የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በልዩ አዳሪ እና አካቶ ቅድመ መደበኛ፣ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አስመልክቶ ባከናወነው ክትትል የተለዩ ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ዙር ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ ላይ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ እና ባሕር ዳር ከተሞች የተውጣጡ ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል፡፡ ክትትሉ በአዲስ አበባ፣ በአምቦ፣ በባህር ዳር፣ በቢሾፍቱ፣ በባኮ፣ በጋምቤላ፣ በሆሳዕና፣ በመቐለ፣ በሰበታ እና በሻሸመኔ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች የተካሄደ ነው።

በውይይት መድረኩ በክትትሉ የተለዩ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን በትምህርት ወቅት የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች የቀረቡ ሲሆን ምንም እንኳን በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የተሻሻሉ ሁኔታዎች ቢኖሩም የትምህርት ቤቶቹ መማሪያ ክፍሎች፣ የአስተዳደር ቢሮዎች እንዲሁም የውስጥ እና የውጭ አካባቢ የተደራሽነት ክፍተት ያለባቸው መሆኑ፣ በአዲሱ የትምህርት ካሪኩለም መሠረት የተዘጋጁ የመማሪያ መጽሐፍት በምልክት ቋንቋ እና በብሬል ተተርጉመው አለመቅረባቸው እንዲሁም በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር ከተጠቀሱ ተግዳሮቶች መካከል ናቸው። በተጨማሪም በየትምህርት ዘርፉ የሰለጠነ የምልክት ቋንቋ ተናጋሪ አለመኖር፣ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚዎች በቁጥር አነስተኛ በመሆናቸው ተማሪዎች በሁሉም የትምህርት ክፍለ ጊዜ የትርጉም አገልግሎት አለማግኘታቸው እና ሴት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ለጾታዊ ጥቃት ተጋላጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚስተዋሉ መሆናቸው ትኩረት የሚሹ ግኝቶች ናቸው። የመንግሥትም ሆን የግል ትምህርት ቤቶች ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ያላቸው የተደራሽነት እና አካታችነት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑ ተጠቁሟል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በኢሰመኮ የቀረቡ ግኝቶች የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ እየፈጠሩ ያሉትን ጫና በተጨባጭ ያመላከቱ መሆናቸውን ገልጸው፤ በተለይም የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ከጉዳት አልባ አቻዎቻቸው እኩል ውጤታማ እንዳይሆኑ ማነቆ የሚፈጥሩ የተደራሽነት ክፍተቶችን ማስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል። የማስተካከያ እርምጃዎች በግለሰብ ወይም በኃላፊዎች ይሁንታ ላይ የተመሠረቱ መሆን የለባቸውም ብለዋል። በተጨማሪም ትምህርት ቤቶች አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ተመጣጣኝ ማመቻቸቶችን ማቅረብ እና አስፈላጊውን ድጋፍ ማግኘታቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው በውይይቱ ተነስቷል።

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ በበኩላቸው አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ለማካተት እና ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም ክትትሉ በተካሄደባቸው ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ የከባቢያዊ፣ የአመለካከት፣ የተግባቦት እና ተቋማዊ መሰናክሎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ አክለውም ክትትሉ የተካሄደባቸው ትምህርት ቤቶች በቁጥር ውስን ቢሆኑም መሰል ሁኔታዎች በበርካታ ትምህርት ቤቶች የሚስተዋሉ በመሆናቸው ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ሀገራዊ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።