ማብራሪያ  

ከእናቶች ጋር የታሰሩ ሕጻናት ምን ማለት ነው?  

በአብዛኛው ጊዜ አባቶች ለእስር ሲዳረጉ እናቶች ሕጻናት ልጆችን መንከባከባቸውን ይቀጥላሉ። ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ እናቶች ሲታሰሩ ለሕፃናቱ እንክብካቤ ሌላ አማራጭ መንገድ (አባት ወይም ዘመድ ወይም ሌላ ግላሰብ ወይም ተቋም) ያልተገኘ እንደሆነ፤ እናቶች ሕጻናት ልጆቻቸውን ይዘው ወደ እስር ስለሚሄዱ፤ ሕፃናት ልጆች ከእናታቸው ጋር በእስር ቤት የሚቆዩበት ሁኔታ ይፈጠራል። ከዚህ በተጨማሪም በእስር ላይ እያሉ የወለዱ እናቶች ከጨቅላ ሕጻናት ልጆቻቸው ጋር በእስር ቤት የሚቆዩበት ሁኔታ ይፈጠራል። ስለሆነም ከእናቶች ጋር የታሰሩ ሕጻናት ማለት በእስር ቤት ውስጥ በታሳሪ እናቶች የተወለዱ ወይም እናቶቻቸው ወደ እስር ቤት ይዘዋቸው የገቡ ሕጻናት ልጆች ማለት ነው።  

የእስረኛ እናቶች እና ብቸኛ አሳዳጊዎች ልጆች የተጋላጭነት ሁኔታ ምን ይመስላል?  

ሕፃናት ልጆች ወላጆቻቸው ወይም አሳዳጊዎቻቸው ሲታሰሩ እንክብካቤና ጥበቃ የሚሰጣቸው በማጣት ወይም እናት እስረኛ ሆና ሕፃናቱ በእስር ቤት ሲወለዱ፣ ወይም ሕፃን ልጆች ሆነው ከእናታቸው ጋር በእስር ቤት እንዲቆዩ በመደረጋቸው ምክንያት  አጠቃላይ ደኅንነታቸውና የሕጻናት መብቶቻቸው ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ የሕፃናት ከወላጅ እናት መለየት ወይም አብሮ ለእስር መዳረግ በእድገታቸው፣ ትምህርትና ጤናቸው ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡ በዚህም ምክንያት፣ የእናቶች መታሰር በእናቶች ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ ሕፃናትን ለጉዳት እና አብሮ ለመታሰር ይዳርጋል። 

ወላጆቻቸውና አሳዳጊዎቻቸው ለእስር የተዳረጉባቸውና በእስር ቤት የሚገኙም ሆነ ከውጭ ያሉ ሕፃናት ብዛትና ያሉበትን ሁኔታ አስመልክቶ በቂ መረጃ ባለመኖሩ የሕፃናቱን የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና የሚያገኙትን አገልግሎት በተመለከተ ግምገማ ለማድረግና የእርምት እርምጃዎችን ለመውሰድ አስቸጋሪ አድርጎታል ። ኢሰመኮ በተለያየ ጊዜ በእስር ቤቶች ባደረጋቸው የክትትል ሥራዎች በእስር ቤት የሚወለዱትን ጨምሮ በተለያየ የእድሜ እርከን የሚገኙ ብዛት ያላቸው ሕፃናት ለሕይወታቸው የሚያስፈልጉ መሰረታዊ አቅርቦቶች ባልተማሉባቸው እና ሰብአዊ መብቶቻቸው ሳይከበሩ ከእናቶቻቸው ጋር እስር ቤት እንዲቆዩ የሚደረጉ መሆኑን ተመልክቷል። ለሚያጠቡ እናቶችና ከእስረኛ እናቶች ጋር እስር ቤት ለሚገቡ ጨቅላ ሕፃናት ምቹ የሆነ ቦታ ባለመዘጋጀቱ እስር ቤት ያሉ እናቶች ከሌሎች እስረኞች ጋር ተቀላቅለው በተጨናነቀ ሁኔታ ለመኖር ተገድደዋል። ሕፃናቱ ተገቢውን የጤና፤ ምግብ፤ ንጽሕና፣ መኝታ እና የመሳሰሉት አገልግሎት እንደማያገኙም ለመረዳት ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ሕፃናቱ የመማር፤ የሥነልቦና ድጋፍና የመጫወቻ ቦታ የማግኘት እድል የላቸውም፡፡ 

ተፈጻሚነት ያላቸው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ሕግጋትና የፖሊሲ ማዕቀፎች ምንድን ናቸው?  

ሀ) ዓለምአቀፍ  

በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወላጆቻቸው የታሰሩባቸው ሕፃናትን ከሚመለከቱት ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ሕግጋት እና የፖሊሲ ማዕቀፎች መካከል ዓለም አቀፉ የሕጻናት መብቶች ስምምነት፣ የአፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ደኅንነት ቻርተር፣ የተባበሩት መንግሥታት የእስረኞችን አያያዝ የሚመለከቱ መሠረታዊ መርሆች እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የሴት እስረኞችን አያያዝ የሚመለከቱት ደንቦች በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። ዓለም አቀፉ የሕጻናት መብቶች ስምምነት ወላጆቻቸው በእስር ቤት የሚገኙ ሕጻናትን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ በርካታ ጠቀሜታ ያሏቸውን መብቶችን እና መርሆዎችን ያስቀምጣል።

በስምምነቱ መግቢያ እንደተገለጸው ሕፃናት “በለጋ እድሜያቸው ምክንያት ተጋላጭ በሚሆኑበት አካላዊ እና አዕምሯዊ እድገት/ብስለት የሚገኙ እንደመሆናቸው ልዩ ድጋፍና እንክብካቤ እንዲሁም የሕግ ድጋፍ” የሚያስፈልጋቸው እንደመሆኑ የሕፃናትን መብቶች በልዩ ሁኔታ የሚያስከብሩ ድንጋጌዎች በስምምነቱ የተለያዩ ክፍሎች ተካተው ይገኛሉ። 

ከነዚህም መካከል ሕፃናት በልዩ ሁኔታዎች ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የግድ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ከወላጆቻቸው መለየት የሌለባቸው ስለመሆኑና ከሁለቱም ወላጆች ጋር የመገናኘት መብት እንዳላቸው፣ በወላጆቻቸው ድርጊቶችና ወላጆቻቸው በሚገኙባቸው ሁኔታዎች ምክንያት ለመድሎ መዳረግ እንደሌለባቸው፣ በሁሉም ሕፃናቱን በሚመለከቱ ጉዳዮች እና ውሳኔዎች የሕፃናቱን የላቀ ጥቅም ማስከበር ተቀዳሚ ትኩረት የሚሰጠው ስለመሆኑና እና መንግስታት ለሕፃናት ደሕንነት የሚያስፈልገውን ሁሉ እንክብካቤ እና ጥበቃ የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው የሚደነግጉት ክፍሎች ይገኙበታል። 

ለ) አፍሪካ  

የአፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ደኅንነት ቻርተር ከላይ በዓለም አቀፉ የሕጻናት መብቶች ስምምነት የተካተቱን አይነት በማናቸውም ሁኔታዎች የሕፃናትን መብቶች እና ሁለንተናዊ ደሕንነት ለማረጋገጥ የሚያገለግሉ መሰረታዊ ድንጋጌዎች እና መርሆች የሚገኙበት ከመሆኑም በተጫማሪ በቻርተሩ አንቀጽ 30 በተለይ እናቶቻቸው የታሰሩባቸው ሕጻናትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን አካቷል። በዚህ አንቀጽ የተካተቱት ዝርዝር ድንጋጌዎች በወንጀል ጉዳይ ጥፋተኛ የተባሉ እናቶች ላይ የቅጣት ውሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ ከእስር በመለስ ያሉ አማራጭ ቅጣቶች ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ መሆኑን፣ ለአሳዳጊ እናቶች የተለዩ የማረሚያ/የማቆያ ቦታዎችን ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን፣ እናቶች ከልጆቻቸው ጋር እንዳይታሰሩ ማድረግን፣ በአሳዳጊ እናቶች ላይ የሞት ቅጣት እንዳይጣልባቸው ማድረግንና በእናቶች ላይ የሚጣል ቅጣት ዋነኛው ዓላማ ተሃድሶ፣ እናቶች ከቤተሰባቸው ጋር የሚሆኑባቸውን ሁኔታዎች መፍጠር እና መልሶ ማቋቋም መሆን እንዳለበት የሚገልጹ ናቸው። 

የአፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ደኅንነት ባለሙያዎች ኮሚቴ እ.ኤ.አ በኅዳር ወር 2013 ዓ.ም. ባወጣው እና የአፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ደኅንነት ቻርተር (ACERWC) አንቀጽ 30ን በሚተረጉመው አስተያየት(comment) ላይ እንደተመለከተው የሕፃናት ብቸኛ ወይም የመጀመሪያ ተንከባካቢዎች በሚታሰሩበት ጊዜ አገራት በሁሉም የፍትህ እና የአስተዳደር ውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች፣ በቅድመ ችሎት እርምጃዎች፣ በችሎት እና ቅጣት አወሳሰን፣ በእስራት፣ በመፍታት እና ከቤተሰብ እና ከማህበረሰቡ ጋር የመቀላቀል ሂደትንም ጨምሮ በወንጀል ፍትህ ሂደቱ ውስጥ በቻርተሩ የተካተቱን ድንጋጌዎችና መርሆች ተፈጻሚ ለማድረግ አስፈላጊ ሕጎችን/ፖሊሲዎችን ማውጣት እና መተግበር እንደሚጠበቅባቸው ይገልጻል፡፡ 

በተጨማሪም ከላይ በተጠቀሱት የተ.መ.ድ. የእስረኛ አያያዝ ደንቦች የሚከተሉት መርሆች ተካተዋል፤  

 • በሴቶች የማረሚያ ቦታዎች ውስጥ ሁሉም አስፈላጊ የቅድመ-ወሊድ እና ድህረ-ወሊድ እንክብካቤ እና ህክምና እንዲሁም ሕፃናት በተቻለ መጠን ከማረሚያ ቤቶች ውጭ በሆስፒታል እንዲወለዱ ሊደረግ እንደሚገባ፣
 • ሕፃናት በእስር ቤት ውስጥ ሲወለዱ ይህ ሁኔታ በልደት የምስክር ወረቀት ሊጠቀስ እንደማይገባ
 • ሕፃናት ከእናቶቻቸው ጋር በእስር ቤት እንዲቆዩ የሚደረግ ከሆነ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች የሚገኙበት የሕጻናት ማቆያ ቦታ/መዋለ ሕፃናት ሊዘጋጅላቸው የሚገባ መሆኑን፣
 • ከእናቶቻቸው ጋር በእስር ቤት የሚገኙ ልጆች እንደ እስረኛ ሊታዩና በእስረኛ አያያዝ ሊያዙ እንደማይገባ፣
 • ልጆቻቸው በእስር ቤት አብረዋቸው የሚገኙ እናቶች በተቻለ መጠን ከልጆቻቸው ጋር ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ እንዲደረግ፣ እንዲሁም በእስር ቤቶች ያለው የልጆች እንክብካቤ በተቻለ መጠን ከእስር ቤት ውጭ ካለው ሁኔታ ጋር ተቀራራቢ ሊሆን ይገባል የሚሉት ናቸው።  

በኢትዮጵያ ያለው የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ ምን ይመስላል?  

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 36 በተለያዩ በዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ሕግጋት ለተካተቱት የሕፃናት መብቶች እውቅና ይሰጣል። ከእነዚህ ውስጥ በተለይ የሕፃናት በሕይወት የመኖር መብት፣ ወላጆችን ወይም አሳዳጊዎችን የማወቅና የእነሱን እንክብካቤ የማግኘት መብት፣ ሕፃናትን በሚመለከቱ ውሳኔዎች የሕፃናት ደሕንነት በቀደምትነት መታሰብ የሚኖርበት መሆኑን የሚገልጸው ድንጋጌ ወላጆቻቸው ለታሰሩባቸው ሕፃናት አግባብነት ያላቸው መብቶች ድንጋጌዎች ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 41 የተጠቀሱት መንግሥት ለጤና፣ ለትምህርት እና ለሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ሀብት የመመደብ እና የሀገሪቱ አቅም በፈቀደው መጠን ካለ ወላጅ ወይም አሳዳጊ ለቀሩ ሕጻናት ድጋፍ እና እንክብካቤ የማድረግ ግዴታዎች ለዚህ ጉዳይ አግባብነት ይኖራቸዋል። ከሕገ መንግሥቱ በተጨማሪ በእስር ላይ ያሉ ወላጆች ሕጻናትን በግልጽ ከሚመለከቱ የፖሊሲ ሰነዶች መካከል የብሔራዊ የሕፃናት ፖሊሲ አንዱ ነው፡፡ ወላጆቻቸው በእስር ላይ ያሉ ሕጻናት ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ አገልግሎቶችን የማግኘት አቅማቸው ውስን የመሆኑን እውነታ በብሔራዊ የሕፃናት ፖሊሲዉ ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ሕግ ሕፃናትን ከእስረኛ ወላጅ መለየትም ሆነ አብረው እንዲታሰሩ ማድረግ የሚፈቅድ ነው፡፡ የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ 365/1995 አንቀጽ 28 የእናት የቅርብ ክትትል የሚያስፈልጋቸው እድሜያቸው ከ 18 ወራት ያልበለጠ ሕፃናት ከታራሚ እናታቸው ጋር በእስር ቤት ሊቆዩ እንደሚችሉ ይገልፃል፡፡ ይሄው አንቀጽ ሕፃኑ/ኗ በእስር ከእናት ጋር በመታሰሩ/ሯ አካላዊ ወይም ሥነ-ልቦናዊ አቋም ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ከሆነ፣ ኮሚሽኑ ሕፃኑ ሌላ አሳዳጊ ወይም ሞግዚት እንዲያገኝ/ድታገኝ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚኖርበት ይደነግጋል። ምንም እንኳን አዋጁ እድሜያቸው ከ 18 ወራት ያልበለጠ ሕፃናትን በሚመለከት ብቻ ከታራሚ እናታቸው ጋር በእስር ቤት ሊቆዩ እንደሚችሉ የሚገልጽ ቢሆንም፤ አማራጭ አሳዳጊ ወይም ሞግዚት በማጣት የተነሳ ከ 18 ወር እድሜ በላይ የሆኑና በተለያየ የእድሜ እርከን ላይ የሚገኙ ሕፃናትም ጭምር ከእናታቸው ጋር በእስር ቤቶች የሚገኙ ሲሆን ይህም የችግሩን ስፋት ያሳያል። 

ከላይ የተጠቀሰውን አዋጅ ተከትሎ የወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 138/1999 በአንቀጽ 11(7) ነፍሰ ጡር የሆነች ታራሚ የመውለጃ ቀኗ ሲደርስ በተቻለ መጠን በቂ የህክምና አገልግሎት ወደሚገኝበት ተቋም ተወስዳ እንድትወልድ የሚደረግ መሆኑንና ሆኖም ህፃኑ በእስር ቤቱ ውስጥ የተወለደ ከሆነ ይኸው ሁኔታ በልደት የምስክር ወረቀቱ ላይ የማይጠቀስ መሆኑን ይገልጻል። በተጨማሪም የደንቡ አንቀጽ 12 ሕፃናት በእስር ቤት ቆይታቸው አስፈላጊውን ምግብ፣ ክትባት፣ ሕክምና እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንዲያገኙ የሚደረግ ስለመሆኑ እንዲሁም ነፍሰ ጡር ወይም እመጫት የሆነች እስረኛ በሀኪም ትዕዛዝ ተጨማሪ ምግብ እንድታገኝ የሚደረግ መሆኑን ይገልጻል። እነዚህ ድንጋጌዎች በደንቡ መካተታቸው ጠቃሚነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ደንቡ ከእናቶቻቸው ጋር በእስር ለሚቆዩ ሕፃናት ስለሚደረገው ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ ዝርዝር ጉዳዮችን እና መርሆችን ያካተተ ባለመሆኑ የሕፃናቱን መብቶች ለማስከበር በቂ አስቻይ ሁኔታዎች የሉም።  

ከላይ በተጠቀሰው አዋጅም ሆነ በደንቡ እናት በእስር ባለችበት ወቅት ሕጻን ልጅ ከእርሷ ጋር በእስር ቤት እንዲቆይ ወይም በአሳዳጊ ወይም ሞግዚት እንክብካቤ እንዲደረግለት በመወሰን ረገድ መከተል ስለሚገባው ሥነ ሥርዓት እና ከግምት መግባት ያለባቸው ዝርዝር ሁኔታዎች አልተካተቱም። በሌሎች አገራት እናቱ ከእርሷ ጋር እንዲኖር ያቀረበችው ጥያቄ እንደሁኔታው በእስር ቤት ባለስልጣን ወይም በፍርድ ቤት ፈቃድ የሚወሰን ሲሆን፣ ከግምት ከሚገቡት ጉዳዮች መካከል የጡት ማጥባት ሁኔታ፣ ሌሎች የሕፃናት እንክብካቤ አማራጮች መኖር/አለመኖር፣ የማረሚያ ቤቱ ማረፊያ ለልጁ እድገት ተስማሚ መሆኑ/አለመሆኑ፣ የልጁ ጤንነት፣ የልጁ ደህንነት መጠበቅ፣ ሙሉ የወላጅ ኃላፊነት፣ የወላጅነትን ኃላፊነት የመወጣት ብቃት፣ የቅጣቱ ርዝመት፣ ማረሚያ ቤት ከመግባቱ በፊት በወላጅ እና በልጁ መካከል ያለው ግንኙነት ይገኙባቸዋል።1 

ወላጆቻቸው የታሰሩባቸው ሕፃናትን መብቶች ለማረጋገጥ ምን ማድረግ ይገባል?  

መንግሥት በሁሉም የፍትህ እና የአስተዳደር ውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ከላይ በተብራሩት ዓለም አቀፍ ሕግጋትና የፖሊሲ ማዕቀፎች መሠረት ወላጆቻቸው የታሰሩባቸው ሕፃናትን መብቶችን ለማረጋገጥ አስፈላጊ ሕጎችን እና ፖሊሲዎችን ማውጣትና የሚከተሉትን እርምጃዎችና ምክረ ሃሳቦች መተግበር ይጠበቅበታል፤ 

 • በእስር ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሕጻናትን እንዲሁም ወላጆቻቸውና፣ ዋና ተንከባካቢዎች በእስር ላይ ሆነዉ በውጭ የሚኖሩት ሕጻናትን መረጃ በመደበኛነት እና ስልታዊ በሆነ መንገድ ማሰባሰብ፤
 • በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ላይ ወላጆች/ብቸኛ አሳዳጊዎች በወንጀል ተጠርጥረው በሚያዙበት ጊዜ የዋስ መብታቸው ተጠብቆ ክርክራቸውን ከውጭ ሆነው እንዲከታተሉ የሚያስችል ድንጋጌ ማካተት፤
 • ለነፍሰጡር ታራሚዎች ወይም ሕጻናት ልጆች ላሏቸው እናቶች ከእስራት ውጪ ያሉ ቅጣቶች ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ማድረግና እነዚህን እናቶችን የሚይዙ ልዩ አማራጭ ተቋማትን ማቋቋም፤
 • ለነፍሰጡር ታራሚዎች ወይም ሕጻናት ልጆች ያሏቸው እስረኞች ላይ የሞት ቅጣት እንዳይጣል ማድረግ፣
 • አንድ ሕፃን በእስር ቤት እንዲቆይ/ድትቆይ ወይም በአሳዳጊ ወይም ሞግዚት እንክብካቤ እንዲደረግለት/ላት በመወሰን ሂደት የሕፃኑን/ኗን የላቀ ጥቅም ማስከበር ተቀዳሚ ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግና የሕጻኑ/ኗ አስተያየት ግምት ውስጥ እንዲገባ ማድረግ፣
 • በእድሜ ዝቅ ላሉ (ለጨቅላ) ሕፃናት የተለየ ትኩረት መስጠት
 • ከወላጆቻቸው ጋር ወደ ማረሚያ ቤት ለሚገቡ ሕጻናት የሚደረገው እንክብካቤ በተቻለ መጠን ከማረሚያ ቤት ውጭ ካለው ሁኔታ ጋር ተቀራራቢ እንዲሆን ማድረግና ሕፃናት ለአካላዊ እና አዕምሯዊ እድገታቸው የሚያስፈልጓቸውን እንደ ምግብ፣ ጤናና፣ ትምህርት፣ የሕጻናት ማቆያ ቦታ/መዋለ ሕፃናት የመሳሰሉትን አገልግሎቶችን በአግባቡ ማቅረብ፣
 • ሕፃናት ከማረሚያ ቤት ከወጡ በኋላ በሕብረተሰቡ ውስጥ መልሶ ማቋቋም እንዲቻል በመንግስት ተቋሞችና በሲቪል ማህበረሰብ ባለድርሻ አካላት መካከል ያለው ትብብር እና ቅንጅት ማጠናከር፣
 • ወላጆቻቸው የታሰሩባቸው ሕፃናትን የሚከታተል የተለያዩ ተቋሞችን ያቀፈ (multi-sectoral) ክፍል ተደራጅቶ የሚመለከታቸው አካላትን የሕፃናቱን አኗኗር የሚያሻሽል የፓሊሲ ለውጥ እንዲያደርጉና እና አስፈላጊ አገልግሎቶች መስጠታቸውን የሚከታተልና የሚመክር መሆን አለበት።

1ነፃነታቸውን በተነፈጉ ሕጻናት ላይ የተሰራ ዓለም አቀፍ ጥናት 2011, p388.