የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአካል ጉዳተኞች ረቂቅ አዋጁ አግባብነት ካላቸው ሕጎች፣ የመንግሥት ተቋማት ሥልጣንና ኀላፊነቶች እንዲሁም ከብሔራዊ የፖሊሲ አቅጣጫዎች አንጻር ሊያካትታቸውና ዳግም ሊጤኑ በሚገቡ ነጥቦች ዙሪያ፤ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ውይይት ሰኔ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር አዘጋጅቷል፡፡

በውይይቱ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ተወካዮችን ጨምሮ ከጤና፣ ከትምህርት፣ ከገንዘብ፣ ከትራንፖርትና ሎጂስቲክስ፣ ከከተማና መሠረተ ልማት፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ ከሥራና ክህሎት፣ ከባህልና ስፖርት እና ከግብርና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን እና ከማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የመጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በረቂቅ አዋጁ የተካተቱ ድንጋጌዎችን በየዘርፉ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ያቀረበ ሲሆን፤ የአስፈጻሚ አካላቱ ተወካዮች በቀረቡት ድንጋጌዎች ላይ እንደየኀላፊነታቸው መልስ ሰጥተውባቸዋል፡፡ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ተወካዮች በበኩላቸው በአዋጁ ይዘት ዙርያ ተጨማሪ ማብራርያዎችን የሰጡ ሲሆን፤ ተሳታፊዎች ረቂቅ ሕጉን ለማበልጸግ የሚያስችሉ ግብአቶችን ሰጥተዋል፡፡

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ
የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ

በዝግጅቱ የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ ኮሚሽኑ ብሔራዊ ሕጎች ከዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ጋር የማይቃረኑ ሆነው መውጣታቸውን የማረጋገጥ ኅላፊነት እንዳለበት አስረድተዋል።  ኢሰመኮ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እየተዘጋጀ የሚገኘውን የአካል ጉዳተኞች ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ አጠቃላይ እና ዝርዝር አስተያየቶች ቀደም ሲል በጽሑፍ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ማቅረቡን ኮሚሽነሯ አስታውሰዋል። አክለውም ረቂቁ የአካል ጉዳተኞች አዋጅ በተሰጡ አስተያየቶች መሠረት ዳብሮ ከሰብአዊ መብቶች ሰነዶች በተለይም ከዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች ስምምነት አንጻር የአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ እና ልዩ ልዩ ፍላጎቶቻቸውን ሊያሟላ በሚችል መልኩ እንዲወጣ ሁሉም የባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡