የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለመጀመሪያ ጊዜ በሦስት ክልሎች በሚገኙ አምስት የአረጋውያን መንከባከቢያ ማእከላት ላይ ያከናወነውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል አስመልክቶ ባለ 41 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ኮሚሽኑ በክትትሉ የሸፈናቸው በኦሮሚያ ክልል የሚገኙት እልፍነሽ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማእከል እና ምግባረ ሰናይ የአረጋውያንና የአካል ጉዳተኞች መርጃ ድርጅት፣ በሲዳማ ክልል የሚገኘው ሜሪ ጆይ አረጋውያን ማእከል – ሃዋሳ ቅርንጫፍ እንዲሁም በአማራ ክልል የሚገኙት አጣዬ የአረጋውያንና ምስኪኖች መርጃ እና ሀበሻ የአረጋውያንና ምስኪኖች መርጃ ማኅበር ማእከል ናቸው፡፡ ዛሬ ይፋ በተደረገው ሪፖርት የአራቱ ማእከላት ግኝቶች የተካተቱ ሲሆን፤ በሀበሻ አረጋውያን እና ምስኪኖች መርጃ ማኅበር የተከናወነው ክትትል ተጨማሪ ምርመራ በማስፈለጉ በሌላ ሪፖርት የሚሸፈንና ይፋ የሚደረግ መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ ባከናወነው ክትትል የማእከላቱን ተቋማዊ አደረጃጀት፣ የተጠቃሚዎች ልየታ ሥርዓት፣ የአገልግሎት ዓይነቶች እና የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታውን ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎች፣ ከተ.መ.ድ. የአረጋውያን መርሆች እንዲሁም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ካወጣው አነስተኛ መስፈርት (minimum standard) አንጻር ለመገምገም ተችሏል፡፡ በዚህም መሠረት የጥራት ደረጃው እንደየማእከላቱ ዐቅም የተለያየ ቢሆንም ሁሉም ማእከላት የምግብና ንጹሕ የመጠጥ ውሃ፣ የመጠለያ፣ የአልባሳት፣ የግል እና የጋራ ንጽሕና መጠበቂያ ግብዓቶች እና የሕክምና አገልግሎቶች የሚያቀርቡ መሆናቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ ክትትሉ በተከናወነባቸው ሁሉም ማእከላት ውስጥ ጾታን፣ ብሔርን፣ አካል ጉዳትን ወይም የጤና ሁኔታን መሠረት ያደረጉ አድሏዊ አያያዞች፣ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ የአረጋውያንን ክብር የሚነኩ እንዲሁም ግላዊነታቸውን የሚጥሱ ድርጊቶች አለመኖራቸውን፤ በአጠቃላይ የአረጋውያኑ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ኢሰመኮ ማረጋገጡን ሪፖርቱ ጨምሮ ገልጿል፡፡

ከሰብአዊ መብቶች አኳያ ሊቀጥሉ እና ሊበረታቱ የሚገባቸው መልካም አሠራሮች ቢኖሩም የአረጋውያን መንከባከቢያ ማእከላቱ በአብዛኛው ቋሚ የገቢ ምንጭ የሌላቸው እና በገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ ያላቸው ተሳትፎም ውስን መሆኑ አገልግሎታቸውን ለማስቀጠልና ዘላቂነቱን (sustainability) ለማረጋገጥ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ የተጠቃሚዎች ልየታ ሥርዓትን በተመለከተ የማእከላቱ አሠራር ግልጽና ወጥ የቅበላ መስፈርቶች፣ ልዩ የቅሬታ መፍቻ ሥርዓት እና በየደረጃው ካሉ የመንግሥትና ማኅበረሰብ አቀፍ አደረጃጀቶች ጋር በቅንጅት እንዲሻሻል የሚጠበቅበት መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም በማእከላቱ የትምህርት፣ የሙያና የሕይወት ክህሎት ስልጠና፣ የማኅበረ ሥነ-ልቦና እንዲሁም ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቶች አቅርቦት ውስንነት ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ፤ በማንኛውም አካል ለአረጋውያን የሚደረግ እንክብካቤ የአረጋውያንን ሰብአዊ መብቶች የማክበር፣ የማስከበር እና የማሟላት ግዴታን ለመወጣት የሚከናወን ተግባር እንጂ በችሮታ ብቻ እንደሚደረግ የእርዳታ ተግባር ሊታይ እንደማይገባው አስታውሰዋል፡፡ ኮሚሽነር ርግበ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት ቀናዒነት በራሳቸው ተነሳስተው ማእከላቱን ለመሠረቱ ግለሰቦች፣ የየማእከላቱ ሠራተኞች፣ በጎ ፈቃደኞች እና ደጋፊዎች፤ በጸጥታ መደፍረስ ሁኔታዎች፣ በኑሮ ውድነት ጫናና ሌሎችም ተግዳሮቶች ሳይገደቡ አገልግሎቱን እየሰጡ መቀጠላቸውን ኮሚሽኑ እውቅና የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክለውም በማእከላቱ የሚሰጡ አገልግሎቶች ጥራትን ለማሳደግ ተገቢውን ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት የመንግሥት ቢሆንም የሚመለከታቸው አካላት ለማእከላቱ መጠናከር የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡


የአረጋውያን መንከባከቢያ ማእከላት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ሪፖርት

(Executive summary) የአረጋውያን መንከባከቢያ ማእከላት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ሪፖርት አንኳር ጉዳዮች