የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በኢትዮጵያ የሥራ ፍልሰት አስተዳደርና በፍልሰተኛ ሠራተኞች መብቶች ማስፋፋትና ጥበቃ ላይ መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል። በውይይቱ የሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል የመንግሥታት ተቋማት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች፣ የውጭ ሀገር ሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች ማኅበራትና ፌዴሬሽን እንዲሁም የፍልሰት ተመላሾች ማኅበራት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በውይይቱ ሰብአዊ መብቶችን ማእከል ያደረገ የሠራተኛ ፍልሰት አስተዳደር ምንነትና ጠቀሜታው፣ እንዲሁም በብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ሚና ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል። ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ የሠራተኛ ፍልሰት አስተዳደር ፍልሰተኞችን ጨምሮ ሁሉም ሰዎች የሰብአዊ መብቶች አሏቸው በሚል መነሻ ላይ እንደሚመሠረት ተገልጿል። በዘርፉ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ የፍልሰተኞችን ሰብአዊ መብቶች ማእከል ያደረገ ሲሆን ለፍልሰተኞቹ፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለመጡበት ማኅበረሰብ፣ ለመነሻ ሀገር እንዲሁም ለመድረሻ ሀገራት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደአለው ተብራርቷል። ኢትዮጵያ በርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶችን ያጸደቀች ቢሆንም የፍልሰተኛ ሠራተኞችንና የቤተሰቦቻቸውን መብቶች ለመጠበቅ የተደረገውን ዓለም አቀፍ ስምምነት፣ የአፍሪካ ኅብረትን የፍልሰት ፖሊሲ ማዕቀፍ መሠረት አድርጎ ከሁለት ዓመታት በፊት የተረቀቀውን ብሔራዊ የፍልሰት ፖሊሲ እንዲሁም  ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ያወጣቸውን ለዚህ ጉዳይ አግባብነት ያላቸው ስምምነቶች አለማጽደቋ በፖሊሲ እና በሕግ ማዕቀፍ ያሉ ክፍተቶች እስካሁን አለመቀረፋቸውን እንደሚያመለክት ተጠቁሟል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በውይይቱ የኢሰመኮ የስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችና የፍልሰተኞች መብቶች ሥራ ክፍል በኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት በተሰማሩ ኤጀንሲዎች ላይ በማተኮር ከኅዳር 7 እስከ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ባደረገው የሰብአዊ መብቶች ክትትል የለያቸው ግኝቶች እና የሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል። ለአብነትም ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የሥራ ስምሪት ስምምነት ወደ ተፈራረመችባቸው ሀገራት ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በመደበኛ መንገድ በአጠቃላይ 104,861 ፍልሰተኛ ሠራተኞች ወደ ውጭ ሀገራት እንደሄዱ ከዚህም ውስጥ ለወንዶች የተፈጠረው የሥራ ዕድል 362 (0.34 በመቶ ብቻ) ሲሆን፣ ከሚሄዱት ፍልሰተኛ ሠራተኞች ውስጥ ከ97 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ለቤት ሠራተኝነት የሄዱ እና የአብዛኞቹ መነሻ አማራ፣ ኦሮሚያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ክልሎች መሆናቸው ተገልጿል።

በተጨማሪ በውይይት መድረኩ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር በአሁኑ ወቅት መንግሥት ፈቃድ የሰጣቸው 1278 የውጭ ሀገር የሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች በአዲስ አበባ ከተማ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውንና 585 የሚሆኑ ኤጀንሲዎች በክልል ደረጃ ጽሕፈት ቤት ከፍተው አገልግሎት እንዲሰጡ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል። የውጭ ሀገር የሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች ማኅበራት፣ የተመላሾች ማኅበራት፣ የዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት፣ የዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት እና የተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ድርጅት (UN WOMEN) ተወካዮች በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ዘርፍ ስላላቸው ሚና፣ በኢትዮጵያ እየተገበሩ ስላሏቸው ሥራዎች እንዲሁም በዘርፉ ስለሚመለከቷቸው ክፍተቶች እና የማስተካከያ እርምጃዎች አጫጭር ማብራሪያ አቅርበው ውይይት ተደርጓል።

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ

በውይይቱ ሰዎች ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር ከመሄዳቸው በፊት ተቀጥረው ለሚሠሩበት የሥራ መስክ አስፈላጊውን ዕውቀትና ክህሎት ይዘው ቢሄዱ ከበርካታ መሰናክል ሊጠበቁ ስለሚችል የዳበረና ውጤታማ ስልጠና በአግባቡ ሊሰጥ እንደሚገባ አብዛኞቹ ተሳታፊዎች ያነሱት ጉዳይ ነው። በተጨማሪም አስቀድመው በተጀመሩ መልካም ጅምሮች ላይ በመመሥረት፣ በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የቅንጅት አሠራርን በማጠናከር ስለመደበኛ ፍልሰት በቂ መረጃ በማሰራጨት፣ የመደበኛ ፍልሰት መንገዶችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ፣ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን እንዲሁም በሰዎች የሚነግዱትን በሕግ ተጠያቂ በማድረግ፣ የፍልሰተኛ ሠራተኞች መብቶች አጠባበቅ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል ጥረቱ መቀጠል እንዳለበት የውይይቱ ተሳታፊዎች ተስማምተዋል።

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በበኩላቸው ወደ ውጭ ሀገራት የሚደረግ የሥራ ፍልሰት ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ መደበኛና በሥርዓት የሚመራ (safe, regular and orderly) ሲሆን ፍልሰተኞች በተሟላ መረጃ ላይ ተመርኩዘው ጥሩውን እና ክፉውን ለይተው መደበኛ የሆኑ የፍልሰት መንገዶችን ተጠቅመው እንዲጓዙ፣ ከሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጠብቀውና ባሰቡት ልክ የራሳቸውን እና የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት ለማሻሻል እንዲሁም ሀገር በውጭ ምንዛሪ እንድትጠቀም ማድረግ የሚችሉበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት እንደሚችል አመላክተዋል። አክለውም በአሁኑ ወቅት መንግሥት በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ዕድል እየፈጠረ ቢሆንም በአንጻሩ መደበኛ ባልሆኑት መንገዶች የሚፈልሱ ሰዎች ቁጥርም በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ መሄዱ በአግባቡ ሊጠናና የማስተካከያ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባው፣ እንዲሁም ለውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እየተደረጉ ያሉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች የሠራተኞችን ሰብአዊ መብቶች ማእከል አድርገው መቀረጽ እንዳለባቸው አሳስበዋል።