የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሰሜን ኢትዮጵያ ከተካሄደው ጦርነት ጋር ተያይዞ በአካል ጉዳተኞች እና በአረጋውያን ላይ የደረሱትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ለመለየት በአማራ ክልል (ባሕር ዳር፣ ደቡብ ጎንደር ደብረታቦር፣ ሰሜን ወሎ ጋሸና እና ወልድያ) እና በአፋር ክልል (ሰመራ፣ ሎጊያ፣ ዱብቲ እና ጉያህ ቀበሌ) ያከናወነውን የሰብአዊ መብቶች ክትትል ግኝቶች እና ምክረ ሃሳቦች ለማጋራት እና ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኙ ውትወታ ለማድረግ ያለሙ የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት የተገኙባቸው ሦስት የምክክር መድረኮችን ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በባሕር ዳር፣ በኮምቦልቻ እና በሰመራ ከተሞች አካሂዷል።

በዝግጅቱ ላይ የክትትሉ ግኝቶች እና ምክረ ሃሳቦች ለባለድርሻ አካላት ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ የምክክር መድረኮቹ ተሳታፊዎችም በክትትል ሂደቱ ላይ የተመለከቷቸውን ውስንነቶች፣ ከክትትሉ በኋላ የተከናወኑ እርምጃዎች፣ መካተት አለባቸው ያሏቸውን ምክረ ሃሳቦች እና በግኝቶቹ መሰረት የተሰጡ ምክረ ሃሳቦችን የአፈጻጸም ሂደት በተመለከተ አስተያየቶችና ጥያቄዎች አቅርበዋል።

ተሳታፊዎቹ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ከጦርነቱ በፊት የነበሩበት የከፋ ሁኔታ በጦርነቱ ተባብሶ ለከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና ጉዳት መጋለጣቸውን፤ ጦርነቱ በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ላይ ካስከተለው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በተጨማሪ የሰብአዊ ድጋፎች አቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠንን ጨምሮ ለአካል ጉዳተኞች እና ለአረጋውያን በሚፈለገው መጠን ተደራሽ አለመሆን፤  በመንግሥት የሚወሰዱ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ውስን መሆናቸውን እና የመልሶ ማቋቋም እና የፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ሥራዎችን በተመለከተ መንግሥት፣ ኮሚሽኑ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

እንዲሁም ጦርነቱን ተከትሎ ትምህርታቸውን ያቋረጡ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች አሁንም ድረስ በቤት   እና በመጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ በመግለጽ ይህን ጉዳይ ኮሚሽኑ ሊመለከተውና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የውትወታ ሥራ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም የምክረ ሃሳቦችን ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ ኮሚሽኑ ውሳኔ ሰጪ የመንግሥት አካላትን በተመሳሳይ መድረክ በውይይት ማሳተፍ እንዳለበት እና መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት እያንዳንዳችው ምክረ ሃሳቦቹን ለማስፈጸም የሚያስችሉ ሥራዎችን በቅርበት እና በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ኮሚሽኑ በየዘርፉ በሚያከናውናቸው የሰብአዊ መብቶች ሥራዎች የሚሰጣቸውን ምክረ ሃሳቦች አፈጻጸምን በተመለከተ በመንግሥት ጠንካራ የተጠያቂነት ሥርዓት አለመኖሩን እንደስጋት በማንሳት፤ ተሳታፊዎች በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ላይ የሚሠሩ የመንግሥት አካላት በጉዳዩ ላይ ከመቼውም ግዜ በላይ ልዩ ትኩረት መስጠት ያለባቸው ወቅት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል። 

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች በግጭቱ የደረሰባቸውን ከፍተኛ የመብቶች ጥሰት ሁሉም የባለድርሻ አካላት እንዲያጤኑት እና በቀረቡት ምክረ ሃሳቦች መሰረት የመልሶ ማቋቋም ጥረቶች አካል ጉዳተኞችንና አረጋውያንን ያካተቱ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አክለውም ኮሚሽኑ የተሰጡት ምክረ ሃሳቦች ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው የበኩሉን እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡