የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብቶች ማእከል ጋር በመተባበር የሲቪል ማኅበራት ከአፍሪካ የሰዎች እና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን (African Commission on Human and Peoples’ Rights) ጋር ጠንካራ እና ውጤታማ የሥራ ግንኙነት እንዲኖራቸው ለማስቻል፤ እንዲሁም የአፍሪካ የሰዎች እና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር አተገባበርን አስመልከቶ ለኮሚሽኑ በሚቀርበው ወቅታዊ የመንግሥት ዘገባና የኮሚሽኑ የግምገማ ሂደት ውስጥ የሲቪል ማኅበራት ያላቸውን ሚና ለማስገንዘብ ያለመ አውደ ጥናት ነሐሴ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. አዘጋጅቷል። 

ዝግጅቱ በኢትዮጵያ የተመዘገቡ የሲቪል ማኅህበረሰብ ድርጅቶች ከአፍሪካ የሰዎች እና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን ጋር ጠንካራና ውጤታማ ግንኙነት እንዲኖራቸው ያለመ ነው። በተለይም የእነዚህ ማኅበራት ሚና ለኮሚሽኑ በሚቀርበው መንግሥታዊ የአፈጻጸም ዘገባ ሂደት ውስጥ ምን እንደሚመስል ግንዛቤ ለማስጨበጥ ታቅዶ የተሰናዳ አውደ ጥናት ነው። በአውደ ጥናቱ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩ በርካታ የሲቪል ማኅበራትን እንዲሁም የኢሰመኮ፣ የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብት ማእከል፣ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለሞያዎችን ተሳትፈውበታል።

አውደ ጥናቱ መንግሥታዊ ዘገባዎች በወቅቱ እንዲቀርቡ ከመወትወት እና በሰብአዊ መብቶች ስምምነት ከተቋቋሙ አካላት (treaty bodies) የሚሰጡ ምክረ ሃሳቦችን አፈጻጸም ከመከታተል አንጻር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ያላቸውን ልዩ ሚና አጉልቶ አሳይቷል። በመድረኩ ለተሳታፊዎች በአማራጭ የሰብአዊ መብቶች አተገባበር ዘገባዎች (alternative/shadow report) አቀራረብ መመሪያዎች ዙሪያ ግንዛቤ የፈጠረ ከመሆኑም በላይ ተሳታፊዎች በተጨባጭ የዘገባ ዝግጅቱን አስመልክቶ ተግባራዊ ልምምድ እንዲያደርጉ ዕድል አመቻችቷል።

የኢሰመኮ የሴቶች እና ሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶቸ ሁኔታ ላይ ተአማኒ እና በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ መረጃዎችን ለዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች አካላት ለማቅረብ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል። አክለውም መንግሥታዊ ዘገባዎችን ለማዘጋጀት በመንግሥት፣ በሲቪል ማኅበራት እና በኢሰመኮ መካከል ቅንጅት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ማኅበራቱ እና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት አማራጭ ዘገባዎችን (alternative/shadow reports) በሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ለተቋቋሙ አካላት (treaty bodies) የማቅረብ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል። ኮሚሽነር መስከረም በኢትዮጵያ የተመዘገቡ የሲቪል ማኅበራት ከአፍሪካ ኮሚሽን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር በኮሚሽኑ የታዛቢነት መቀመጫ (observer status) እንዲጠይቁም መክረዋል።

አውደ ጥናቱ የሲቪል ማኅበራት ያላቸውን ዕድል በመጠቀም ከአፍሪካ የሰብአዊ መብቶች አካላት ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ፣ በመንግሥት የሰብአዊ መብቶች አተገባበር ዘገባዎች ዝግጅት ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ፣ አማራጭ ዘገባዎችን እንዲያቀርቡ፣ በሰብአዊ መብቶች አካላት የሚሰጡ ምክረ ሃሳቦችን ወደ ሀገራዊ ቋንቋዎች ተርጉመው እንዲያሰራጩ፤ እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች አፈጻጸምን እንዲከታተሉ አቅጣጫ በመስጠት ተጠናቋል።