የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰብአዊ ክብር፣ ነጻነት እና ፍትሕ ለሁሉም በሚል መሪቃል የሚከበረውን የዘንድሮ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን ታሳቢ በማድረግ ሰብአዊ ክብር፣ ነጻነት እና ፍትሕ ለሕፃናት እና ለሴቶች በሚል ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ታኅሣሥ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. በኮሚሽኑ ዋና ቢሮ ከፌዴራል መንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ተቋማት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢሮዎች እና በአዲስ አበባ ከሚገኙ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቢሮዎች የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ምክክር አድርጓል። 

የምክክር መድረኩ የተዘጋጀው በኮሚሽኑ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት የቀረቡ ምክረ-ሃሳቦችን ለባለግዴታዎች ተደራሽ በማድረግ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኙ ለማስቻል፣ ባለግዴታ አካላት በዋና ዋና የመብቶች ጥሰት እና አሳሳቢ ጉዳዮች ዙሪያ ግንዛቤያቸው እንዲጎለብት፣ ከመድረኩ የሚገኙ ሃሳቦችን በማደራጀት መንግሥት ለጉዳዩ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው ለመወትወት፣ በኮሚሽኑ የቀረቡ ምክረ-ሃሳቦች አተገባበር ላይ ለመወያየትና አፈጻጸሙን በተመለከተም ቀጣይነት ያለው የክትትል እና የትብብር ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ትስስርን ለማጎልበት ነው፡፡ 

በዓመታዊ ሪፖርቱ በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል በተነሳው ጦርነት ሳቢያ በሴቶች እና በሕፃናት ላይ መጠነ ሰፊ እና ለጦርነት ዓላማ ስልታዊ በሆነ መልኩ ለተፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶች ውጤታማ መፍትሔ የሚያስገኝ የተሟላ የሕግ፣ የወንጀል ምርመራና የክስ አመሠራረት ሥርዓት መጓደል፣ ነጻና ለሁሉም ተደራሽ የሆነ የልደት ምዝገባ አሠራር በሕግ አለመደንገጉ፣ ሕፃናት ሃሳባቸውን በነጻ የመግለጽና በሚመለከታቸው ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ የማድረግ መብታቸውን ለመተግበር የሚያስችል ወጥ ሕግ አለመኖር እንዲሁም በአፋርና ሱማሌ ክልል የሕፃናትና የሴቶች መብቶችን የሚያስጠብቅ የቤተሰብ ሕግ አለመውጣቱ ዋና ዋና የሕግና የፖሊሲ ክፍተቶች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡  

በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ሴቶች አያያዝ አነስተኛውን መስፈርቶችን ያሟላ አለመሆኑ፣ ከእናቶቻቸው ጋር በእስር ቤት የሚቆዩ ሕፃናት የትምህርትና አማራጭ እንክብካቤ የማግኘት መብቶች መጓደላቸው በሪፖርቱ ከተካተቱ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ በሚያልፉ ሴቶች እና ሕፃናት ላይ ከተፈጸሙ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ከጥቃትና ብዝበዛ የመጠበቅ መብትን በተመለከተ የሴቶችና የሕፃናት ሕገ-ወጥ ዝውውር መበራከት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች እና ሕፃናት መፈናቀላቸው እና በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች እና አካባቢዎች ውስጥ ለጾታዊ ጥቃቶች እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተጋላጭ መሆናቸው እና ልዩ ፍላጎታቸውን መሠረት ያደረጉ በቂ፣ ተደራሽና ወቅቱን የጠበቁ የሰብአዊ ድጋፎች አለማግኘታቸው በምክክር መድረኩ ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት በዓለም አቀፍ የወንጀል ድርጊት የደረሱ ጉዳቶችን ለመጠገን ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ ተገቢው የካሳና የተሐድሶ ማዕቀፍ አለመኖሩ፣ ከሰሜኑ ጦርነት እና በሌሎች ቦታዎች ከተቀሰቀሱ ግጭቶች ጋር በተያያዘ ጾታዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ተጎጂዎች የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ በሁሉም የግጭት ቦታዎች እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ባሉባቸው ቦታዎች ላይ አለመተግበራቸው እና የአንድ ማዕከል መመሪያ ሰነድ በግጭት ወይም በሌሎች ያልተገመቱ ሁኔታዎች ውስጥ ጭምር ሥራ ላይ ሊውል በሚችል መንገድ አለመቀረጹ ለውይይት ከቀረቡ ጉዳዮች መካከል ናቸው።  

በተጨማሪም በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በኩል ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ እንዲካተቱ እና እንዲሳተፉ ለማድረግ ጥረቶች መጀመራቸው የሚበረታታ ቢሆንም ለውይይት የሚመረጡ ርዕሰ ጉዳዮች የሴቶችን ድምጽ እና የሴቶች መብቶችን በአግባቡ እንዲያካትቱ፣ ሴቶች በምክክር ሂደቱ ተሳትፏቸው ትርጉም ያለው እንዲሆን፣ የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸው እንዲሰፋ በየደረጃው መዋቅሮችን ለመዘርጋት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅበት እንዲሁም በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚሠሩ ሴት ሠራተኞች መሠረታዊ መብቶች ጥሰት መቀጠል ምክከር የተደረገባቸው ሌሎች ጉዳዮች ናቸው፡፡  

በዝግጅቱ ወቅት የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ለተሻሻለ የሰብአዊ መብቶች አተገባበር ከባለግዴታዎች ጋር የሚደረግ ይህን መሰል የምክክር መድረክ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ የሕፃናትና የሴቶች መብቶች ጉዳይ የሁሉም ኃላፊነት በመሆኑ ለኮሚሽኑ ግኝቶች እና ምክረ-ሃሳቦች ተገቢውን ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል በማለት አሳስበዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በተከሰቱት ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ሕፃናት ከመንግሥት፣ ከማኅበረሰብ እና ከቤተሰብ ማግኘት ያለባቸው ጥበቃ በመጓደሉ ለተደራራቢ የመብቶች ጥሰት መጋለጣቸውን እንዲሁም ሴቶች በደረሰባቸው ጾታዊ መድሎዎች እና በተፈጸሙባቸው ጾታዊ ጥቃቶች ምክንያት መሠረታዊ መብቶቻቸውን የሚጥሱ፣ ነጻነቶቻቸውን የሚገድቡና ሰብአዊ ክብራቸውን የሚያጎድፉ እንዲሁም ፍትሕን የሚያጓድሉ በደሎች የደረሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም “ባለግዴታ አካላት በሪፖርቱ የተለዩ አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ በቅንጅት በመሥራት ኃላፊነታውን ሊወጡ ይገባል” በማለት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡  

የኢሰመኮ የአረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ አክለው ኮሚሽኑ ይፋ በሚያደርጋቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሪፖርቶች ከሚቀርቡ ምክረ ሃሳቦች በተጨማሪ ከባለግዴታ አካላት ጋር በሚደረጉ መሰል የምክክር እና የጉትጎታ መድረኮች ላይ የሚሰጡ ምክረ-ሃሳቦችን ጭምር በመተግበር የመንግሥት አካላት ለሰብአዊ መብቶች አያያዝ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡ 

የውይይት መድረኩ የተሳተፉ ባለግዴታዎች በሕፃናት እና በሴቶች ሰብአዊ መብቶች እና አሳሳቢ የመብቶች ጥሰት ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኙ ምቹ አጋጣሚን ፈጥሯል። በተጨማሪም ተሳታፊዎች ባላቸው የኃላፊነት ደረጃ የራሳቸውን ግዴታ እንደሚወጡ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር እና ግፊት በማድረግ ለምክረ-ሃሳቦቹ ተፈጻሚነት እንደሚሠሩ አስታውቀዋል። 

በተመሳሳይ መሰል ምክክሮች በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት በባሕር ዳር፣ ሃዋሳ፣ ጅማ፣ ጅጅጋ እና ሰመራ የሚቀጥል ይሆናል።