የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ሰኔ 13 (June 20) የሚከበረው የስደተኞች ቀንን በማስመልከት የከተማ ስደተኞች የሰብአዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ ባሉ መልካም ዕድሎች እና ተግዳሮቶች ዙሪያ ሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ውይይት አካሂዷል።  በመድረኩ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚኖሩ ኤርትራዊያን፣  ሱዳናውያን እና የኮንጎ ስደተኞች፤ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ዋና ኮሚሽነር (UNHCR) እንዲሁም ከጄሱዪት ሬፊዩጂ ሰርቪስ (Jesuit Refugee Service) የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የኮሚሽኑ ሥልጣን እና ተግባራት ለተሳታፊዎች የተብራራ ሲሆን ኮሚሽኑ በ2015 ዓ.ም. በጋምቤላ፣ በሶማሊ፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች በሚገኙ ዘጠኝ መጠለያ ጣብያዎች ውስጥ በሚገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ዙሪያ ክትትል ማከናወኑን፤ የክትትል ግኝቶችን እና ምክረ ሐሳቦችን መሠረት በማድረግ የስደተኞች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ይሻሻል ዘንድ የውትወታ ሥራ መሠራቱ ተገልጿል። በተጨማሪም ለስደተኞች አገልግሎት ለሚሰጡ አካላት በስደተኞች መብቶች ዙሪያ ስልጠና መሰጠቱን፤ ከስደተኞች፣ ከኤምባሲዎች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ኮሚሽኑ አቤቱታዎችን መቀበሉን እና በቀረቡት አቤቱታዎች መሠረት የምርመራ እና የውትወታ ሥራ ማከናወኑ ተመላክቷል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ ስደተኞች በተለያዩ ተቋማት ለስደተኞች የሚሰጠው አገልግሎት ግልጽነት የጎደለው እንዲሁም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በስደተኞች መብቶች ላይ በቂ ግንዛቤ አለመኖሩ ከለዩአቸው ተግዳሮቶች መካከል መሆናቸውን አስረድተዋል። በተመሳሳይ የስደተኞች ምዝገባና የሰነድ አገልግሎት ላለፉት ሁለት ዓመታት በመቋረጡ ምክንያት የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መኖራቸውን እና በስደተኞች ላይ ከሕግ አግባብ ውጭ እየተፈጸመ ያለ እስር መኖሩንም ጠቁመዋል። አክለውም ስደተኞች እንደ ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር የሰብአዊ መብቶቻቸው ሊከበሩላቸው እንደሚገባ እና የሚደረግላቸው ጥበቃ እና ድጋፍም በሕግ አግባብ መሆን እንዳለበት ለዚህም ኢሰመኮ ድምጽ እንዲሆናቸው ጠይቀዋል።

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በመክፈቻ ንግግራቸው የስደተኞች ቀን የሚከበርበት ዓላማ ስደተኞች የሚያጋጥሟቸውን የተለያዩ ፈተናዎች ለማለፍ የሚያሳዩትን ጥንካሬ እና ቆራጥነት ለማሰብ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ዋና ኮሚሽነሯ በዚህ ዓመት “Hope Away From Home – A world where refugees are always included” (ከቤት ርቆ የሚታይ ተስፋ፤ ስደተኞች ሁሌም የተካተቱበት ዓለም) በሚል መሪ ቃል የስደተኞች ቀንን ስናከብር በተለይ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ የሚኖሩትን በርካታ ስደተኞች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን እንዴት ማጠናከር እንደሚቻል በማጤን ነው ብለዋል። አክለውም ኢሰመኮ በቀጣይ በተሰጠው ሥልጣን እና ኀላፊነት መሠረት በስደተኞች ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለተሳታፊዎች ገልጸዋል።