የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍን የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ባለ 46 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ የተዘጋጀው የዘርፍ ሪፖርት ኢሰመኮ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ላይ በተጨማሪነት በተለይ የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ በዝርዝር በማተኮር ኮሚሽኑ የለያቸውን አበረታች እመርታዎችን፣ ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮችን እና ምክረ ሐሳቦችን አካቷል፡፡

ኮሚሽኑ ሪፖርቱን ያዘጋጀው በበጀት ዓመቱ ባከናወናቸው ክትትሎች፣ ምርመራዎችና የመስክ ምልከታዎች፣ ባስተናገዳቸው የግለሰቦች አቤቱታዎች፣ የሕግና የፖሊሲ ግምገማዎች፣ ጥናቶች እና ምክክሮች፣ የማኅበረሰብ ውይይቶች፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንዲሁም የውትወታ እና ሌሎች ሥራዎቹ ላይ በመመሥረት ነው።

ሪፖርቱ የሴቶችና የሕፃናት ከጥቃት የመጠበቅ መብት፣ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት የሴቶች እና ሕፃናት መብቶች አያያዝ፣ የሕፃናት በቂ የኑሮ ደረጃ የማግኘት መብት፣ የቤተሰብ እንክብካቤ ያጡ ሕፃናት መብት ላይ ትኩረት አድርጓል። በተጨማሪም የሴቶች ጤናማ የሥራ ሁኔታ የማግኘት እና የፖለቲካ ተሳትፎ እና የሰላም እና ደኀንነት መብቶች እንዲሁም በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ የደረሱ የሕፃናት እና የሴቶች ሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሁኔታ ሪፖርቱ ትኩረት ያደረገባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው።

በአበረታች እመርታነት በሪፖርቱ ከተለዩ መካከል የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ ክለሳ ሂደት የማስረጃ ሕግ ድንጋጌዎችን ማካተቱ፣ በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕን ለመተግበር በተዘጋጀው ረቂቅ የፖሊሲ አማራጮች (Green Paper) ዙሪያ ሴቶች እንዲሁም በሴቶችና በሕፃናት መብቶች ላይ የሚሠሩ ተቋማት እንዲሳተፉና ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ጥረት መጀመሩ እና የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ሰላምና ደኅንነት ብሔራዊ የድርጊት መርኃ ግብር /National Plan of Action on Women, Peace and Security/ የመንደፍ ዝግጅት መጀመሩ ይገኙበታል። በተጨማሪም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽንን እንደገና ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 186/2014 በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ሴቶች፣ በወንጀል ጉዳይ የታሰሩ ሕፃናት እና አካል ጉዳተኞች ልዩ ድጋፍ እና እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ዕውቅና የሚሰጥና ጥበቃ የሚያደርግ የሕግ ማዕቀፍ መሆኑ በመልካም እመርታነት በሪፖርቱ ተካተዋል።

በሌላ በኩል የሴቶችና የሕፃናት ከጥቃት የመጠበቅ መብታቸው፤ በሰው መነገድ ድርጊት፣ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ በጠለፋና አስገድዶ መድፈር እንደተጣሰ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሂደት የጥቃት ተጎጂ የሆኑ ሕፃናት እና ሴቶችን ለዳግም ጥቃት የሚያጋልጥ፤ በሦስተኛ ወገን ወይም በጥቃት አድራሾች ለሚደርስባቸው ተጨባጭ ሥጋቶች በቂ ጥበቃ እና ከለላ የማይሰጥ፤ ከዕድሜ፣ ከጾታ እና ከአካል ጉዳተኝነት ልዩ ፍላጎቶች ጋር የተጣጣመ እንዳልሆነም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ በተያያዘ በወንጀል የተጠረጠሩ ወይም የተከሰሱ ሕፃናት ከመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ውጪ ጉዳያቸው የሚታይበት አሠራር የሌለ መሆኑ እና በፖሊስ እና በማረሚያ ቤቶች ያለው አያያዝም ሰብአዊ መብቶቻቸውን እና ክብራቸውን የሚጥስ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

በሪፖርቱ የቤተሰብ እንክብካቤ አጥተው በጎዳና እና በማሳደጊያ ተቋማት የሚኖሩ ሕፃናትን በተመለከተ ኮሚሽኑ በክትትል ያገኛቸውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎች አቅርቧል። እንዲሁም አንዳንድ የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት የወላጅ እንክብካቤን ያጡ ሕፃናትን የሚቀበሉበት መሥፈርቶች አድሎአዊ መሆናቸው እና በተቋማቱ የሚሰጡት አገልግሎቶችም የሕፃናትን ዕድሜ እና ልዩ ፍላጎቶቻቸውን መሠረት ያደረገ እንዳልሆነ በሪፖርቱ በአሳሳቢነት ተጠቅሷል፡፡ በተመሳሳይ በአዲስ አበባ በዓላትን እና የተለያዩ ሁነቶችን ምክንያት በማድረግ በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት በግዳጅ እና በጅምላ ታፍሰው ከጎዳና ላይ የሚነሱበት እና ተይዘው የሚቆዩበት መንገድ ሰብአዊ መብቶቻቸውን የሚጥስ መሆኑም በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

በሃዋሳ ኢንደስትሪ ፓርኮች ለሚሠሩ በተለይም ነፍሰ-ጡር ለሆኑ ሴት ሠራተኞች አገልግሎት የሚሰጥ የጤና ተቋም በፓርኩ ውስጥ አለመኖር እና የሠራተኞችን የመደራጀት መብት የሚያጣብብ አሠራር መኖር በአሳሳቢነታቸው የቀጠሉ የመብቶች ጥሰቶች እና በአፋጣኝ ሊሰስተካከሉ የሚገቡ ክፍተቶች ስለመሆናቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ በሀገሪቱ በተከሰቱ ሰው ሠራሽ ቀውሶች እና የተፈጥሮ አደጋዎች የተነሳ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶችና ሕፃናትን ለመፈናቀል፣ ለጾታዊ ጥቃቶች እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲሁም ለሌሎች ተደራራቢ የመብቶች ጥሰቶች ተጋላጭነታቸውን እንደጨመር በሪፖርቱ ተገልጿል። የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ የሕፃናት እና የሴቶችን መብቶች በተመለከተ ኮሚሽኑ ባከናወናቸው ክትትሎች፣ ምክክሮች እና የተለያዩ ክንውኖች ትብብር በማድረግ እና ግብአት በመስጠት ኃላፊነታቸውን ለተወጡ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው “ሕፃናትና ሴቶች ሰብአዊ መብቶቻቸው ተከብረው ከጥቃት፣ ከሥጋትና ከመድልዎ ነጻ የሆነ፤ ሰላም፣ እኩልነትና ሰብአዊ ክብር የሰፈነበት ሕይወትን እንዲኖሩ በሪፖርቱ የተካተቱትን ምክረ ሐሳቦች ለማስፈጸም ጥረት እና ርብርብ ሊደረግ ይገባል” በማለት አሳስበዋል፡፡