የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን የሥራ ክፍል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የአካል ጉዳተኞች መብቶች ዓለም አቀፍ ስምምነት (UN Convention on the Rights of Persons with Disabilities) መከበር እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች አተገባበር ዙሪያ ሚያዚያ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. በጅማ ዞን አስተዳደር እና በጅማ ከተማ ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች ላይ የሚሠሩ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትና አካል ጉዳተኞች ማኅበራት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በጅማ ከተማ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም የአፍሪካ የሰብአዊና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር የአረጋውያን መብቶች ፕሮቶኮልን እና የአረጋውያን ብሔራዊ የድርጊት መርሐ ግብርን አተገባበር በተመለከተ ሥልጠና እና ጉትጎታ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል፣ ከሲዳማ ብሔራዊ ክልል እና ሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ አከናውኗል፡፡

በጅማ ከተማ በተካሄደው ዝግጅት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢሰመኮ ጅማ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በዳሳ ለሜሳ “ኢሰመኮ በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የተሟላ ሕዝባዊ ግንዛቤ በመፍጠር፣ በመብቶች አያያዝ ወቅታዊ ሁኔታ ክትትሎችን፤ ጥናትና ምርምር በማካሄድ መንግሥትን በሰብአዊ መብት ዙሪያ የማማከር እንዲሁም መብቶች ተጥሰው ሲገኙ የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማድረግ ይሰራል” ብለዋል። አክለውም “ለመብት ጥሰት ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች (እንደ አካል ጉዳተኞች እና ሌሎች) ልዩ ትኩረት በመስጠት ሰብአዊ መብቶች መከበራቸዉን በውል ለማረጋገጥ ለባለድርሻ አካላት የተለየ የምክክርና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማዘጋጀት ክትትልና ውትወታ በማካሄድ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል” ሲሉ ለተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል።

ተዋዋይ መንግሥታት የሕዝብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎችን መጀመርና በቀጣይነት አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ አዎንታዊ አመለካከትና የላቀ ማኅበራዊ ግንዛቤን እንዲያበረታቱ የተ.መ.ድ. የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት (አንቀጽ 8) ይደነግጋል፡፡ በአካል ጉዳተኞች ጽንሰ ሃሳብ እንዲሁም የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ዙሪያ የኅብረተሰቡ ግንዛቤ ማደጉ አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ሰው ተመሳሳይ መብቶች እና ዕድሎች እንዲያገኙ ትልቅ በር ከፋች ነው።   

በዝግጅቱ ላይ በጅማ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ የመንግሥት እና አገልግሎት ሰጪ ሕንጻዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹና ተደራሽ አለመሆናቸው በተሳታፊዎች የተመላከተ ሲሆን ፤ መስማት የተሳናቸዉ ሰዎች በፍርድ ቤቶች የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ ችግር መኖሩንም ገልጸዋል። ተሳታፊዎች በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ ከተካሄደው ጦርነት ጋር እና በሌሎች አካባቢዎች በሚከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር እንደሚጨምር ክግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ  አንስተዋል። የሕግ ማዕቀፎች ለመፈጸማቸዉ የሚከታተል አካል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲከታተል ተሳታፊዎች ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡

እዲሁም በሐዋሳው ዝግጅት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢሰመኮ ከፍተኛ የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን መብቶች ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር አስመላሽ ዮሐንስ “ኮሚሽኑ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ናቸው” ብለዋል። በተጨማሪም ኮሚሽኑ በማቋቋሚያ አዋጁ ማሻሻያ ካደረገባቸው መካከል በኮሚሽነር ደረጃ የሚመራ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች የሥራ ክፍል ማቋቋም አንዱ ነው። የሥራ ክፍሉም በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ላይ ትኩረት አድርጎ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን እና ኮሚሽኑ በሚሠራቸው ማንኛውም ሥራዎች ውስጥ አረጋውያንን ማዕከል ያደረገ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የአፍሪካ የሰብአዊና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር የአረጋውያን መብቶች ፕሮቶኮል በአንቀጽ 4 ላይ ለተዋዋይ መንግሥታት ከሚያስቀምጠው ግዴታዎች አንዱ በየደረጃው ያሉ የሕግ አስፈጻሚ አካላት ፖሊሲዎችንና ሕጎችን በተገቢው መንገድ መተርጎምና የአረጋውያንን መብቶች ማስጠበቅ የሚያስችል ሥልጠና መውሰዳቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሥልጠናው የአረጋውያንን መብቶች ዕውቅና እና ጥበቃ የሚሰጡ ሀገራችን ያወጣቻቸውን እና ያጸደቀቻቸውን ብሔራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሕግ እና የፖሊሲ ማዕቀፎችን ለባለድርሻ አካላት ማስተዋወቅ እና ግንዛቤ መፍጠርን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡

የዝግጅቱ ተሳታፊዎች ከሥራ በጡረታ የሚሰናበቱ አረጋውያን በቂ የሆነ የጡረታ አበል ሊያገኙ እንደሚገባ በአፍሪካ ሕብረት የአረጋውያን መብቶች ፕሮቶኮል የተደነገገ ቢሆንም፣ ሀገራዊ የጡረታ አዋጁ ቶሎ ቶሎ የሚሻሻል ባለመሆኑ ምክንያት በጡረታ ለሚተዳደሩ አረጋውያን የጡረታ አበሉ የኑሮ ውድነቱን ያማከለ አይደለም ብለዋል። አክለዉም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 41 (5) “መንግሥት አቅም በፈቀደ መጠን” ለአረጋውያን እንክብካቤ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት መቀመጡ አሻሚ መሆኑን አንስተዋል። 

የአረጋውያንን መብቶች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች (የግንዛቤ ማነስ፣ የበጀት እጥረት እና የሰለጠነ የሰው ኃይል ማነስ) ላይ በአትኩሮት  መሥራት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው። ስለሆነም ኮሚሽኑ በአረጋውያን መብቶች ዙሪያ የሚያደርገውን የውትወታ እና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ዶ/ር አስመላሽ ለተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል።