የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በልዩ አዳሪ እና አካቶ ቅድመ መደበኛ፣ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን አስመልክቶ ከአዲስ አበባ፣ አምቦ፣ ባሕር ዳር፣ ቢሾፍቱ፣ ባኮ፣ ጋምቤላ፣ ሆሳዕና፣ መቐለ፣ ሰበታ እና ሻሸመኔ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ባከናወነው ክትትል የተለዩ ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሁለት የምክክር መድረኮች በአዲስ አበባ እና ሃዋሳ ከተሞች አካሂዷል።

በውይይት መድረኮቹ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ የማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ የጋምቤላ፣ የኦሮሚያ እና የሲዳማ ክልሎች ትምህርት ቢሮዎች፣ ጽሕፈት ቤቶች እና ክትትል የተደረገባቸው ትምህርት ቤቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል። ኢሰመኮ በአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የአዲስ አበባ እና የባሕር ዳር ከተሞች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ተመሳሳይ የውይይት መድረክ በመጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ማካሄዱ ይታወሳል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

የኦሮሚያ እና የጋምቤላ ክልል ተሳታፊዎች በተገኙበት ሚያዝያ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. በተካሄደ የውይይት መድረክ ኢሰመኮ በኦሮሚያ ክልል በአምቦ፣ ባኮ፣ ቢሾፍቱ እና ሰበታ እንዲሁም በጋምቤላ ክልል በተመረጡ ልዩ አዳሪ እና አካቶ ቅድመ መደበኛ፣ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ባከናወነው ክትትል የለያቸውን ግኝቶች ለውይይት አቅርቧል። የከባቢያዊ፣ ተቋማዊ፣ መረጃና ተግባቦት ክፍተት፣ የአመለካከት ችግሮች መኖር፣ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ለማስቻል ተደጋጋሚ የማኅበረሰብ ቅስቀሳ አለመደረግ እና በክልል እና በከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤቶች የሚደረጉ ድጋፍና ክትትሎች በቂ አለመሆን ከግኝቶቹ መካከል የተጠቀሱ ናቸው። በጋምቤላ ክልል ደግሞ ክትትል በተደረገባቸው ትምህርት ቤቶች ዐይነ ሥውራን ተማሪዎችን ማግኘት አለመቻሉ፣ የዐይናቸው የማየት ዐቅም ከቀነሰ ጥቂት ተማሪዎች በቀር ዐይነ ሥውራን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እየሄዱ ባለመሆኑ ለዐይነ ስውራን የመጣ የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ጥቅም ላይ ሳይውል ተከማችቶ መገኘቱን አረጋግጧል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

የምክክሩ ተሳታፊዎች የቀረቡት ግኝቶች በልዩ አዳሪ እና አካቶ ትምህርት ቤቶች ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚያንጸባርቁ እንደሆኑ እና ክፍተቶች መፍትሔ እንዲያገኙ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ኢሰመኮ በሲዳማ እና በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙ የተመረጡ ልዩ አዳሪ እና አካቶ ቅድመ መደበኛ፣ መጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ባከናወነው ክትትል ግኝቶች ዙሪያ ግንቦት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ውይይት አካሂዷል። ከተደራሽነት አንጻር በእነዚህ ክልሎች የተስተዋሉ ክፍተቶች ከኦሮሚያ እና ከጋምቤላ ክልል ግኝቶች ጋር ተመሳሳይነት እንዳላቸው ተገልጿል። የዚህኛው መድረክ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች የተዛባ አመለካከት ለክፍተቱ ዋነኛ ምክንያት ነው ብለው እንደሚያምኑ በመግለጽ በትምህርት ቤቶችም ሆነ በትምህርት ቢሮዎች አካባቢ በልዩ ፍላጎት ዘርፍ የሚሠሩ ባለሙያዎች የትምህርት ደረጃ ዝቅተኛ መሆን፣ አስፈላጊውን በጀት እና በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ለቦታው አለመመደብ የሚሉት ጉዳዮችን በማሳያነት አንስተዋል።

በሁለቱም መድረኮች ላይ ትኩረት የሚያሻቸው እና ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የማይተገበሩ ሁኔታዎች በሚል ከተነሱ ግኝቶች መካከል የጉዳት ዓይነትን መሠረት አድርገው የሚቋቋሙ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ተደራራቢ ጉዳት ያለባቸውን ተማሪዎች የማይቀበሉ መሆኑ፣ ሴት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሚያጋጥሟቸውን ተደራራቢ ተጋላጭነት መሠረት ያደረገ ልዩ ድጋፍ አለመኖር፣ እንደየጉዳት ዓይነታቸው ተማሪዎች የሚደርስባቸው የመብት ጥሰት ዓይነት እና ስፋት የሚለያይ መሆኑ፣ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ተማሪዎች የትምህርት መብታቸውን ለመጠቀም ከፍተኛ ተግዳሮት የሚገጥማቸው መሆኑ የሚሉት ይገኙበታል።

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ሜቲ አቶምሳ የውይይት መድረኩ የክትትል ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ከማስተዋወቅ ባሻገር አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ከጉዳት አልባ አቻዎቻቸው እኩል የትምህርት መብት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ዋና ዋና ክፍተቶችን በመለየት ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በር ከፋች ነው ብለዋል። አክለውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚቀላቀሉ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ቁጥር ማሽቆልቆሉን ከግምት በማስገባት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ብቁ ሆነው የሚቀርቡበትን ሥርዓት በመዘረጋት እንዲሁም አተገባበሩን በመከታተል ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።