ራኬብ መሰለ
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚ
ሽነር

እ.ኤ.አ. በመስከረም 2021 ዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ባወጣው መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ 4.23 ሚሊዮን የሚሆኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ይገኛሉ፡፡ ይህ የተፈናቃዮች ቁጥር ዘላቂ መፍትሔ ሳያገኙ በተራዘመ የመፈናቀል ሁኔታ (Protracted displacement) ውስጥ የሚኖሩትንም ተፈናቃዮች የሚያካትት ነው። 3.5 ሚሊዮን (85%) የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ በመሆኑ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች እስካልቆሙ ድረስ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር ሊጨምር ይችላል።

የሀገር ውስጥ መፈናቀል የአጭር ጊዜ ችግር አይደለም፡፡ ይልቁንም መንግሥት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለማስገኘት ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎች ጋር የሚጣጣም የፖሊሲ እና የሕግ ማዕቀፍ መንደፍ፣ የሚመለከታቸው የዘርፍ አካላት ሁሉ መፈናቀልን አካተው እንዲሰሩ ግዴታ መጣልና በተለይም ይህንኑ በተቀናጀ የጎንዮሽና የተዋረድ አሰራር የሚያስፈጽም በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ ተቀባይነት ያለው አካል መሰየምና ማብቃት ይኖርበታል። በተጓዳኝ መፈናቀልን ለመከላከል እና ለተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል የሰው እና የገንዘብ ግብአት ከሰብአዊ ድርጅቶችና ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ጭምር መመደብ ያስፈልጋል፡፡

ዘላቂ መፍትሔ ማለት የተፈናቀሉ ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ተቋቁመው ሕይወታቸውን በመደበኛ ሁኔታ እና ከመድሎ ነጻ በሆነ ሁኔታ መኖር እስኪጀምሩበትና ጥበቃና ድጋፍ የማይፈልጉበት ሁኔታ እስኪደርሱ ድረስ ያለውን ሂደት ያካትታል፡፡ እንዲሁም ዘላቂ መፍትሔ ተፈናቃዮች ወደነበሩበት ቦታ በራሳቸው ሙሉ ፈቃድ እንዲመለሱ ወይም ሌላ አዲስ ቦታ እንዲሰፍሩ ወይም ከአካባቢ ማኅበረሰብ ጋር ተዋህዶ የመኖር አማራጮችን የሚያካትት ሲሆን፣ ዋነኛው የሰብአዊ መብት መመዘኛ በተፈናቃዮች ሙሉ ፍቃድ እና የማኅበረሰብ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነው፡፡

የተፈናቃዮች ፈቃድ ሳይገኝና ደኅንነታቸው ሳይጠበቅ ወደ ቀድሞ የመኖሪያ ቦታቸው መመለስ ወይም የሰፈሩበትን ጊዜያዊ መጠለያ ዘግቶ ተፈናቃዮችን መበተን ለመፈናቀል ችግር ዘላቂ መፍትሔ አያስገኝም፡፡ በሌላ በኩል ተፈናቃዮች ዜጎች እንደመሆናቸው በየትኛውም የሀገሪቷ አካባቢ ሄደው የመኖር መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል፡፡ በመሆኑም ተፈናቃዮችን በዘላቂ ሁኔታ ለማቋቋም ወደ ቀድሞ የመኖሪያ ቦታቸው መመለስ ብቸኛው አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡ 

እንደአግባቡ በሌላ ሦስተኛ (ወይም አዲስ) ቦታ ማስፈርን ወይም በተፈናቀሉበት ማኅበረሰብ ተዋህዶ መኖርን በአማራጭነት ማየት ያስፈልጋል፡፡ መፍትሔው ዘላቂ እንዲሆን ተፈናቃዮች ሕይወታቸውን በሰላም እና በተረጋጋ ሁኔታ ለመቀጠል እንዳይችሉ የሚያደርገው የደኅንነትና ጥበቃ ስጋት ሊቀረፍ ይገባል፡፡ ተፈናቃዮች የመጡበት ወይም የሚሰፍሩበት ቦታ ላይ የደኅንነት ስጋት ካለ ወይም ስጋቱ ካልተቀረፈ እዛ ቦታ ለመመለስ ወይም ለማረፍ ፈቃደኛ እንዲሆኑ ሊጠበቅባቸው አይገባም፡፡ 

ዘላቂ መፍትሔ በሚመቻችበት ወቅት የተፈናቃዮች የመኖሪያ፣ መሬትና ንብረት ጉዳይ ሊታይ ይገባል። ተፈናቃዮች ወደ መደበኛ መኖሪያ ቦታቸው ለመመለስ ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች መካከል ዋነኛው በመፈናቀል ሂደት የመኖሪያ ቤታቸው፣ እና ሌሎች ንብረቶቻቸው መቃጠላቸው፣ መውደማቸው ወይም ለጥቅም ማዋል እንዳይቻል ሆኖ መበላሸታቸው ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ መኖሪያ ቤታቸውና መሬታቸው በሕገ ወጥ መንገድ በሌላ ሰው ተይዞ ወይም ወደሌላ ሰው ተላልፎ ያገኙታል፡፡ ቤታቸውንና መሬታቸውን ለማስመለስ አስፈላጊው የባለቤትነት ምዝገባና ማስረጃ ለማግኘትም የሚቸገሩበት ሁኔታ አለ፡፡ በሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ በሚደረግበት ወቅትም የመኖሪያ ቦታ ለማግኘት የገንዘብ አቅማቸው አነስተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ተፈናቃዮች ለመቋቋምና ራሳቸውን ለመቻል ሥራ፣ መተዳደሪያ፣ ገቢ ማስገኛ እና የማኅበራዊ ዋስትና ዕድሎች ሊፈጠሩላቸው ይገባል፡፡ 

ይህንንና መሰል ችግሮችን የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት እንደአስፈላጊነቱ እና አግባብነቱ የገንዘብ እርዳታ ወይም ካሳ፣ እንዲሁም ከንብረት ባለቤትነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ግጭቶችን ለመፍታት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ቀለል አሰራሮችን መንደፍ ያስፈልጋል፡፡

በሌላ በኩል ትምህርት ቤቶች በወደሙበት ወይም ለተፈናቃዮች ጊዜያዊ መጠለያ ሆኖ እንዲያገለገሉ በተደረጉበት ሁኔታ፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና መምህራን በሌሉበት ወይም ትምህርት ቤቶች ተጨማሪ ተማሪዎች የመቀበል አቅም ከሌላቸው የሕጻናትና ወጣት ተፈናቃዮችን የመማር መብት ማስከበር አዳጋች ነው። ስለሆነም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ተፈናቃዮች ባሉበት አካባቢያዎች ትምህርት የሚያገኙበት ሁኔታ የሚመቻችበት፣ የትምህርት ተቋማት በአፋጣኝ የሚገነቡበት፣ ለመምህራን እገዛ የሚደረግበት እንዲሁም የሕጻናትና ወጣት ተፈናቃዮችን የመማር መብት ያማከለ ድጋፍ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡      

ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከሚያስፈልጉ መስፈርቶች መካከል የማኅበረሰብ ሆስፒታሎችና የጤና ኬላዎች፣ ውሃና የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎቶች የመሳሰሉትን የመሰረተ ልማትና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ተደራሽነት ነው። ተፈናቃዮችን እንደዚህ አይነት አገልግሎቶችና መሰረተ ልማት በሌሉበት ቦታ እንዲሰፍሩ ማድረግ ለዳግመኛ መፈናቀል (secondary displacement) ይዳርጋል፤ ከተቀባይ ማኅበረሰቡ ጋርም የሚኖረውን ግንኙነት አስቸጋሪ ያደርገዋል፤ ብሎም ለቀጣይ ግጭትም ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም ሁሉንም ማኅበረሰብ ያካተተ፣ ልማትን መሰረት ያደረገ መሰረተ ልማቶችና አገልግሎቶችን ማጠናከር አስፈላጊ ነው፡፡ 

ይህንን ለማሳካት የልማት፣ የደኅንነት እና የአደጋ መከላከልና የአስተዳደር አካላትን ከጅምሩ በመልካም አስተዳደር፣ መሰረተ ልማት፣ ማኅበራዊ ትስስር፣ ደኅንነት እንዲሁም የአደጋ መቀነስ ስራዎች ውስጥ በአግባቡ ማሳተፍ ይገባል፡፡ እንዲሁም ሴቶችን፣ ሕጻናትን፣ የአካል ጉዳተኞችን፣ አረጋውያንን ጨምሮ፤ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ፍላጎቶች ያማከለ መፍትሔ ሊቀረጽ ይገባል፡፡

በኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ከሚመለከቱ የሕግ ማዕቀፎች መካከል አንዱ በአዋጅ ቁ. 1187/2012 የጸደቀውና በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን ለመጠበቅና ድጋፍ የማድረግ ወይም የካምፓላ ስምምነት ተብሎ የሚታወቀው የአፍሪካ ሕብረት ስምምነት ነው። ይህንን ስምምነት የማስፈጸም እና የመከታተል ኃላፊነቱ ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሰላም ሚኒስቴር ተሰጥቷል (አዋጅ ቁጥር 1187/2012 አንቀጽ 4)፡፡

ሆኖም ግን ሕጉ እንዲተገበር አሁንም ሊከናወኑ የሚገቡ ሥራዎች አሉ። በአንድ በኩል የካምፓላ ስምምነት አባል መንግሥታት በስምምነቱ ውስጥ ከተካተቱ ግዴታዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ መፈናቀልን ለመከላከል፣ የተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ እንዲሁም ዘላቂ መፍትሔን በተመለከተ ብሔራዊ ሕግ ማውጣት እንዳለባቸው ባስቀመጠው ግዴታ መሰረት (አንቀጽ 2 (ሀ)) ይህንን አይነቱን ሕግ በአስቸኳይ ሊቀረጽና ሊጸድቅ ይገባል።   

በተጨማሪም በመፈናቀል ሁኔታ ያሉ ሰዎች የተለያዩ ፍላጎቶች ስላሏቸውና ድጋፍ ስለሚያስፈልጋቸውና መንግሥት አስፈላጊውን እና ሁሉን አቀፍ ጥበቃና ድጋፍ ለማቅረብ እንዲችል የሚመለከታቸውን የዘርፍ አካላት ሁሉ በተቀናጀ እና በተባበረ ሁኔታ ማሰራት አለበት፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ተፈናቃዮች የሚያስፈልጋቸውን የጥበቃና ድጋፍ አገልግሎት በእድሜ፣ በጾታ፣ በአካል ጉዳት ዓይነት፣ ወዘተ ለይቶ ማወቅ፣ መሰነድና ማስተናገድ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት የሚሰጡ የተለያዩ አገልግሎቶችን በተቀናጀ መልኩ እንዲቀርቡ የሚያደርግና ይህንኑ ለማስፈጸም ተገቢው ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው መንግሥታዊ አካል ሊኖር ይገባል፡፡ 

የሀገር ውስጥ መፈናቀል ውስብስብ ችግርና ዘርፈ ብዙ እርምጃዎች የሚፈልግ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትን ቁርጠኝነትና የተቀናጀ ድጋፍ ይጠይቃል፡፡ የሀገር ውስጥ መፈናቀልን በተቀናጀ መልኩ ማስተዳደር ማንንም ሰው ላለመተው (leave no one behind) የሚያልሙትን ዘላቂ የልማት ግቦች (Sustainable Development Goals) ለማሳካት አስተዋጽዖ ያደርጋል፡፡