የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መግለጫ

ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም.

የሰብአዊ መብቶች ትምህርት በመደበኛ ትምህርት ሥርአተ-ትምህርት ውስጥ በአግባቡ ሊካተት ይገባል

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) የሰብአዊ መብቶች ትምህርት በመደበኛ ትምህርት (አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች) ሥርአተ-ትምህርት ውስጥ በአግባቡ ሊካተት እንደሚገባ አሳሰበ። ኮሚሽኑ ይህን ያመለከተው በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ትምህርት አሰጣጥን በተመለከተ ባከናወነው ባለ 55 ገጽ የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት ላይ ነው። የዳሰሳ ጥናቱ የተከናወነው ሰብአዊ መብቶችን የማክበር ባህል የዳበረበት ማህበረሰብ ለመፍጠር የሰብአዊ መብቶች ትምህርት በመደበኛ ትምህርት ስርአተ-ትምህርት ውስጥ ማካተት ያለውን ከፍተኛ አስተዋዖ ታሳቢ በማድረግ ነው። በጥናቱ አግባብነት ያላቸው ሕጎች፣ ፖሊሲዎችና የስትራተጂ ሰነዶች እንዲሁም ስርአተ-ትምህርቶች ዳሰሳና ትንተና ተከናውኗል። በተጨማሪም፥ በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ትምህርት አሰጣጥ ተግባራዊ ሁኔታን ለመረዳት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከተመረጡ ሶስት ክልሎች የተሰበሰቡ መረጃዎች ትንተና አከናውኗል።

በዳሰሳ ጥናቱ ግኝት መሰረት፥ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት በመደበኛ ትምህርት ስርአት ውስጥ ለማካተት የተደረገ ጥረት ቢኖርም፥ በተሰጠው ሽፋን፣ በአቀራረፁ እና በአቀራረቡ ብዙ ውስንነቶች ያሉበትና የሰብአዊ መብቶች ግንዛቤ፤ እሴቶቸንና መርሆዎችን በተማሪዎች ዘንድ ለማስረፅ የሚያስችል አይደለም። በትምህርት ዘርፍ ተቋማት መዋቅርና አሰራር ለሰብአዊ መብቶች ትምህርት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን፤ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት በሥነ-ምግባርና ሥነ-ዜጋ ትምህርት ለማካተት የተሞከረ ቢሆንም በተገቢው ስፋትና ጥልቀት አለመሆኑና በየደረጃው የሚሰጡ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት አርዕስቶች ተደጋጋሚነት እንዲሁም ተማሪዎች በየትምህርት ቤቶቻቸው ውስጥ የሰብአዊ መብቶች አተገባበርን እያዩ እዲማሩ የሚያስችሉ አሰራሮች አለመኖር ዋናዋናዎቹ ችግሮች ናቸው። በመሆኑም፥ በትምህርት ዘርፍ የሚሰሩ የፌደራል እና የክልል መንግስታት ተቋማት፣ ስራቸው ሰብአዊ መበቶችን ማስፋፋትና ማስከበር ላይ ያተኮረ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና የምርምርና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰብአዊ መብቶች ትምህርት በመደበኛ ትምህርት ስርአተ-ትምህርት ውስጥ በአግባቡ እንዲካተት የየበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የዳሰሳ ጥናቱ ምክረ-ሃሳብ ያመለክታል።

በኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት ዳይሬክተር አቶ መብራቱ ገበየሁ “የሰብአዊ መብቶች ትምህርት በመደበኛ ትምህርት ስርአተ-ትምህርት ውስጥ ማካተት ሰብአዊ መብቶችን ማክበር እና ማስከበር የሚችል ማህበረሰብ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው፤ በመሆኑም በዳሰሳ ጥናቱ የተመለከቱትን ምክረ-ሃሳቦች ባለ ድርሻ አካላት በተናጠልም በጋራም በመተግበር የሰብአዊ መብቶች ትምህርት በመደበኛ ትምህርት ስርአተ-ትምህርት ውስጥ በአግባቡ ተካቶ እንዲሰጥ ማድረግ ይገባል” ብለዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢሰመኮ ለባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ሙያዊና የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የገለፁት አቶ መብራቱ፤ “ኮሚሽኑ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በስትራቴጂክ እቅዱ አካትቶ እየሰራበት ነው” ብለዋል።

የዳሰሳ ጥናቱ ሪፖርት ከዚህ መግለጫ ጋር ተያይዟል።

የሪፖርቱን ኮፒ በአድራሻዎ እንዲላክልዎት ከፈለጉ ከዚህ ቀጥሎ በተመለከተው የኢሜል አድራሻ ይጠይቁ።

nigusie.gerie@ehrc.org