የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ በእስር ላይ የነበሩ በርካታ ሰዎች ታኅሣሥ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ጨምሮ ባለፉት ቀናት ከእስር መለቀቃቸው አበረታች እርምጃ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ከእስር ከተለቀቁት መካከል ሴቶች፣ አረጋውያን፣ የጤና ችግር ያለባቸው እና ሌሎች ጉዳያቸው ተጣርቶ በቀላል ዋስትና የተለቀቁ ሰዎች ይገኙበታል፡፡ 

ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ እና በሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች ተመሳሳይ እርምጃዎች እንዲቀጥሉ፣ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ ከግምት በማስገባት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተደነገገው መሰረት በሀገር አቀፍ ደረጃ አስፈላጊነቱና የተፈጻሚነቱ አካባቢያዊ ስፋት እየተገመገመ ተገቢው ማሻሻያ እንዲደረግ ጥሪ ያቀርባል፡፡ በተጨማሪም ጋዜጠኞችን ጨምሮ አሁንም በቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎች የተያዙበት ጉዳይ የማጣራት ሂደቱ የተፋጠነ እንዲሆን፣ የእስር አያያዝ እንዲሻሻል፣ የታሰሩበት ስፍራ ለቤተሰቦች ያልተገለጸ ሰዎች እንዲገለ፤ እንዲሁም በአጠቃላይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የሰብአዊ መብቶችን መርሆች ባከበረ መልኩ መተግበሩ እንዲረጋገጥ በድጋሚ ያሳስባል።

የእንግሊዝኛውን ቅጂ እዚህ ያንብቡ