የአትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2014 ዓ.ም. በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ በሚገኙ 126 ፖሊስ ጣቢያዎችና 27 ማረሚያ ቤቶች ላይ ባካሄደው ክትትል የለያቸውን ክፍተቶች ለማረም ባቀረባቸው ምክረ ሃሳቦች ላይ ከማረሚያ ቤት፣ ከፖሊስ አመራሮች እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ከሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ 2 ቀናት በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት አድርጓል፡፡ 

በማረሚያ ቤት ክትትል ግኝቶች ላይ በተካሄደው ውይይት በክትትሉ የተለዩ ጠንካራ እና ትኩረት የሚሹ ክፍተቶች ተለይተዉ ቀርበዋል። በጠንካራ ጎን ከተለዩት ጉዳዮች መካከል የታራሚዎች መረጃ አያያዝ ጥሩ መሆኑ፣ ታራሚዎችን በፈርጅ ለያይተው ለመያዝ ጅምር ጥረቶች መኖራቸው፣ የቀለም ትምህርት መኖሩ፣ የምግብ ጥራትና መጠን ለማሻሻል የበጀት ማሻሻያ መደረጉ፣ በታራሚዎችና በማረሚያ ቤቶች አስተዳደር መካከል ያለው ግንኙነት ጥሩ መሆኑ፣ በአብዛኞቹ የማረሚያ ቤቶች ድብደባ እና ተያያዥ ኢ-ሰብአዊ አያያዞች መቅረታቸው፣ የአልጋ፣ የፍራሽና መኝታ አቅርቦት መሻሻል እና ተቋርጦ የነበረው ለታራሚዎች የሚሰጥ ይቅርታ መጀመሩ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ 

በሌላ በኩል የማረሚያ ቤትን ዓላማ፣ መተዳደሪያ ሕግ እና ደንብ በአግባቡ ለታራሚዎች አለማሳወቅ፣ በሚሰጠው የትምህርትና የሙያ ስልጠና የሴት ታራሚዎች ተሳትፎ ያነሰ መሆን፣ የማደሪያ ክፍሎች የንጽሕና ጉድለት፣ የማደሪያ ክፍሎች መጨናነቅ፣ የአልጋና ፍራሽ እጥረት መኖሩ፣ በቂ የሕክምና አገልግሎት አለመኖር፣ የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት፣ በብዙ ማረሚያ ቤቶች ለሴት ታራሚዎች የተመቻቸ የአምልኮ ስፍራ አለመኖር፤ በተጨማሪም ለሴት ታራሚዎች፣ ለነፍሰ ጡር ታራሚዎች፣ ከታራሚ እናቶቻቸው ጋር ለሚኖሩ ሕፃናት፣ ለአእምሮ ሕሙማን እና ለአካል ጉዳተኛ ታራሚዎች ሁኔታቸውን ያገናዘበ ልዩ ድጋፍ አለመኖሩ በክፍተት ተለይተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር እና በኮሚሽኑ ስር የሚገኙ የ36 ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኃላፊዎች፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የኦሮሚያ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ቢሮ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

የኦሮሚያ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢብራሂም ሃጂ በኮሚሽኑ ስልጣን እና አቅም መፈታት የሚችሉ ክፍተቶችን ለማረም በቁርጠኝነት የሚሠሩ መሆኑን ገልፀው አንዳንዶቹ ችግሮች ከበጀት ጋር የተያያዙ እንዲሁም የሌሎችን መስሪያ ቤቶች ትብብር የሚፈልጉ ናቸው ብለዋል፡፡ አክለውም በተለይም የኦሮሚያ ጤና ጥበቃ ቢሮ ከታራሚዎች የጤና አገልግሎት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ መስሪያ ቤቱ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይ ኢሰመኮ በ2014 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በፖሊስ ጣቢያዎች የተጠርጣሪዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ያደረገውን ክትትል መሰረት በማድረግ በክትትሉ ግኝቶች ላይ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን እና በኮሚሽኑ ስር ከሚገኙ ከ21 የዞን እና ከ19 የከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎች፣ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንዲሁም ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከተውጣጡ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

ኢሰመኮ በክትትሉ በጠንካራ ጎን ከለያቸው ጉዳዮች መካከል፣ ተጠርጣሪዎች አብዛኛውን ጊዜ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ሕግን መሰረት አድርጎ መሆኑ፣ የተጠርጣሪዎች መረጃ ከሞላ ጎደል በፖሊስ መዝገብ ላይ መመዝገቡ፣ ሥርዓታዊ የሆነ አካላዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት መቀነሱ፣ የተጠርጣሪ እና የቤተሰብ ጉብኝት ሁኔታ ጥሩ መሆኑ የሚጠቀሱ ናቸዉ፡፡

ክፍተቶችን በተመለከተ በወቅታዊ ሁኔታ እና ጸጉረ ልውጥ ናቸው ተብለው የሚያዙ ሰዎች በእስረኛ መዝገብ ላይ አለመመዝገባቸው፣ በዚህ ሁኔታ የሚያዙ ተጠርጣሪዎች በሕግ በተቀመጠ ጊዜ ውስጥ ወይም ሙሉ በሙሉ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸው፣ በተወሰኑ የፖሊስ ጣቢያዎች ተጠርጣሪዎች የተያዙበት ምክንያት የማይነገራቸው መሆኑ፣ የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ሕግን ባልተከተለ መልኩ ከአስተዳደር አካላት እና “ከፀጥታ ምክር ቤቶች” በሚሰጡ ትዕዛዞች ሰዎች የሚታሰሩ መሆኑ፣ በአንዳንድ የፖሊስ ጣቢያዎች በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ሰዎች ታስረው መገኘታቸው የሚጠቀሱ ናቸው። 

በተጨማሪም በፍርድ ቤት ነፃ የተባሉ፣ የምርመራ መዝገባቸው የተዘጋ ወይም በዋስትና የተለቀቁ ሰዎችን አስሮ ማቆየት እየተለመደ መምጣቱ፣ በወንጀል በተጠረጠሩ ሌሎች ሰዎች ምትክ የቤተሰብ አባላትን ማሰር በስፋት እና በበርካታ ፖሊስ ጣቢያዎች መታየቱ፣ ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበትን ወንጀል እንዲያምኑ ወይም ተይዘው ባሉበት ለሚፈጽሙት ጥፋት የሚደበደቡ መሆናቸው፣ በበጀት እጥረት ምክንያት ለተጠርጣሪዎች የምግብ፣ የውሃ እና የሕክምና አገልግሎት የማይቀርብ ወይም እጅግ ውስን በመሆኑ ከቤተሰብ ርቆ የሚታሰሩ ተጠርጣሪዎች ከፍተኛ ችግር ላይ መውደቃቸው በዋነኝነት ተነስተዋል፡፡

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል አራርሳ መርዳሳ በክልሉ የሚስተዋለው የፀጥታ ችግር የፖሊስ ሥራ ላይ የራሱን ተጽዕኖ ያሳደረ መሆኑን ገልፀው፤ ይህንን ሁኔታ እንደ ዕድል በመጠቀም የተጠርጣሪዎችን መብቶች መጣስ የማይገባ እና የታዩ ክፍተቶችም መታረም እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ኮሚሽነር ግርማ ገላን፣ የኢሰመኮን የክትትል ግኝቶች እና ምክረ ሃሳቦች እንደ ግብዓት በመውሰድ የማስተከካያ እርምጃ እንደሚወስዱ ቃል ገብተዋል፡፡ 

የኢሰመኮ የምርመራ እና ክትትል ሪጅናል ዳይሬክተር አቶ ኢማድ አብዱልፈታ በበኩላቸው ያሉ ሀገራዊ እና ክልላዊ ተግዳሮቶች እንደተጠበቁ ሆነው የተጠርጣሪዎች እና የታራሚዎችን ሰብአዊ መብቶች ለማሻሻል የታየውን ተነሳሽነት አድንቀው ሁለቱም ተቋማት የኢሰመኮን ግኝቶች እና ምክረ ሃሳቦች በቅንነት በመውሰድ ለውጥ ለማምጣት በቁርጠኝነት እንዲሰሩበት፣ ሌሎችም ተገቢነት ያላቸው የመንግሥት አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እና ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል፡፡