የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በኦሮሚያ ክልል በተለይም ከመስከረም 1 ቀን 2014 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ባሉት ሁለት ዓመታት ያደረገውን ክትትል እና ምርመራ መሠረት በማድረግ ከሕግ/ከፍርድ ውጪ የሆኑ እና በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢ መሆናቸውን በማመላከት በተለይም የክልሉ እና የፌዴራል የጸጥታ አካላት ተገቢውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነት ማረጋገጥን ጨምሮ ዘላቂ መፍትሔ በአስቸኳይ እንዲሰጡ ጥሪ አድርጓል።

የሁለቱን ዓመታት ግኝቶች ይፋ የሚያደርገው ይህ ዛሬ ይፋ የሆነው ባለ 11 ገጾች ሪፖርት በክልሉ ቄለም ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ አርሲ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ሰሜን ሸዋ እና ምሥራቅ ሸዋ ዞኖች ላይ ያተኮረ ነው። መረጃ እና ማስረጃዎች ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂዎች ቤተሰቦች፣ ከዐይን ምስክሮች፣ ከሕክምና ባለሙያዎች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከአባገዳዎች እና ከመንግሥት አካላት በአጠቃላይ 158 ሰዎችን በማነጋገር የተሰባሰቡ ናቸው።

የሪፖርቱ መረጃዎች በተሰባሰቡባቸው 9 ዞኖች የሚንቀሳቀሱ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች፣ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ” በመባል የሚጠራው) እና ኢ-መደበኛ የአማራ ታጣቂዎች ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎችን በመጣስ በግጭት ወይም በውጊያ ዐውድ እና ከውጊያ ዐውድ ውጭ በርካታ ሲቪል ሰዎችን ከሕግ ወይም ከፍርድ ውጪ መግደላቸውን ኮሚሽኑ ማረጋገጥ ችሏል። በዚህ ሪፖርት ዝርዝሩ በቀረበባቸው ጉዳዮች፣ ኮሚሽኑ የተገደሉትን በርካታ ሰዎች ማንነታቸውን ለማጣራትና ለማረጋገጥ ችሏል፡፡ በተጨማሪም በርካታ ሲቪል ሰዎች ለከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት፣ ለተስፋፋ እገታ፣ መፈናቃል እና ዝርፊያ ተዳርገዋል።

በተለይም ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች እና ሌሎች በሰዎች ላይ የደረሱ ጉዳቶች “እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች” ሲሆኑ፣ ዓለም አቀፍ ባልሆነ ጦርነት ዐውድ ውስጥ ለሲቪል ሰዎች የሚሰጠውን ጥበቃ በመተላለፍ የተፈጸሙ ከመሆናቸው አንጻር የጦር ወንጀልን እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀልንም ሊያቋቁሙ የሚችሉ ናቸው። ስለሆነም፣ ፈጣን፣ ገለልተኛ እና የተሟላ የወንጀል ምርመራ ሊደረግባቸው እና ተጠያቂነት ሊረጋገጥበትና ተጎጂዎችም ሊካሱበት የሚገባ፤ እንዲሁም ለግጭቱ ዘላቂ ሰላማዊ መፍትሔዎችን ማፈላለግ የሚገባ መሆኑን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አሳስቧል። በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ የሰብአዊ መብቶችን እና የሰብአዊነት ሕጎችን፣ መርሖችንና ድንጋጌዎች እንዲያከብሩ በተለይም በሲቪል ሰዎች ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠቡ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አሳስቧል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ኮሚሽኑ ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ ያወጣውን መግለጫ አስታውሰው፣ “የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ በብዙ ቦታዎች ለቀጠለው ግጭትና መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሁሉም ወገኖች በቁርጠኝነት ሰላማዊ ውይይትን ከመቀበልና ከመተግበር ውጪ መፍትሔ የለም፣ የግጭቶቹ መራዘምም የሰዎችን ሥቃይ ያራዝማል እንጂ መፍትሔን አይወልድም” ብለዋል።