የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተሻሻለው የማቋቋሚያ አዋጁ አንቀፅ 6 መሰረት በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅን ክትትል የማድረግ ስልጣን እና ሀላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ በዚህም መሰረት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ የሰብአዊ መብቶችን ሁኔታ ለመከታተል የምርጫ ክትትል ቡድኖች በማቋቋም ምርጫ በሚካሄድባቸው በሁሉም ክልሎች ባለሙያዎችን አሰማርቷል፡፡

የኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ምርጫ ክትትል ቡድኖች በሚሰማሩባቸው ስፍራዎች በምርጫው እለት እና ከምርጫው በኋላ ባሉት ቀናት በምርጫ ጣቢያዎችም በመገኘት ምልከታ ያደርጋሉ፤ መራጮችን፣ የምርጫ አስተባባሪዎችን፣ የፀጥታ አካላትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ እጩዎችን፣ ታዛቢዎችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማነጋገር መረጃዎችን ያሰባስባሉ፡፡ በፖሊስ ጣቢያዎች እና በሕክምና ተቋማት በመገኘትም አስፈላጊውን ክትትል ያደረግሉ፡፡

ማንኛውም ሰው እና ተቋማት በሙሉ የኮሚሽኑን መለያ ካርድ (ባጅ) በመያዝ ለሚሰማሩት የኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ምርጫ ክትትል ቡድን አባላት አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ ይገባል፤ እንዲሁም ማንኛውም ሰው ለክትትል ቡድኑ አባላት ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ መረጃ እና ጥቆማ ማቅረብ የሚችል ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በኮሚሽኑ የነፃ የስልክ መስመር 7307 ላይ በመደወል መረጃ መስጠት እንደሚችል ኮሚሽኑ አሳውቋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በምርጫው ወቅት ሰብአዊ መብቶች መከበራቸውን ማረጋገጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሀላፊነት መሆኑን አስታውሰው ‹‹በኢሰመኮ ማቋቋሚያ አዋጅ በግልፅ በተቀመጠው መሰረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለኮሚሽኑ ስራ መሳካት ትብብር የማድረግ ግዴታቸውን እንዲወጡ እና በክትትል ስራ ለሚሰማሩት የኮሚሽኑ ባለሙያዎች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ›› ጥሪ አቅርበዋል፡፡