የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀውን የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ሁኔታ የተመለከተ ባለ 44 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ዓመታዊ የዘርፍ ሪፖርት ኢሰመኮ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ላይ በተጨማሪነት በተለይ በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ላይ በዝርዝር በማተኮር በበጀት ዓመቱ የታዩ መልካም እመርታዎች፣ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ አሳሳቢ ጉዳዮች እና ምክረ ሐሳቦችን ይዟል።
በሪፖርቱ ውስጥ የተካተቱት መረጃዎች እና ማስረጃዎች በዋናነት በኮሚሽኑ ከሐምሌ 2014 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2015 ዓ.ም. ካከናወኗቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራዎች፣ በግለሰቦች እና በሲቪክ ማኅበራት የቀረቡ አቤቱታዎች፣ መለስተኛ ጥናቶች እና በልዩ ልዩ የምክክር መድረኮች ላይ የተገኙ ግብአቶችን መሠረት ያደረጉ ናቸው። በተጨማሪም ከመንግሥት አስፈጻሚ አካላት፣ ከአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ማኅበራት አመራሮችና ኃላፊዎች ጋር ከተደረጉ ቃለመጠይቆች፣ ከመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እና ከሌሎች ሰነዶች የተገኙ መረጃዎች ተካትተዋል።
የአካል ጉዳተኞች ስምምነትን መሠረት ያደረገ ረቂቅ አዋጅ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ለፍትሕ ሚኒስቴር መቅረቡ፣ የአፍሪካ አካል ጉዳተኞች ፕሮቶኮልን ለማጽደቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥያቄ መቅረቡ፣ የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ ድርጅት መቋቋሙ እና የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት አካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የአካል ድጋፍ አገልግሎት መሰጠቱ በሪፖርቱ ከተካተቱ ቁልፍ እመርታዎች መካከል ይገኙበታል።
በተጨማሪም፣ አዳዲስ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት መቋቋማቸውና ነባሮችም መጠናከራቸው፣ ኢሰመኮ ይፋ ባደረገው የአረጋውያን መንከባከቢያ ማእከላት ሪፖርት ምክረ ሐሳቦች መነሻነት አገልግሎቶቻቸው ላይ ማሻሻያ ያደረጉ ማእከላት መኖራቸው፣ የግል ሕፃናት ማሳደጊያዎች ለአካል ጉዳተኛ ሕፃናት የተሻለ የመብት ጥበቃ እያደረጉ መሆኑ፣ ለአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ነጻ የሕግ ድጋፍ መሰጠቱ እንዲሁም በክልል ደረጃ የወጡ የሥራ ስምሪት ሕጎች ለአካል ጉዳተኞች የተሻለ የመብት ጥበቃ ማድረጋቸው አበረታች መሆናቸው በሪፖርቱ ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል፣ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያንን ጉዳዮች የሚመለከተው ተቋማዊ መዋቅር ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ ባሉት የመንግሥት መዋቅሮች ወጥ ባለመሆኑ የሚፈጠሩ የአሠራር መዘበራረቆች እና እነሱን ተከትለው የሚመጡ አስተዳደራዊ ቅሬታዎችና በደሎች መበራከታቸው፣ ሀገራዊ ሕግጋትን ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር ለማጣጣም የሚደረገው እርምጃ ፈጣን አለመሆኑ እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚማሩ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሚያጋጥሟቸው ዘርፈ-ብዙ ተግዳሮቶች አሳሳቢ ጉዳዮች ተብለው ተለይተዋል።
ሪፖርቱ በሀገሪቱ በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የአካል ጉዳተኞች ቁጥር መጨመሩና የአካል ድጋፍና ተሐድሶ አገልግሎት ተደራሽነት ዝቅተኛ መሆኑ እንዲሁም በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የተቀበሩ ፈንጂዎች እያደረሱት ያለውን የሞትና አካል ጉዳት ሥጋትም በአሳሳቢነታቸው አመላክቷል። በተጨማሪም በመንግሥትም ሆነ በግል የሕፃናት መንከባከቢያ ተቋማት አካል ጉዳትን መሠረት ያደረጉ አገልግሎቶች በሚፈለገው መጠን አለመኖራቸው፣ ክብረ-ነክ ቃላት (derogatory terms) የመሪነት፣ የኃላፊነት እና የአስተማሪነት ሚና ባላቸው ሰዎች በመገናኛ ብዙኃን ጥቅም ላይ መዋላቸው እና የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ትክክለኛ ቁጥር አለመታወቁ አሳሳቢ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ኢሰመኮ በሪፖርቱ የተለዩትን አሳሳቢ ሁኔታዎች ለመቅረፍ ብሎም የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ሰብአዊ መብቶችን በተሟላ ሁኔታ ለማክበር፣ ለመጠበቅ እና ለማስፋፋት ያስችላሉ ያላቸውን ምክረ ሐሳቦችም አመላክቷል።
የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ፤ ሪፖርቱ ለአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች በቂ ጥበቃ የሚያደርጉ ሕጎችና ፖሊሲዎች አለመኖር ወይም በይዘትና አተገባበር ሂደታቸው ላይ በሚታዩ ክፍተቶች ወይም ከተቋማዊ አሠራሮችና ከተሳሳቱ አመለካከቶች የመነጩ ዐይነተ-ብዙ መሰናክሎችን በዘላቂነት ለማስቀረት ጥሩ ግብአት እንደሚሆን ተናግረዋል። ኮሚሽነር ርግበ አክለውም፣ በሪፖርቱ የተካተቱ ምክረ ሐሳቦች እንዲፈጸሙ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት፣ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ተቋማት እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።