹ ቁልፍ የሌላቸውና በቀላሉ የሚከፈት በር ያላቸው በመሆኑ በተለይ ከጥቃት ተጋላጭነት አኳያ በሴት ሕፃናት ላይ ከፍ ያለ ሥጋት የሚያሳድር ነው፡፡

23. ሕፃናቱ በዚህ የማቆያ ማእከል (የአቃቂ ቃሊቲ የተሐድሶ ማእክል) በሚቆዩበትም ወቅትም ወደ ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ ወይም በማንኛውም ዓይነት የፍትሕ ሂደት ውስጥ እንደማያልፉ ለማወቅ ተችሏል። በሌላ መልኩ አቤቱታ የሚያቀርቡበትም ሆነ ለሚደርሱ በደሎች ምላሽ የሚያገኙበት አሠራርም ግልጽ አይደለም።

24. የአዲስ አበባ ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በፕሮጀክት (በልዩ ሁኔታ) እና በመደበኛ ሁኔታ ሕፃናትን ጨምሮ ከጎዳና ላይ የሚነሱ ሰዎችን የሚመለከት ራሱን የቻለ መመሪያ እና አሠራር እንዳለው እና ከጎዳና ላይ ሰዎችን በማንሳት ወደ ማእከል የማስገባት ሥራ በዕቅድ ተይዞ የሚከናወን ተግባር መሆኑንና፤ በዚህም መሠረት ከየክፍለ ከተማው በአጠቃላይ በዓመት ከ3,000 እስከ 4,000 ጎዳና ላይ ያሉ ሰዎችን በማንሳት አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ ተግባራዊ እንደሚደረግ የቢሮው ኃላፊዎች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡

25. ሕፃናትን ጨምሮ ከጎዳና ላይ ለሚነሱ ሌሎች ሰዎች ተፈጻሚ የሆነው ይህ የአሠራር መመሪያ ሕፃናቱ ከጎዳና በሚነሱበት ወቅት፣ ከተነሱ በኋላ እና በማቆያ (ማእከል) በሚቆዩበት ጊዜ መከናወን ስለሚገባቸው ተግባራት በዝርዝር ያስቀምጣል። ከነዚህ ዝርዝር ተግባሮች ውስጥም ሰዎች በጎዳና ላይ ባሉበት ወቅት ለምን እንደሚነሱ ግንዛቤ የመፍጠር እና የማሳመን ሥራ፣ ወደ ማእከል ከገቡ በኋላ በቆይታቸው ስለሚያገኙዋቸው አገልግሎቶች (የምግብ፣ አልባሳት፣ የጤና፣ የምክር፣ ስልጠና፣ እና የሥነ-ልቦና ድጋፍ)፣ እንዲሁም ከማእከሉ ከወጡ በኋላ ስለሚከናወነው ቤተሰብን የማፈላለግ እና መልሶ የማገናኘት፣ ጉዲፈቻ እና አሳዳጊዎችን የመፈለግ፣ የሥራ ዕድልና የትስስር ፈጠራ ወዘተ…) ጉዳዮችን የሚጨምር ሲሆን ይህም ሙሉ በሙሉ በፈቃደኝነት እና በማሳመን ላይ በመመሥረት ብቻ የሚከናወን ተግባር እንደሆነ ተመልክቷል።

26. የመረጃ አያያዝን በተመለከተም ሕፃናቱ በቅድሚያ እንዲቆዩ ወይም እንዲያድሩ የተደረገበት ቦታ ላይ ወይም ማእከል ከገቡ በኋላ የግል መረጃ የሚያዝ ቢሆንም አንድ ወጥ የሆነና የተሟላ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት እንደሌለም ኮሚሽኑ ተመልክቷል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃም የጎዳና ላይ ሕፃናትን በአካባቢ፣ በጾታ፣ በዕድሜ፣ በአካል ጉዳት ዓይነት ወዘተ ተሰባጥሮ እና ተደራጅቶ የተቀመጠ መረጃ የለም፤ በተጨማሪም ለችግሩ ዘላቂ የፖሊሲ እልባት ለመስጠት ቁልፍ የሆነው፣ ባለድርሻ አካላትን ሁሉ ያሳተፈ የተሟላ ጥናትና ትንተና ገና ወደፊት እንደሚሠራ የሚጠበቅ ነው፡፡

ምክረ-ሐሳቦች

27. በክትትሉ የተለዩትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ለማስተካከል እና በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናትን መብቶች ለመጠበቅ መንግሥት አግባብነት ያላቸውን የሕግ፣ የፖሊሲ፣ የተቋም እና የአሠራር እርምጃዎች በአፋጣኝ መውሰድ የሚጠበቅበት ሲሆን በተለይም የሚከተሉትን ምክረ-ሐሳቦች መተግበር አስፈላጊ ነው፤

  • በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናትን ከጎዳና ላይ ማንሳትና ተገቢ አገልግሎቶችን መስጠት ከዚህ በላይ በተገለጸው በከተማ መስተዳድሩ መመሪያ መሠረት በፈቃደኝነትና አስፈላጊ ሁኔታዎችን ሁሉ በማመቻቸት የሚተገበር እንጂ፤ በኃይል፣ በዘፈቀደ እና ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ሊፈጸም ስለማይገባ የከተማ መስተዳድሩ ይህን ዓይነት የኃይል፣ የዘፈቀደ ሕገ-ወጥ አሠራር በአፋጣኝ እንዲያስወግድ፣ ግልጽ የሆነ ክልከላ እንዲያስቀምጥ እንዲሁም ግድፈት በሚፈጽሙ አካላት ላይም አስፈላጊ የእርምት እርምጃዎችን እንዲወስድ፣
  • በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ሕፃናትን የመያዝ ወይም ነጻነታቸውን የመገደብ ተግባር ሙሉ በሙሉ ከሕፃናት መብቶች ስምምነት እና ከዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ የሕፃናትን መብቶች፣ ጥቅምና ደኅንነትን ባስጠበቀና በሕግ አግባብ ብቻ እንደመጨረሻ አማራጭ እና ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚፈጸም መሆኑን የከተማ መስተዳድሩ እንዲያረጋግጥና አስፈጻሚ አካላት በሙሉ ግዴታቸውን በዚሁ መሠረት እንዲወጡ እንዲያደርግ፤
  • የፌዴራል መንግሥትና የከተማ መስተዳድሮች በመቀናጀት ለችግሩ ዘላቂ የፖሊሲ መፍትሔ የሚቀየስበትን ተገቢውን ምክክር፣ የመረጃ ጥንቅር፣ ጥናትና ትንተና በማካሄድ፣ የጎዳና ሕፃናትን ጨምሮች በባለድርሻ አካላት ሙሉ ተሳትፎ ተገቢው መፍትሔ እንዲዘረጋ እና ተግባራዊ እንዲደረግ፣
  • የፌደራል የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት መብቶችን ለማስጠበቅና መብቶቻቸው መከበራቸውን ለማረጋገጥ ሁሉን አቀፍ የሆነ እና የሕፃናት መብቶች እና መርሆች ላይ የተመሠረተ ስልታዊ ዕቅድ በመንደፍ ለተግባራዊነቱም በዘርፉ የሰለጠኑ አስፈላጊ ባለሙያዎችን እና በጀት በመመደብ እንዲሁም ይህን የሚመለከት በቂ ሥልጣን እና ኃላፊነት ያለው ተቋማዊ መዋቅር እና አሠራር በመዘርጋት ተግባራዊ እንዲያደርግ፤
  • መንግሥት በመላው ሀገሪቱ በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናትን አጠቃላይ ሁኔታ እና አውድ የሚያሳይ ብሔራዊ መረጃ በመሰብሰብ እና በዕድሜ፣ በጾታ፣ በአካል ጉዳት ዓይነት እና በአካባቢ በማሰባጠር እና በማዋቀር ለሚመለከታቸው አካላት ምቹ በሆነ መንገድ ተደራሽ የሆነ መረጃ እንዲያደራጅ፡፡

[1] የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መብቶች ኮሚቴ እ.አ.አ. በ2017 በጎዳና ላይ ስላሉ ሕፃናት ሁኔታ ላይ የሰጠው አጠቃላይ ትንታኔ (አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 21) CRC/C/GC/21 አንቀጽ 4

[2] Consortium for Street Children, The Facts about Street Children –
Consortium for Street Children

[3] የሕፃናት መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 21 አንቀጽ 14 እና 39

[4] የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መብቶች ኮሚቴ እ.አ.አ. በ2019 በሕፃናት ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ የሕፃናት መብቶች አያያዝን በተመለከተ የሰጠው አጠቃላይ ትንታኔ (አጠቃላይ ትንታኔ ቁትር 24 CRC/C/GC/24) ክፍል 3(6)

[5] የሕፃናት መብቶች አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 21 አንቀጽ 36 እና 38

[6] የሕፃናት መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 21 አንቀጽ 39

[7] የሕፃናት መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 21 አንቀጽ 13

[8] የሕፃናት መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 21 አንቀጽ 5 እና 33