የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሶማሊ ክልል በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት የሚያልፉ ሕፃናት ሰብአዊ መብቶች አያያዝ እና ጥበቃ ከሕፃናት መብቶች፣ መርሖች እና መስፈርቶች አንጻር ለመገምገም ባከናወነው ክትትል ሪፖርት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከተማ ምክክር አካሂዷል። በምክክሩም ክትትል በተደረገባቸው የሶማሊ ክልል አራት ዞኖች ማለትም በሸበሌ (ጎዴ ወረዳ)፣ በቆርሃይ (ቀብሪ ዳር ወረዳ)፣ በጀረር (ደጋሀቡር ወረዳ) እና በፋፈን (ጅግጅጋ ከተማ፣ ቀብሪ በያ እና ቶጎ ጫሌ ወረዳ) የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት መሪዎች ተሳትፈዋል።

በውይይት መድረኩ በሶማሊ ክልል በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት የሚያልፉ ሕፃናት የሚያጋጥሟቸው የመብት ጥሰቶች፤ ሕፃናት በወንጀል ተግባራት ተሳታፊ እንዳይሆኑ አስቀድሞ ሊወሰዱ የሚገባቸው የመከላከል እርምጃዎች በዝርዝር ቀርበዋል። ከዚህ በተጨማሪም ሕፃናት በወንጀል ተግባራት ተሳታፊ ሆነው ሲገኙም እስርን እንደመጨረሻ አማራጭ ብቻ መጠቀምን እንዲሁም ከመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ውጪ ባሉ አማራጭ የፍትሕና የማረሚያ ስልቶች እንዲያልፉ ማድረግን የተመለከቱ የክትትል ሪፖርቱ ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ተብራርትዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የክትትሉ ግኝቶች ተቀባይነት ያላቸው መሆናቸውን ገልጸው በኮሚሽኑ ክትትል ግኝቶች ላይ ያሏቸውን ሐሳቦች አጋርተዋል። በተጨማሪም የሕፃናት መብቶችንና መርሖችን ለመተግበር አካባቢያዊ ተግዳሮቶች እንዳሉና እነዚህንም ለመቅረፍ የባለድርሻ አካላት ሁሉን አቀፍ ቅንጅታዊ አሠራር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም ኮሚሽኑ ለሚመለከታቸው አካላት በተለይም ለፍትሕ ተቋማትና ለማኅበረሰብ ተኮር አደረጃጀቶች የሚሰጣችውን ስልጠናዎች እና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር መብራቱ ገበየሁ ከወንጅል ጋር በተያያዘ በክልሉ ማረሚያ ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች ሕፃናት መኖራቸውን ጠቁመው፤ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት የሚያልፉ ሕፃናት መብቶችን አያያዝና ጥበቃ ለማሻሻል በክትትል ግኝቱ ላይ የተመሠረተ ሁሉን አቀፍ እና አሳታፊ የድርጊት መርሐ-ግብር አውጥቶ መተግበር እንዲሚያስፈልግ አብራርተዋል። አክለውም ሕፃናት፤ ቤተሰብ፤ የጎሳና የሃይማኖት መሪዎች እና  የመሳሰሉት የማኅበረሰቡ ክፍሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የፍትሕ አካላት፣ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም መንግሥትታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በቅንጅት በመሥራት በፍትሕ ሥርዓት የሚያልፉ ሕፃናት መብቶች እንዲከበሩ የበኩላቸውን ኀላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡