የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በእስር ላይ የሚገኙትን እና የሚድያ አባላት የሆኑትን የክብሮም ወርቁ፣ የታምራት ነገራ፣ የመዓዛ መሃመድ እና  የእያስፔድ ተስፋዬን  ጉዳይ ለማጣራት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ገልጿል፡፡ ይሁንና በተለይም ታምራት ነገራ በፖሊስ ከተያዙበት ከታኅሣሥ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ፣ እንዲሁም  ከጥቅምት 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር የቆዩት ክብሮም ወርቁ በኅዳር 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ከተፈቀደላቸው ጊዜ ጀምሮ ኢሰመኮ ይህን መግለጫ እስካወጣበት ጊዜ ድረስ የተያዙበት ቦታ ለቤተሰቦቻቸው ባለመነገሩ የቤተሰብ ጥየቃ መብታቸው ያልተከበረላቸው ከመሆኑም በላይ ያሉበት ሁኔታ አለመታወቁ ኮሚሽኑን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳስበው ነው። በአስቸኳይ ግዜ ሁኔታም ውስጥ ቢሆን ታሳሪዎች ያሉበት ሁኔታ ሊታወቅና በቤተሰብ እና በሕግ አማካሪ የመጎብኘት መብቶች ሊጣሱ አይገባም፡፡

ስለሆነም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ሁለቱም ታሳሪዎች የሚገኙበትን ቦታ በአስቸኳይ ለቤተሰቦቻቸው እና ለሕግ አማካሪያቸው እንዲያሳውቁና በቤተሰቦቻቸው የመጎብኘት መብታቸውን እንዲያረጋግጡ ኮሚሽኑ በጥብቅ ያሳስባል። ኮሚሽኑ አያይዞም የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የሰብአዊ መብቶችን መርሆች ባከበረ መልኩ መተግበሩን የሚመለከታቸው አካላት በቅርብ ሊከታተሉ እና ሊያረጋግጡ እንደሚገባ ያስተላለፈውን ጥሪ በድጋሚ አስታውሷል።