የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የግል የጤና ተቋማት ለኅብረተሰቡ የፋይናንስ ተደራሽነታቸውንና የጤና መብት አተገባበር እና በግንባታ ዘርፍ ደኅንነቱ የተጠበቀና ጤናማ የሥራ ሁኔታ መብት አተገባበር ዙሪያ በ2015 ዓ.ም. በሠራቸው የክትትል ሪፖርቶችን መሠረት በማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በቦንጋ ከተማ መስከረም 23 እና 24 ቀን 2016 ዓ.ም. የውትወታ መድረኮች አካሄደ። የመድረኮቹ ዓላማ በክትትል ሪፖርቶቹ የተለዩ ግኝቶችን መሠረት በማድረግ የተሰጡትን ምክረ ሐሳቦች ለባለድርሻ አካላት በማስገንዘብ መብቶቹ በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡
የግል የጤና ተቋማት ለኅብረተሰቡ የፋይናንስ ተደራሽነታቸውንና የጤና መብት አተገባበርን አስመልክቶ በተካሄደው የውትወታ መድረክ ከኮሚሽኑ ባለሙያዎች በተጨማሪ ከክልሉ፤ የጤና ጥበቃ ቢሮ እና የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን፤ ከክልሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ እና የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ኤጀንሲ፤ ከተለያዩ የግል ጤና ተቋማት፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እና በጤና አገልግሎት ቁጥጥርና አቅርቦት ላይ ከሚሠሩ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በጤና ዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎቶች ለኅብረተሰቡ ያላቸው የፋይናንስ ተደራሽነት እና የጤና መብት አተገባበር በሚመለከት በኮሚሽኑ የተደረገው የክትትል ሪፖርት ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል፡፡ የግሉ የጤና ዘርፍ ለጤና አገልግሎት ዋጋ ንረት ያለው ሚና እና በዘርፉ የሚጠየቁ ክፍያዎች መጠን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ጉዳዮች፣ ግለሰቦች በግል ተቋማት እንዲገለገሉ የሚያስገድዱ ምክንያቶች፣ ለግሉ የጤና ዘርፍ የመንግሥት ድጋፍ፣ ቁጥጥር እና ክትትል፣ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሻሻል የሚረዱ ተግባራት እና በዘርፉ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ዙርያ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱም የሚስተዋሉ ችግሮችን እንዴት መቅረፍ እንደሚቻል፣ በክትትል ሪፖርቱ የተለዩ ምክረ ሐሳቦች ስለሚተገበሩባቸው መንገዶች እና በቀጣይ ከእያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ስለሚጠበቁ ተግባራት አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡
በተመሳሳይ የግንባታ ዘርፍ ደኅንነቱ የተጠበቀና ጤናማ የሥራ ሁኔታ መብት አተገባበርን በተመለከት በተካሄደው መድረክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የግንባታ ዘርፉ የሚመለክታቸው መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። በግንባታ ዘርፍ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ጤናማ የሥራ ሁኔታ መብት አተገባበርን በሚመለከት ኮሚሽኑ በአምስት ከተሞች ባካሄደው ክትትል የተለዩ ግኝቶች ማለትም ባለድርሻ አካላት ስለመብቱ ያላቸውን ግንዛቤ፣ የሥራ ደኅንነት እና ጤንነት መብት የአተገባበር ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማት ተቋማዊ አደረጃጀት፣ የአደጋ ሥጋትን ወይም በጤና ላይ ሊደርሱ የሚችሉ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ለመከላከል እና ለማስቀረት በአሠሪዎች የሚወሰዱ እርምጃዎችን፣ በዘርፉ ያለውን የሠራተኛ ማኅበራት እና የሠራተኞች ተሳትፎ እንዲሁም ለጉዳት ተጋላጭ ለሆኑ ሠራተኞች የሚደረግ ልዩ ጥበቃን በተመለከተ የክትትሉ ግኝቶች ለተሳታፊዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በተጨማሪም የሥራ ሁኔታ ክትትል፣ ቁጥጥር እና ድጋፍ ተግባራት፣ በዘርፉ በብዛት የሚስተዋሉ አደጋዎች፣ በሽታዎች እና ምክንያቶቹ፣ በዘርፉ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ጤናማ የሥራ ሁኔታ መብትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ መልካም ተሞክሮዎች እና ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ተነስተው ውይይት ተደርጓል።
ተሳታፊዎች የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት በማድረግ በግንባታ ዘርፍ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ጤናማ የሥራ ሁኔታ መብት አተገባበር ተግዳሮቶችን እና መልካም አጋጣሚዎችን በማንሳት ተውያይተዋል። በክትትል ሪፖርቱ የተለዩ ምክረ ሐሳቦች ስለሚተገበሩባቸው መንገዶች እና በቀጣይ ከእያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ምን እንደሚጠበቅ ያላቸውን አስተያየትም ሰጥተዋል።
በኢሰመኮ የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ብራይትማን ገብረሚካኤል በክትትል ግኝቱ የተለዩትን ክፍተቶች ለማሻሻል ሁሉም ተሳታፊዎች ድርሻቸውን እንዲወጡ እና የግል የጤና ተቋማት ለኅብረተሰቡ በገንዘብ ተደራሽ እንዲሆኑ በማስቻል የጤና መብት በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አክለውም በግንባታ ዘርፉ ከአደጋ ነጻ የሆነና ጤናማ የሥራ ሁኔታ መብትን ሙሉ ተግባራዊነት ለማረጋገጥ በጋራ መሥራት አስፈላጊ በመሆኑ ባለድርሻ አካላትን አስተባብሮ እና አቀናጅቶ የሚመራ ጠንካራ ሥርዓት መዘርጋት አጽንዖት ሊሰጠው እንደሚገባ አስረድተዋል።