የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ
ሚያዚያ 21 ቀን 2014 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መድ.) የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የምሥራቅ አፍሪካ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር ሚያዝያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. “Africa Pre-trial Detention Day’’ ወይም “የአፍሪካን ቅድመ-ክስ/ቅድመ ፍርድ እስራት ቀን” አስመልክቶ የፌደራል እና የክልል ፍትሕ ተቋማትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡ ይህ ቀን የአፍሪካ ሕብረት የሰብአዊ እና የሰዎች መብቶች ኮሚሽን እ.ኤ.አ. በኦክቶበር 15 ቀን 2015 ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት በየዓመቱ ኤፕሪል 25 ቀን ታስቦ ይውላል።

በዝግጅቱ ላይ የቅድመ-ክስ እስራትን በተመለከተ ተፈጻሚ የሆኑ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፎችን በመዳሰስ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የሚገኙ የቅድመ-ክስ እስረኞች አያያዝ እና ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ተሳታፊዎች ሃሳብ ተለዋውጠዋል። ክፍተቶችን በመለየት ወደፊት በቅንጅት ሊሰሩ በሚችሏቸው ተግባራት ላይም መክረዋል።  የኢሰመኮ የክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል በ2014 ዓ.ም. በጀት ዓመት ባከናወነው የማረሚያ ቤቶች ክትትል ያሉ ግኝቶችን ለተሳታፊዎች አቅርቧል፡፡

የኢሰመኮ የሲቪል፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጂብሪል በመክፈቻ ንግግራቸው፣ ክስ ሳይመሰረት የሚደረጉ እስሮች ለነጻነት መብት ጥሰት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ገልጸው፣ “በሕይወት የመኖር መብት፣ ከስቃይ እና ኢሰብአዊ አያያዝ የመጠበቅ መብት፣ የዋስትና መብት እና የተቀላጠፈ ዳኝነት የማግኘት መብትን የሚቃረን ነው” ብለዋል፡፡ 

በተለይም የተራዘመ የቅድመ-ክስ እስራት በራሱ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሊሆን ስለሚችል የተራዘመ ከክስ በፊት ያለ እስራትን ለመከላከል ልዩ ትኩረት ይሻል፡፡ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ዘንድ የተሻለ ተቋማዊ አሰራር እንዲኖር ለማድረግ የቅድመ-ክስ ወይም ፍርድ እስረኛ ሰዎች ጥበቃን በሚመለከት ያሉትን የሕግ ማዕቀፎች መፈተሽ፣ የአሰራር ክፍተቶችንና ተግዳሮቶችን መለየት እና አስፈላጊ ማሻሻያዎችን እና የእርምት እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚኖርባቸው በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡

ለውይይቱ በመነሻነት የቀረቡ ሌሎች ጽሑፎች ከወንጀል ጋር ተያይዞ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሴቶችን፣ሕፃናትን፣ ወጣት አጥፊዎችን አያያዝና በአጠቃላይ የቅድመ-ክስና ፍርድ እስርን ዳሰዋል። 

የተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት የምሥራቅ አፍሪካ ቢሮ ተወካይ ማርሴል ክሌመንት አክፖቮ፣ “የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የቅድመ-ክስ እስራትን በተመለከተ የጥበቃ እና ከለላ ድንጋጌዎችን ያካተተ ቢሆንም፣ በሀገሪቱ የዘፈቀደ እና የተራዘመ የቅድመ-ክስ እስራት አሳሳቢ ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡ አክለውም በመንግሥት በኩል የወንጀል ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕጉን ለማሻሻል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ተወካይ ኡሳኒ ኒኮላስ በበኩላቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት የቅድመ-ክስ እስራትን በተመለከተ ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸውን ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች እና በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ የመብት ጥበቃዎችን እንዲሁም የሉዋንዳ መመሪያዎችን በሙሉ ተፈጻሚነታቸው እውን መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው ብለዋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝደንት የተከበሩ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ

የማጠቃለያ ሃሳብና የወደፊት አቅጣጫዎችን በተመለከተ ምክረ ሃሳቦች የሰጡት የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝደንት የተከበሩ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ “የቅድመ-ክስ እስራት ጥያቄን ተገቢነት በሚገባ በመመዘን እና የተጠርጣሪዎችን መብት በመጠበቅ በፍ/ቤቶች በኩል እያደገ የመጣ ለውጥ መኖሩን’’ አንስተው፤ ‘’ምንም እንኳን የአቅም ውስንነቶች ቢኖሩም መሰረታዊ ከሆነው መረጃ ልውውጥ ጀምሮ የቅንጅት ሥርዓት መዘርጋት እና ማጠናከር ተገቢ ነው” ብለዋል። በተጨማሪም በቅድመ-ክስና ፍርድ እስራት እንዲሁም በሌሎች እስራቶች ውስጥ የሴት እስረኞችን ልዩ ሁኔታ ማጤን ሌላኛው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው የቅድመ-ክስ እስራት በሕግ በተመለከተው ሁኔታዎች ብቻ ማለትም ተጨማሪ የወንጀል ተግባርን ለመከላከል፣ የተጠርጣሪውን ማምለጥ ለመከላከል ወይም በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ የተጠርጣሪዎችን ተገቢ ያልሆነ ጣልቃ ገብነት ለመከላከል በአሳማኝ ምክንያታዊ ሁኔታ ብቻ የሚፈቀድ በመሆኑ፤ የቅድመ ክስ እስርን ተገቢነትን ለመቆጣጠር የፍርድ ቤቶች ክትትል አስፈላጊ መሆኑን አስታውሰው፤ በፖሊስና ዐቃቤ ሕግ በኩልም ተገቢ ያልሆነ ቅድመ ክስ እስራትን ለማስቀረት የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡