የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የፍትሕ ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ያላቸው የተደራሽነት ሁኔታ ላይ ባካሄደው ክትትል የተለዩ ግኝቶችንና ምክረ ሐሳቦችን ለባለድርሻ አካላት ያቀረበባቸውና የተወያየባቸው ተካታታይ የምክክር መድረኮችን ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተዘጋጀው መድረክ አጠናቋል፡፡ የውይይት መድረኩ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች እና የፍትሕ ጽሕፈት ቤቶች ላይ በተከናወነ ክትትል የተለዩ ግኝቶች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ኢሰመኮ ቀደም ሲልም በአፋር፣ በአማራ እና በሶማሊ ክልሎች ባደረጋቸው ክትትሎች የተገኙ ውጤቶችን ሰኔ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ እንዲሁም የኦሮሚያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች ግኝቶችን ደግሞ ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በጅማ ከተማ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አቅርቦ ውይይት አካሂዷል፡፡

የሰብአዊ መብቶች ክትትሉ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ወደ ፍትሕ ተቋማት ሲሄዱ የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመለየት እና ምክረ ሐሳቦችን ለማመላከት ያለመ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ከተማ እና በ6 ክልሎች ሥር በሚገኙ 23 ፍርድ ቤቶች እና 18 የፍትሕ ጽሕፈት ቤቶች በክትትሉ ተሸፍነዋል፡፡ በምክክር መድረኮቹ በክትትሉ የተለዩ ተቋማዊ፣ ከባቢያዊ እና የመረጃና ተግባቦት ተደራሽነት ክፍተቶች እንዲሁም የአመለካከት ተግዳሮቶች በክትትሉ ለተሸፈኑ ተቋማት ተወካዮች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ማኅበራት እንዲሁም ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

አብዛኛዎቹ ፍርድ ቤቶችም ሆኑ የፍትሕ ጽሕፈት ቤቶች አካል ጉዳተኛ እና አረጋዊ ተገልጋዮችን አካቶ ለማስተናገድ የሚያስችል ተቋማዊ ሕጎች፣ መመሪያዎች ወይም አሠራሮች የሌላቸው መሆኑ እና የችሎት አደራሾችን ጨምሮ አብዛኛዎቹ አገልግሎት መስጫ ሕንጻዎች/ቢሮዎች ከባቢያዊ ተደራሽነት የሌላቸው መሆኑ በውይይት መድረኮቹ  ተነስቷል፡፡ በተለይም ተቋማቱ ለዐይነ ሥውራን፣ መስማት ለተሳናቸው፣ የአእምሮ እድገት ውስንነት ወይም የማኅበረ-ሥነ ልቦና ጉዳት ላለባቸው ባለጉዳዮች የጉዳት ዓይነታቸውን ታሳቢ ያደረገ የመረጃና ተግባቦት አማራጭ ሥርዓት (ማለትም፡- የብሬይል፣ የድምጽ ቅጂ፣ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ፣ የማኅበረ ሥነ-ልቦና ባለሙያ…) በተሟላ ሁኔታ ለማቅረብ የሚያስችል ዐቅም የሌላቸው መሆኑ በተጨማሪነት ተመላክቷል፡፡ በተጨማሪም  ክትትል የተደረገባቸው የፍትሕ ተቋማት የሚመደብላቸው በጀት ውስን ቢሆንም በቀላል ወጪዎች መስተካከል የሚችሉ ከባቢያዊና ተቋማዊ የተደራሽነት ጉድለቶች እንደተስተዋሉ ተነግሯል፡፡

ተሳታፊዎች በበኩላቸው ኮሚሽኑ አገልግሎት በሚሰጡበት ቦታ ተገኝቶ ክትትል ማድረጉ እና የውይይት መድረኮቹ ላይ በመሳተፋቸው ያሉ ክፍተቶችን በተሻለ ሁኔታ መለየት መቻላቸውን  ገልጸዋል፡፡ ምክረ ሐሳቦቹን ለመፈጸም በተለይም ከበጀት ጋር የተገናኙ ተግዳሮቶችን ጠቁመው በቀጣይ ለጉዳዩ የሚሰጡትን ትኩረት እንደሚጨምሩ አስረድተዋል፡፡ የሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል ምክር ቤቶች እና የፋይናንስ ተቋማት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት እንዲሰጡም በውይይቱ ላይ ጥሪ ቀርቧል፡፡

በውይይት መድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ የፍትሕ ተደራሽነት መብት ለአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ሌሎች ሰብአዊ መብቶቻቸውን በተሟላ ሁኔታ ለመጠቀም የሚያስችላቸው ቅድመ ሁኔታ መሆኑን ገልጸው የክትትሉን አስፈላጊነት፣ ዓላማና የሚጠበቁ ውጤቶች በዝርዝር አስረድተዋል። ኮሚሽነር ርግበ አክለውም በክትትሉ ግኝቶች መነሻነት የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን በክትትሉ ከተሸፈኑ ፍርድ ቤቶች እና የፍትሕ ጽሕፈት ቤቶች በተጨማሪ ሌሎች አካላትም እንዲተገብሩ አሳስበዋል፡፡