የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአማራ ክልል የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን እና ከተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ የዓይነ ሥውራን፣ የእንቅስቃሴ ጉዳት፣ መስማት የተሳናቸው እና የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ማኅበራት ተወካዮች፣ የአካል ጉዳተኞች መብቶችን በተመለከቱ የሕግ ማዕቀፎች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከግንቦት 16 እስከ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በእንጅባራ ከተማ ሰጥቷል።

ለሦስት ተከታታይ ቀናት የቆየው ስልጠና ስለ ኢሰመኮ ስልጣንና ተግባር፣ የሰብአዊና የአካል ጉዳተኝነት መብቶች ጽንሰ-ሃሳብ፣ የአካል ጉዳተኞች መብቶችን በተመለከቱ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ሀገር አቀፍ የሕግ ማዕቀፎች ዙሪያ ያተኮረ ሲሆን፤ እነዚህን ሕጎች ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ውስጥ አካል ጉዳተኞች በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው ውስጥ ከሚገጥሟቸው ዓይነተ-ብዙ መሰናክሎች አንጻር በማስተሳሰር የተሰናዳ ነበር።

ተሳታፊዎች በክልሉ የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ሥምሪት እና የመሰረተ-ልማቶች ተደራሽነት መብትን በተመለከተ በማኅበረሰቡ፣ በመንግሥት፣ በአካል ጉዳተኞች ዘንድ የተንሰራፋ የግንዛቤ ክፍተት መኖሩን አንስተዋል። ማኅበራት ያልተደራጁባቸው የአካል ጉዳት ዓይነቶች (ለምሳሌ፡-የአዕምሮ እድገት ውስንነት) መኖራቸው፣ ማኅበራቱ ያላቸው የሰው ኃይል እና የገንዘብ አቅም ውስንነት፣ የውትወታ ሥራዎችን ለማከናወን ያሉ የግንዛቤ ክፍተቶች በተግዳሮትነት ተጠቅሰዋል።

የአካል ጉዳተኞች የሥራ ሥምሪት መብትን የሚመለከት አዋጅ የወጣ እና ሥራ ላይ የዋለ ቢሆንም፤ በተለያዩ የመንግሥት እና የግል ተቋማት ያለው ያልተጣጣመ አሠራር አካል ጉዳተኞች በሥራ ቅጥር፣ ዕድገት፣ ድልድል፣ ዝውውር፣ ሥልጠናና ሌሎች የሥራ ሁኔታዎች ወቅት መድልዎ እንዲደርስባቸው መንስኤ እንደሆነ በውይይት ወቅት ተመላክቷል። የሥራ ቅጥር ማስታወቂያዎች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ አለመሆናቸው፣ የተመጣጣኝ ማመቻቸት ርምጃዎችን አለመውሰድ፣ ከትምህርት ዝግጅትና ከሥራ ልምዳቸው ውጪ በሆኑ የሥራ መደቦች መመደብ የመሳሰሉት ተግዳሮቶች መሮራቸውን የማኅበራቱ ተወካዮች ገልጸዋል። አክለውም እንደ ሕክምና፣ ትምህርት፣ ልዩ ልዩ የመንግሥት አገልግሎቶች፣ መንገድ፣ ፍርድ ቤት፣ ባንክ፣ የንግድ ተቋማት የመሳሰሉ መሰረታዊ አገልግሎት መስጫዎች ለአካል ጉዳተኞች በሚፈለገው መጠን ምቹ እና ተደራሽ አለመሆናቸው አንስተዋል።

የሥልጠናው ተሳታፊዎች እነዚህን እና መሰል የአካል ጉዳተኞች መሰናክሎች ለማስወገድ የሚረዱ ልዩ ልዩ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ለፌዴራልና ለክልል ሕግ አውጪ ምክር ቤቶች፣ በየደረጃው ላሉ የሕግ አስፈጻሚ አካላት፣ ለፍርድ ቤቶች፣ ለኢሰመኮ እና ለመገናኛ ብዙኃን ልዩ ልዩ ምክረ ሃሳቦችን አቅርበዋል፡፡ ለዋቢነት ያክል በፌዴራል እና በክልል ሕግ አውጪ ምክር ቤቶች ለአካል ጉዳተኞች የተለዩ መቀመጫዎች እንዲኖራቸው፤ አካል ጉዳተኞች እና የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት በተቋማት አደረጃጀት ክለሳ፣ በሕግና ፖሊሲ ዝግጅት ሂደቶች እና በመሳሰሉት አካል ጉዳተኞችን በቀጥታ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ንቁ እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ እንዲደረግ የሚሉት የሚጠቀሱ ናቸው።

የሲቪል ሰርቪስ እና የግል ድርጅቶች የቅጥር፣ የትምህርትና ስልጠና ዕድሎች፣ የደረጃ ዕድገት እና ተያያዥ መመሪያዎች ከአካል ጉዳተኞች ሥራ ስምሪት መብት አንጻር ዳግም እንዲጤኑ እና መገናኛ ብዙኃን የአካል ጉዳተኞች መብቶች ግንዛቤ እንዲፈጥሩ የበኩላቸውን ሚና እዲጫወቱ በስልጠናው ላይ ጥሪ ቀርቧል። በበጎ ጎኑ ደግሞ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ልዩ ልዩ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት በክልል፣ በዞን እና በወረዳ ደረጃ የተዋቀሩ ሲሆን፤ የአካል ጉዳተኞች መብቶች እንዲከበሩ በርካታ ሥራ የሚሠሩ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያ ንግግር ያሰሙት የኢሰመኮ ባሕር ዳር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አለባቸው ብርሃኑ፣ “አካል ጉዳተኞች ለልዩ ልዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ይበልጥ ተጋላጭ በመሆናቸው በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የዘርፍ ኮሚሽነር የተሰየመለት እና ጉዳዩን የሚመለከት ሥራ ክፍል በማደራጀት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው” ብለዋል። አክለውም ኮሚሽኑ ስለ አካል ጉዳተኝነት ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ለማረም የሚረዱ የስልጠና እና የውትወታ፣ እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራዎቹን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራትን እና ፌዴሬሽኖችን አቅም ለማሳደግ የሚረዱ ልዩ ልዩ ስልጠናዎች፣ የገንዘብ እና የእውቀት ድጋፎች፣ ወጥ የሆነ አደረጃጀት እንዲኖራቸውና እርስ በርሳቸው በቅንጅት የመሥራት ልምድ እንዲያዳብሩ መግባባት ላይ ተደርሷል። በተጨማሪም ሰልጣኞችም በስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት በየደረጃው ላሉ አባላቶቻቸው የማካፈል እና የአካል ጉዳተኞች መብቶችን የተመለከቱ ሕጎች በተግባር እንዲከበሩ ለማስቻል ሰፊ ሥራ የሚጠበቅባቸው መሆኑን አጽንዖት በመስጠት ስልጠናው ተጠናቋል፡፡