የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ ጋምቤላ ወረዳ፣ ጎግ ወረዳ እና ጋምቤላ ከተማ ከግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. አንስቶ በተከሰቱ ግጭቶች እና የጸጥታ መደፍረስ የተነሳ በደረሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ላይ ከመስከረም 20 እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ያከናወነውን ምርመራ እንዲሁም ከመስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም. በኋላ በደረሱ ጥቃቶች ዙሪያ እና በመንግሥት የተወሰዱ እርምጃዎችን አስመልክቶ ተጨማሪ ክትትል በማድረግ ያሰባሰባቸውን መረጃዎች እና ማስረጃዎች የሚያካትት ባለ 15 ገጽ የምርመራ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ኢሰመኮ ግጭት ወደተከተሰባቸው ቦታዎች በአካል በመሄድ ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ከዐይን ምስክሮች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ቃለ መጠይቆች እና የቡድን ውይይቶች አድርጓል፡፡ በተጨማሪም በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ መንግሥት የጸጥታና አስተዳደር አካላትን እንዲሁም የፌዴራል ተቋማትን በማነጋገር መረጃዎችንና ማስረጃዎችን አሰባስቧል።

በሪፖርቱ እንደተመለከተው ግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢታንግ ልዩ ወረዳ ሥር በሚገኝ ፒኝዋ ቀበሌ ነዋሪ የነበሩ አንድ ግለሰብ መጥፋታቸውን ተከትሎ፣ በፒኝዋ ቀበሌ እና አጎራባች በሆነው በሌር ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል በተነሳ ግጭት በወቅቱ በርካታ ሰዎች መሞታቸውን፣ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ የግለሰቦች እና የተቋማት ንብረት ላይ ጉዳት እና ዘረፋ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚሁ ግጭት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በጎግ ወረዳ፣ ጋምቤላ ወረዳ እና ጋምቤላ ከተማ ከግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. እስከ ጥር ወር 2016 ዓ.ም. በተለያዩ ወቅቶች በሰዎች ሕይወት እና በንብረት ላይ ተጨማሪ ጉዳት ደርሷል። ኢሰመኮ ማረጋገጥ በቻለው መረጃዎች እና ማስረጃዎች መሠረት ቢያንስ የ138 ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ 113 ሰዎች ላይ አካል ጉዳት መድረሱን እንዲሁም በግለሰቦች እና ተቋማት ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን በሪፖርቱ በዝርዝር ተካቷል፡፡

ከግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በነበሩ ግጭቶች እና ጥቃቶች በክልሉ የተለያዩ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በሚኖሩ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ላይ በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ እንዲሁም ከመጠለያ ጣቢያ ውጪ ለምግብ ፍለጋ እና ለተለያዩ ጉዳዮች ሲንቀሳቀሱ በታጠቁ ቡድኖች እና ግለሰቦች በደረሰ ጥቃት ብዙ ሰዎች መገደላቸውን እና የአካል ጉዳት መድረሱን ሪፖርቱ አካቷል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ስደተኞችም ጭምር በእነዚሁ ግጭቶች ተሳታፊ እንደነበሩ ነዋሪዎች እና የመንግሥት አካላት ያስረዳሉ።

የጋምቤላ ክልል መንግሥት ይህ ሪፖርት ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ ግጭቱ በተከሰተበት ኢታንግ ልዩ ወረዳ ከማኅበረሰቡ ጋር በተለያየ ጊዜ ሰፊ እና ተደጋጋሚ የሰላም እና የዕርቅ ውይይቶች ያከናወነ ሲሆን፤ በወንጀል ድርጊት ላይ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ የአስተዳደር አመራሮች እና የጸጥታ አባላት ተጠያቂነት የማረጋገጥ እርምጃዎችም ተጀምረዋል፡፡ በተጨማሪም የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር ተደጋጋሚ ግጭት እና ጥቃት በሚከሰትባቸው ስፍራዎች ላይ የፌዴራል ፖሊስ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የክልሉን የጸጥታ ኃይሎች በመመደብ አካባቢውን የማረጋጋት እና ሰላም የማስፈን ጥረቶችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።

የጋምቤላ ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ከደቡብ ሱዳን የመጡ ስደተኞችን ተቀብሎ የሚያስተናገድ እንደመሆኑ በስደተኞች እና ተቀባይ ማኅበረሰብ መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችና ግጭቶችን ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ከስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት (RRS) እንዲሁም ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ቢገኝም፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቂ የጸጥታ ኃይሎችን ግጭቶች በተደጋጋሚ በሚከሰትባችው ስፍራዎች በቋሚነት መመደብን ጨምሮ የሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረትን ይሻል፡፡

በክልሉ መንግሥት የተጀመሩ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራዎች እንዲቀጥሉ እና በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ተገቢውን ካሳ እንዲያገኙ ሊደረግ እንደሚገባ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አሳስቧል፡፡ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የክልሉ መንግሥት ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ እያከናወነ የሚገኘው አካባቢውን የማረጋጋት እና ሰላም የማስፈን ሥራዎች በእጅጉ የሚበረታቱ መሆኑን አስታውሰው፤ “የተሟላ ፍትሕ የሚረጋገጠው ጥፋተኞች ተጠያቂ ሲሆኑ፣ የተበደሉ ሲካሱና ለወደፊትም ተመሳሳይ አደጋ እንዳይከሰት አስፈላጊ እርምጃዎች ተግባራዊ ሲደረጉ ስለሆነ ለዚህ ውጤት በቁርጠኝነት መሥራት መቀጠል አለበት” በማለት ጥሪ አቅርበዋል።