የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2015 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ 118 ፖሊስ ጣቢያዎችና 14 ማረሚያ ቤቶች ላይ ባካሄደው ክትትል በለያቸው ግኝቶች እና በሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች ዙሪያ ሰኔ 18 እና 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ባዘጋጃቸው ሁለት መድረኮች ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይት መድረኮቹ ላይ የኦሮሚያ ክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር እና በኮሚሽኑ ሥር የሚገኙ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኀላፊዎች፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የከተማ እና የዞን አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኀላፊዎችተገኝተዋል፡፡ በተጨማሪም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት፣ የጨፌ ኦሮሚያ የአስተዳደር፣ ፍትሕ እና የሰው ሀብት ልማት ቋሚ ኮሚቴ፣ በኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የፍትሕ እና ጸጥታ ክላስተር ማስተባባሪያ ጽ/ቤት፣ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ፣ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ፣ ትምህርት ቢሮ እና ሴንተር ፎር ጀስቲስ የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ተወካዮች በውይይቱ ተሳትፈዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ
የውይይቱ ተሳታፊዎች በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ

ማረሚያ ቤቶች በፍርድ ቤት ትእዛዝ ብቻ ታራሚዎችን መቀበላቸውና የመረጃ አያያዝ የተሻሻለ መሆኑ፣ የተወሰኑ ክፍተቶች ቢታዩበትም ከትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር ታራሚዎችን የቀለም ትምህርት ማስተማር መቻሉ፣ ታራሚዎች በፈርጅ ተለያይተው መያዛቸው፣ በአብዛኞቹ ማረሚያ ቤቶች ኢ-ሰብአዊ አያያዝ በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ፣ የማረሚያ ቤቶች የግቢ እና የክፍሎች ንጽሕና አጠባበቅ መሻሻሉ፣ ታራሚዎችን አደራጅተው ሥራ ላይ ከማሠማራት አንጻር አበረታች ጅምሮች መኖራቸው፣ የመኝታ ክፍል፣ የአልጋ እና የፍራሽ አቅርቦት መሻሻል፣ የማረሚያ ቤቶች ማስፋፊያ ግንባታ፣ እድሳት እና የግብአት ማሟያ ግዢ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸው፣ በቂ የውሃ አቅርቦት እንዲኖር በትኩረት እየተሠራ መሆኑ እንዲሁም በአብዛኞቹ ማረሚያ ቤቶች በታራሚዎችና በአስተዳደር መካከል ያለው ግንኙነት ጥሩ መሆኑ በውይይት መድረኩ በአዎንታዊነት ተጠቅሰዋል፡፡

በተመሳሳይ በፖሊስ ጣቢዎች የወንጀል ተጠርጣሪዎች በአብዛኛው በሕጋዊ መንገድ ማስተናገዳቸው፣ የተጠርጣሪዎች መረጃ አያያዝ መሻሻል፣ ሥርዓታዊ የሆነ አካላዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት አለመኖር፣ የተጠርጣሪዎች የጉብኝት መብት አፈጻጸም የተሻለ መሆኑ እንዲሁም በተጠርጣሪዎች ላይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የፈጸሙ የፖሊስ አባላት ላይ የወንጀል እና የአስተዳደር እርምጃዎችን ከመውሰድ አንጻር አበረታች ጅምሮች መኖራቸው በበጎ መልኩ ተጠቅሰዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ
የውይይቱ ተሳታፊዎች በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ

በሌላ በኩል በተወሰኑ ማረሚያ ቤቶች የማደሪያ ክፍሎች መጨናነቅ፣ የአልጋና ፍራሽ እጥረት ሙሉ በሙሉ አለመቀረፉ፣ በተወሰኑ ቦታዎች አሁንም የታራሚዎች ድብደባና ተያያዥ ኢ-ሰብአዊ አያያዞች መከሰታቸው በውይይቱ ተገልጿል፡፡ እንዲሁም በማረሚያ ቤቶች ውስጥ በሚገኙ የጤና ተቋማት እና በክልሉ ጤና ቢሮ መካከል ያለው የሥራ ግንኙት ደካማ በመሆኑ በሕክምና ቁሳቁስ እና በሕክምና ባለሙያ እጥረት ምክንያት ታራሚዎች ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸው፤ ለታራሚዎች ይሰጥ የነበረው ይቅርታ እና ምሕረት መስፈርቱን ለሚያሟሉ ታራሚዎች ጊዜውን ጠብቆ አለመሰጠቱ፣ በማረሚያ ቤቶች የታራሚ ፋይሎች አያየዝ ሥርዓት ወደ ዲጂታል ባለመቀየሩ ለአደጋ ተጋላጭ መሆኑ፣ ለታራሚዎች የሚቀርብ ምግብ ከጥራትና መጠን አንፃር በእጅጉ መቀነሱ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የሴት ታራሚዎችን በተመለከተ የትምህርት ተሳትፏቸው አነስተኛ መሆን፣ የተመቻቸ የአምልኮ ስፍራ አለመኖሩ፤ ለሴት ታራሚዎች እና ለነፍሰጡር ሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እና ሌሎች ሁኔታቸውን ያገናዘበ ድጋፍ የማይቀርብላቸው መሆኑ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል ተጠቅሰዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ  ከእናቶቻቸው ጋር የሚታሰሩ ሕፃናት ተገቢውን ድጋፍ እያገኙ አለመሆናቸው እንዲሁም  ለአእምሮ ሕሙማን እና ለአካል ጉዳተኛ ታራሚዎች ሁኔታቸውን ያገናዘበ ልዩ ድጋፍ አለመኖሩ ከተለዩ ክፍተቶች መካከል ይገኙበታል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ

በፖሊስ ጣቢያዎች “ወቅታዊ ሁኔታ” በሚል ምክንያት የሚያዙ ተጠርጣሪዎች በሕግ በተፈቀደው ጊዜ ወይም ሙሉ በሙሉ ፍርድ ቤት የማይቀርቡ መሆናቸው፣ በአብዛኛው ተጠርጣሪዎች ሲያዙ የተያዙበት ምክንያት የማይነገራቸው መሆኑ፣ በሚያዙበት ጊዜ እና ፖሊስ ጣቢያ ከገቡ በኋላ በፖሊስ አባላት ድብደባ የሚፈጸምባቸው ተጠርጣሪዎች መኖራቸው፣ የምግብ፣ የውሃ እና የሕክምና አገልግሎት የማይቀርብ ወይም ውስን መሆኑ፣  ተገልጿል፡፡

በፍርድ ቤት ነጻ የተባሉ እና ዋስትና የተጠበቀላቸው እንዲሁም በዐቃቤ ሕግ አያስከስስም ተብሎ መዝገባቸው የተዘጋ ሰዎችን አስሮ የማቆየት ተግባራት መኖራቸው፣ በወንጀል በተጠረጠሩ ሰዎች ምትክ የቤተሰብ አባላትን ማሰር፣ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሰዎች በአስተዳደር አካላት፣ በቀድሞ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት፣ በመከላከያ ሰራዊት አባላት እና በፖሊስ ጭምር ሕጋዊ አካሄድን ሳይከተሉ መታሰራቸው፤ አልፎ አልፎ  ከፖሊስ ጣቢያ ውጪ ኢ-መደበኛ በሆኑ ቦታዎች እንዲቆዩ መደረጋቸው እና በአንዳንድ በክልሉ በሚገኙ የፖሊስ ጣቢያዎች በፍትሐ ብሔር ጥፋቶች ምክንያት ሰዎች ታስረው መገኘታቸው በአሳሳቢነት ከተለዩ ጉዳዮች መካከል ናቸው፡፡

የኦሮሚያ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢብራሂም ሃጂ በመድረኩ በሰጡት አስተያይት የታራሚዎችን አያያዝ ለማሻሻል ብዙ እርምጃዎች መወሰዳቸውን እና በዚህም ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን ጠቅሰው ኢሰመኮ የሚያቀርባቸውን ምክረ ሐሳቦች የኮሚሽኑ ሥልጣን እና ዐቅም በፈቀደ መጠን ተፈጻሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡ ኮሚሽነሩ አክለውም የተወሰኑት ክፍተቶች ከበጀት እጥረት ጋር የተያያዙና የሌሎች ተቋማትን ድጋፍ የሚፈልጉ በመሆናቸው የሚመለከታቸው አካላት ተገቢ የሆነ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ
የውይይቱ ተሳታፊዎች በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘርሁን ዱጉማ በበኩላቸው ኢሰመኮ በፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ክትትል አድርጎ ያቀረባቸው አብዛኞቹን ግኝቶች የሚቀበሏቸው መሆኑን ጠቅሰው በክልሉ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የፈጠራቸው ተግዳሮቶች እንደተጠበቁ ሆነው መሥሪያ ቤታቸው ባደረጋቸው ማጣራቶች እና ከኢሰመኮ የሚቀርቡለትን ምክረ ሐሳቦች መነሻ በማድረግ በርካታ የእርምት እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል ለሰብአዊ መብቶች መከበር የፖሊስ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚያው ልክ የፖሊስ ሥራ በጥብቅ ሕግ እና ዲሲፕሊን ካልተመራ ለሰብአዊ መብቶች መጣስ መንሴ ሊሆን እንደሚችል  ጠቁመዋል፡፡ ዶ/ር አብዲ አክለውም “የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በኢሰመኮ የተለዩ ክፍተቶችን ለማረም ከዚህ በፊት የጀመራቸውን ተጠያቂነትን የማረጋገጥ እና አሠራሮችን የማሻሻል ተግባራትን በቁርጠኝነት በማስቀጠል የተጠርጣሪዎችን መብቶች በዘላቂነት ለማስከበር ተግባራዊ የለውጥ እርምጃዎችን እንዲወስድ” አሳስበዋል፡፡

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል ሪጅናል ዳይሬክተር ኢማድ አብዱልፈታህ በበኩላቸው “ጨፌ ኦሮሚያ እና የኦሮሚያ ጤና ቢሮ በክልሉ ማረሚያ ቤቶች እያጋጠመ ያለውን የምግብ እና የጤና አገልግሎት አቅርቦት እና የጥራት ጉድለት ለመቅረፍ  ከማረሚያ ቤቶች ጋር በቅንጅት በመሥራት ተገቢ የሆኑ ድጋፎችን ማድረግ አለባቸው” ብለዋል፡፡