የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከኅዳር 10 እስከ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በሸገር ከተማ በፖሊስ ማቆያዎች እና በሸገር ከተማ ማረሚያ ቤት በጥበቃ ሥር ያሉ የተጠርጣሪዎችና የታራሚዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ባደረገው ክትትል በለያቸው ግኝቶች እና ባቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥር 30 እና የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እና ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለን ጨምሮ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር፣ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የሸገር ከተማ ዐቃቤ ሕግ፣ የኦሮሚያ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ፣ የሸገር ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ ኃላፊ፣ የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ተሳትፈዋል። በተጨማሪም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ተወካይ፣ የኦሮሚያ ገንዘብ ቢሮ ተወካይ፣ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ተወካይ፣ የሸገር ከተማ ማረሚያ ቤት ምክትል ዳሬክተር፣ የኦሮሚያ ማረሚያ ቤቶች ምክትል ዋና ኮሚሽነር እናየማረሚያ ቤቱ ክሊኒክ ኃላፊ፣ እንዲሁም በሸገር ከተማ ዋና መምሪያ ሥር የሚገኙ የ12ቱም ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች የወንጀል ምርመራና መከላከል ዘርፍ ኃላፊዎች በዝግጅቱ ተገኝተዋል።
በውይይት መድረኩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሚፈጽሙ አባላት ላይ አስተማሪ የሆነ እርምጃ መወሰድ መጀመሩ፣ ተጠርጣሪዎች በሚገባቸው ቋንቋ ቃላቸውን እንዲሰጡ እና ሳምንቱን ሙሉ በቤተሰብ እንዲጠየቁ መደረጉ በክትትሉ በጠንካራ ጎን የታዩ ናቸው። በሌላ በኩል አብዛኞቹ ፖሊስ ጣቢያዎች ተጠርጣሪዎችን በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት እንደማያቀርቡ፣ ፍርድ ቤት ተጠርጣሪዎችን በዋስትና ከለቀቀ በኋላ ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ የራሳቸው ወይም የሌላ ሰው ካርታ ወይም የመኪና ባለንብረትነት ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ መጠየቁ፣ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር በሚውሉበት ጊዜ ያለመናገር መብት እንዳላቸው እና የሚናገሩት ቃል በፍርድ ቤት በማስረጃነት ሊቀርብባቸው እንደሚችል እንደማይነገራቸው፣ የተጠርጣሪዎች የምግብ በጀት አነስተኛ መሆኑና በሁሉም ክፍለ ከተማዎች ወጥ በሆነ መልኩ አለመመደቡ እና ነጻ የሕህክምና አገልግሎት አለመኖር በአሉታዊነት በክትትሉ የተለዩ ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል።
የሸገር ከተማ ማረሚያ ቤትን በሚመለከት ታራሚዎችን በገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ በማሰማራት እና አምራች ዜጎች ሆነው እንዲወጡ እንደሚሠራ፣ ከእናቶቻቸው ጋር በማረሚያ ቤት የሚገኙ ሕፃናት ትምህርታቸውን ከማረሚያ ቤቱ ውጪ መቀጠል እንዲችሉ እገዛ መደረጉ፣ የታራሚዎች ማደሪያ ክፍሎች ደረጃቸውን የጠበቁ፣ ንጽሕናቸው የተጠበቀ እና በቂ መንቀሳቀሻ ስፍራ ያላቸው መሆናቸው በጠንካራ ጎን የተነሱ ጉዳዮች ናቸው።
በተቃራኒው የማረሚያ ቤቱ ሕጎችና መመሪያዎች ለታራሚዎች በጽሑፍ አለመድረሱ፣ የተመደበው የምግብ በጀት አነስተኛ በመሆኑ በቂና ጥራቱን የጠበቀ ምግብ አለመቅረቡ፣ የሪፈራል ማረሚያ ቤት እንደመሆኑ የማረሚያ ቤቱ ክሊኒክ ከተለያዩ የኦሮሚያ ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎችን ተቀብሎ ቢያስተናግድም በቂ የመድኃኒትና የቁሳቁስ አቅርቦት አለመኖሩ፣ በከፍተኛ የሕክምና ተቋማት መታከም ያለባቸው ታራሚዎች በተሽከርካሪ እና አጃቢ እጥረት እንዲሁም ከሕክምና ተቋማቱ ጋር የነበረው ውል በመቋረጡ የሕክምና አገልግሎቱ በሚፈለግበት ጊዜ አለመቅረቡ እንደ ክፍተት የተለዩ ናቸው፡፡
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ዘሪሁን ዱጉማ፣ ሰብአዊ መብቶችን ማስከበር የጋራ ኃላፊነት እንደሆነና የሰብአዊ መብቶች አለመከበር ሰላምና እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ገልጸዋል። አክለውም የሰብአዊ መብቶች መከበር ላይ የፖሊቲካ ቁርጠኝነት ቢኖርም በክልሉ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ተግዳሮት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ምክትል ዋና ኮሚሽነሩ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በፈጸሙ ከ800 በላይ በሚሆኑ አባላት ላይ የቅጣት እርምጃ እንደተወሰደ እና በ48 ሰዓት ተጠርጣሪዎችን ፍርድ ቤት ማቅረብን በሚመለከት በመደበኛ ወንጀሎች ላይ ችግር እንደሌለ ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሚሊሻ ጽሕፍት ቤት ኃላፊ አቶ መገርሳ ድርብሳ በበኩላቸው የሚስተዋሉ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ክፍተቶችን ለመፍታት ከክልሉ ዐቃቢ ሕግ ቢሮ ጋር በመቀናጀት ለሚሊሻ አባላት ስልጠና እየተሰጥ መሆኑን ገልጸዋል። የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ከአመክሮ አፈጻጸም መዘግየት ጋር ተያይዞ ለተነሳው ችግር በፍርድ ቤቶች በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሠራሮች መፍትሔ ለመስጠት ተቀራርቦና ተናቦ መሥራት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
በክትትሉ የተለዩ ግኝቶችን መነሻ በማድረግ ተሳታፊዎች ከተሰጣቸው ኃላፊነት በመነሳት ሊተገብሩ የሚገባቸው ምክረ ሐሳቦች ላይ የቡድን ውይይት አድርገው በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ሊከናወኑ የሚገባቸው ተግባራትን በመለየት የአንድ ዓመት ድርጊት መርኃ ግብር አዘጋጅተዋል።
የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር ዶ/ር ሚዛኔ አባተ፣ የመድረኮቹ ዓላማ የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለመመካርና መፍትሔ ለማፈላለግ፣እንዲሁም በተቋማቱ መካከል የልምድ ልውውጥ በማድረግ የተጠርጣሪዎችና ታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ የተሻሻለ እንዲሆን ማገዝ መሆኑን አብራርተዋል። አክለውም በአስቸኳይ ጊዜ ዐውድም ሆነ የመንግሥት የአስተዳደርና የጸጥታ አካላት ‘ወቅታዊ ሁኔታ’ ብለው የሚለዩት ሁኔታ ሲከሰት ሰላምና ደኅንነትን የማስከበር፣ ወንጀል የመከላከልና የወንጀል ምርመራ ሥራ በሕግ አግባብ ብቻ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።