የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከኢንተርናሽናል ሚዲያ ሰፖርት (International Media Support) ጋር በመተባበር የመገናኛ ብዙኃንና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን አስመልክቶ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን እና የመገናኛ ብዙኃን፣ የሙያ ማኅበራትና ሌሎች የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮችን ያሳተፈ የውይይት መድረክ ታኅሣሥ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሄደ።

በመድረኩ በኢትዮጵያ ስላለው የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት፣ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ እና የመረጃ ተደራሽነት መብቶች አተገባበር፣ ስለ ጋዜጠኞች እና የማኅበረሰብ አንቂዎች አሁናዊ ሁኔታ፣ ሐሰተኛ መረጃን እና የጥላቻ ንግግሮችን ጨምሮ እያጋጠሙ ስላሉ ተያያዥ ተግዳሮቶች እና ስለ መፍትሔዎቻቸው ውይይት ተደርጓል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ሐሳብን በነጻነት የመያዝና የመግለጽ መብትን እንዲሁም የመረጃ ተደራሽነትን ከማስፋፋት፣ ከማስከበር እና ከማስጠበቅ አንጻር ስላላቸው ድርሻ እና በትብብር ሊያከናውኗቸው ስለሚገቡ ተግባራት የተወያዩ ሲሆን፤ ለዚህም ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮችን ለይተው የመፍትሔ ሐሳቦችን አስቀምጠዋል። ተመሳሳይ የውይይት መድረኮችን በየጊዜው በማዘጋጀት የሚስተዋሉ መሻሻሎችን እና ተግዳሮቶችን በማሳየት የውትወታውን ሥራ ማጠናከር ተገቢ መሆኑን ሐሳብ አቅርበዋል። ተሳታፊዎች የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን በየተቋሞቻቸው ለመተግበር እና በትብብር የሚከናወኑ ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት የሚወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢሰመኮ የሲቪል የፖለቲካ እና የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል እና የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ ሐሳብን መያዝና መግለጽ የሰው ልጅ ተፈጥሮ መሆኑን ጠቅሰው ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ተግባራዊነት መሠረት እንዲሁም ለሌሎች ሰብአዊ መብቶች በተለይም በሕዝባዊ ጉዳዮች የመሳተፍ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብቶችን እውን ለማድረግ ወሳኝ ነው ብለዋል። “በኢትዮጵያ መብቱን ለመተግበር የሕግ ማዕቀፍ መዘርጋቱ እና ከ2010 ዓ.ም. በፊት በአንዳንድ ድረ ገጾች እና መገናኛ ብዙኃን ላይ የነበረ ክልከላ መነሳቱ እንደ አወንታዊ እርምጃ የሚጠቀስ ቢሆንም ሐሳብን በነጻነት የመያዝና የመግለጽ መብትን ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል” ብለዋል። ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አክለውም መብቱን ለማረጋገጥ ካጋጠሙ ተግዳሮቶች መካከል የሕግ አተገባበር ክፍተቶች፣ የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥ እና የሚድያ አዋጁን የሚጻረር የጋዜጠኞች እስራት ኢሰመኮ በሐምሌ 2015 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ላይ በአሳሳቢነት የተጠቀሱ መሆናቸውን አሰታውሰዋል።