የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰብአዊ መብቶች ትምህርት የሥራ ክፍል ‘በሰላም፣ አብሮነት እና መቻቻል’ ላይ ያተኮረ የሰብአዊ መብቶች የአሰልጣኞች ስልጠና በጎንደር፣ መቱ፣ ሎጊያ እና አሶሳ ከተሞች አካሂዷል። ከሚያዚያ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የቆየው ስልጠና በባሕርዳር፣ ጋምቤላ፣ ሰመራ እና አሶሳ ከተሞች ከሚንቀሳቀሱ የወጣት ማኅበራት እና በወጣቶች ላይ ከሚሰሩ የሲቪክ ማኅበራት የተውጣጡ 29 ሴት እና 110 ወንድ በድምሩ 139 ወጣቶችን አሳትፏል።

ስልጠናው የወጣት ማኅበራት አባላት እና አመራሮችን የሰብአዊ መብቶች እውቀት፣ አመለካከት እና ክህሎት በመገንባት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል ያለመ ነበር። በተጨማሪም የስልጠናው ተሳታፊዎች የእለት ተእለት ሁኔታዎችን ከሰብአዊ መብቶች አንፃር እንዲተነትኑ እና ስራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት በተቋምም ሆነ በግለሰብ ደረጃ በተግባር ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች እንዲለዩ እና እንዲተገብሩ በሚያስችል ይዘት የተዋቀረ ነው።