ጥር 13 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጥበቃ በተመለከተ የተካሄደው የምክክር መድረክ ቁልፍ መንግስታዊ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሲሆን፣ በዋነኝነት የእነዚህን አካላት ሚና እና ኃላፊነት፣ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ያሉ የሕግ ማዕቀፎችን እና አሰራሮችን በዝርዝር ተመልክቷል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር “የምክክር መድረኩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን መብቶች ለማስጠበቅና መብቶቻቸው መከበራቸውን ለማረጋገጥ የሚረዱ ዓለምአቀፍ የሕግ ማዕቀፎች እንዲጸድቁ፣ እንዲተገበሩና ተመጣጣኝ ተቋማዊ መዋቅሮች እና አሰራሮች እንዲዘረጉ የሚያደርገው ጥረት አካል እንደሆነ” አስረድተዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ

የሰላም ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ እንዲሁም የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ተወካዮች የተሳተፉበት ይህ መድረክ በተለይም የእነዚህ መስሪያ ቤቶች በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ዙርያ ያላቸውን ሚናና ኃላፊነት ላይ ከሚደረጉ የባለሙያና የከፍተኛ ኃላፊዎች ውይይት የመጀመሪያው መሆኑ ተገልጿል። በዚሁ ስብሰባ ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም. ባጸደቀችው የካምፓላ ስምምነት መሰረት የገባችውን ግዴታዎች ከግምት ውስጥ በመክተት ተፈናቃዮች በቅድመ-መፈናቀል፣ በመፈናቀል እና በድኅረ-መፈናቀል ወቅት ጥበቃ እና ድጋፍ የማግኘት መብታቸውን የሚያረጋግጡ ተቋማዊ መዋቅሮች እንዲዘረጉ ለማድርግ ውይይት ተካሂዷል።

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ

በተጨማሪም ከተፋናቃዮች መብቶች አጠባበቅ ጋር በተገናኘ ልምድ ካላቸው መንግስታዊ ተቋማት ሙያተኞች ጋር በመምከር፣ በሕጎችና ተቋማዊ መዋቅሮች እንዲሁም አሰራሮች ዙሪያ ያሉ ክፍተቶች ለመለየት ውይይት ተደርጓል። የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በዝግጅቱ ማብቅያ ባደረጉት ንግግር እነዚህን ቀጣይነት ያላቸው የውይይት መድረኮችን መሰረት በማድረግ በአጭር እና በረጅም ጊዜ የሚከናወኑ ተግባራት እንደሚለዩና የስራ ክፍፍል እንደሚደረግ ገልጸዋል።