የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአካል ጉዳተኞች ያለውን ተደራሽነት አስመልክቶ የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ  አየር ማረፊያዎች ላይ በአከናወነው ክትትል በለያቸው ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አከላት ጋር መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ተወያይቷል፡፡ በውይይቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የተለያዩ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት፣ የመንግሥት ተቋማት እና የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በውይይቱ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ አየር መንገዶች ተቋማዊ፣ ከባቢያዊ፣ የመረጃና ተግባቦት ተደራሽነት ክፍተቶች እንዲሁም አመለካከት ላይ ትኩረት በማድረግ ባካሄደው ክትትል የተለዩ ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኛ የሆኑ አምስት አካል ጉዳተኞች በዓለም አቀፍ እና በሀገር ውስጥ የበረራ አገልግሎቶች ላይ የሚስተዋሉ ልዩነቶችን እና አየር መንገዱን ሲጠቀሙ የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ተጨባጭ ምሳሌዎችን በመስጠት ልምዳቸውን አጋርተዋል። የአየር መንገዱ አካል ጉዳተኛ ደንበኞች ባጋሩት ልምድ አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ በረራዎች ላይ የሚሰጠው አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ ተደራሽ እና የአካል ጉዳተኛ መንገደኞችን ሰብአዊ ክብር የጠበቀ መሆኑን ገልጸው፣ ይህንኑ ልምድ ወደ ሀገር ውስጥ በረራዎች እንዲያስፋፋ ጠይቀዋል።

የአየር መንገዱ ተወካዮች በበኩላቸው የተነሱት ሐሳቦች እጅግ ጠቃሚ እና እንደ ግብአት በመውሰድ የሚሠራባቸው መሆኑን በመጠቆም፣ አየር መንገዱ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠውን አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለማሻሻል የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ሜቲ አቶምሳ፣ የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር፣ ኢሰመኮ (በግራ በኩል) | የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ (በቀኝ በኩል)

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ አካል ጉዳተኞች ራሳቸውን ችለው ለመኖር እና በሁሉም የሕይወት ዘርፍ የተሟላ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን በመጥቀስ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድም አገልግሎት ሰጪ ተቋም እንደመሆኑ ያለበትን ኃላፊነት በተሟላ ሁኔታ እንዲወጣ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። አክለውም  ኮሚሽኑም ከአየር መንገዱ አጋር በመሆን የአካል ጉዳተኞችን ሰብአዊ መብቶች ለማስከበር እና ለማስጠበቅ በጋራ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡