የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የጋምቤላ ክልል የቤተሰብ ሕግ አፈጻጸም ላይ ከሚመለከታቸው አካላት መረጃ በመሰብሰብ እና የሰነድ ምልከታዎችን በማድረግ በለያቸው ግኝቶች እና በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ዙሪያ የተለያዩ የመንግሥት ባለድርሻ አካላት፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተወካዮች ጋር ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በጋምቤላ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

በውይይት መድረኩ የጋምቤላ ክልል የቤተሰብ ሕግ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ ለረጅም ዓመታት ሥራ ላይ የቆየ ቢሆንም ሕጉ በሚወጣበት ጊዜ ኅብረተቡን ያሳተፈ አለመሆኑ፤ የነባር ብሔረሰቦች ወግ፣ ባህል፣ እሴቶች እና የአኗኗር ዘይቤን ከግምት ባስገባ መልኩ አለመውጣቱ፤ በአብዛኛው ኅብረተሰብ ዘንድ ስለ ቤተሰብ ሕጉ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑ እና የአስፈጻሚ አካላት ቁርጠኝነት ማነስ ተፈጻሚነቱ ላይ አሉታዊ አስተዋጽዖ እያሳደረ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ በዚህም ምክንያት በክልሉ ከቤተሰብ ሕጉ ይልቅ ልማዳዊ እና ባህላዊ አሠራሮች በይበልጥ ተፈጻሚ መሆናቸው ተጠቅሷዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ኅብረተሰቡ በቤተሰብ ሕጉ ዙሪያ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆን ሴቶች የሚደርስባቸውን የመብ ጥሰት ወደ ሚመለከተው አካል ሄደው ሪፖርት እንዳያደርጉ እና መፍትሔ እንዳያገኙ ማድረጉ፤ ሴቶች በጋብቻ ውስጥ እና ከጋብቻ በኋላ በፍቺ ወቅት ያላቸውን መብቶች በአግባቡ እንዳይጠቀሙበት እያደረገ መሆኑ፤ እንዲሁም የሴቷ ሙሉ ነጻ ፈቃድ ሳይረጋገጥ ከፍተኛ ገንዘብ ወይም ከብት በጥሎሽ በመስጠት ወደ ጋብቻ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑ በተሰበሰበው መረጃ ከተለዩ ግኝቶቸ መካከል ተጠቅሷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በቤተሰብ ሕጉ አፈጻጸም ላይ ለተስተዋሉ ክፍተቶች እና ችግሮች የመፍትሔ ሐሳቦች ያቀረቡ ሲሆን ከነዚህም መካከል ኅብረተሰቡ በክልሉ የቤተሰብ ሕግ ላይ ግንዛቤውን እንዲያጎለብት ሕጉን የማስተዋወቅና የማስገንዘብ ተግባራት እንዲከናወኑ፣ በሕጉ አፈጻጸም ዙሪያ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ስትራቴጂያዊ አጋርነት በመፍጠር የሚጠበቅባቸውን ግዴታዎች፣ ኃላፊነቶችና ሚናዎችን እንዲውጡ፤ ሴቶች እና ሕፃናት የሚደርስባቸውን የመብቶች ጥሰት ወደሚመለከተው የፍትሕ አካል በመውሰድ መብቶቻቸውን የመጠየቅ እና የመጠቀም ዐቅም ማጎልበት እና የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ባረጋገጠ እንዲሁም የማኅበረሰቡን ባህል፣ እምነት፣ ወግ፣ ልማድ እና የአኗኗር ዘይቤ ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የክልሉን የቤተሰብ ሕግ የማሻሻል ሥራዎች እንዲሠሩ የሚሉ ምክረ ሐሳቦች ይገኙበታል። በውይይቱ የተሳተፉ በሴቶችና ሕፃናት መብቶች ላይ አተኩረው የሚሠሩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የሲቪል ማኅበራት ተወካዮችም በቀጣይ ለተለዩት ክፍተቶች መፍትሔ ለመሥጠት ለሚያደርጓቸው ተግባራዊ እንቅሰቃሴዎች የጋራ ዕቅድ ለማዘጋጀትና በትብብር ለመሥራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር የምስራች ለገሰ
የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር የምስራች ለገሰ

የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር የምስራች ለገሰ በጋምቤላ የቤተሰብ ሕግ አፈጻጸም የታዩ ክፍተቶችን በሚገባ ለመመለስ የማኅበረሰቡን ወግ፣ ባህል፣ ዕሴቶች እና የአኗኗር ዘይቤ ያማከለ እንዲሁም ማኅበረሰቡ የሚያውቀውና የተወያየበት የቤተሰብ ሕግ የሚያስፈልግ መሆኑ በአንጻሩም በሴቶችና ሕፃናት መብቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያደርጉ አስተሳሰቦችን የሚቀርፍና ኅብረተሰቡ አሁን ያለበትን የእድገት ደረጃ ከግምት ያስገባ ሆኖ መሻሻል እንዳለበት ገልጸዋል።