የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ 
መስከረም 26 ቀን 2015 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በጋምቤላ ከተማ ላይ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) እና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ በጋምቤላ ክልል የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ቡድኖቹ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አስመልክቶ ያከናወነውን የምርመራ ሪፖርት መስከረም 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። 

በሪፖርቱ በዝርዝር እንደተመለከተው ከሰኔ 7 እስከ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ሲቪል ሰዎች ላይ የደረሱትን ጉዳቶች አስመልክቶ ኮሚሽኑ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ፣ ከክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት፣ ከፌዴራል ፖሊስ የምዕራብ መምሪያ ጋምቤላ ቅርንጫፍ ሬጅመንት፣ ከከተማው ማዘጋጃ ቤት እና ከጋምቤላ አጠቃላይ ሆስፒታል ስለ ጉዳዩ መረጃ እና ምላሽ ተቀብሏል። የፌዴራል ፖሊስ የምዕራብ መምሪያ ጋምቤላ ቅርንጫፍ ለኮሚሽኑ በሰጠው ምላሽ በሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ኦነግ ሸኔ እና ጋነግ ታጣቂዎች በከፈቱት ውጊያ ከመንግሥት በኩል “የፌደራል ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ኃይሎች እና መደበኛ ፖሊሶች መሳተፋቸውን”፤ እንዲሁም “በውጊያው ወቅት በተወሰነ መልኩ የሰው እንቅስቃሴ በከተማ ውስጥ ስለነበር፤ በበራሪ ጥይቶች የተመቱ ሲቪል ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ” ግምት የነበራቸው ቢሆንም፣ “ከውጊያው በኋላ ባደረጉት ማጣራት የክልሉ ልዩ ኃይሎች በተለይ ሰኔ 8 እና 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በከተማው በሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃት እንዳደረሱ መረዳታቸውን” ገልጸዋል። 

አክለውም መረጃው እንደደረሳቸውም ከሚመለከተው የመንግሥት ኃላፊ ጋር በመነጋገር ድርጊቱ መቆም እንዳለበት፣ ጥቃት አድራሾችም በሕግ አግባብ መጠየቅ እንዳለባቸው፣ በድርጊቱም የተነሳ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ካሳ እንዲከፈላቸው አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ለኢሰመኮ አስረድተዋል። ከሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ ፕሬዝዳንት የሚመራ ሕዝባዊ ውይይት ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከክልሉ ምሁራን፣ ከከተማው ነዋሪዎች እና የክልሉ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር መደረጋቸውንም ጨምረው አስረድተዋል፡፡ 

ሆኖም የሪፖርቱን ይፋ መደረግ ተከትሎ በማኅበራዊ ትስስር ድረ ገጾች እና መገናኛ ብዙኃን የተሳሳተ፣ አነሳሽ እና ዛቻ ያዘሉ መረጃዎች ሲሰራጩ፤ እንዲሁም በኢሰመኮ ባልደረቦች ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ መልእክቶች ሲዘዋወሩ ቆይተዋል። ኮሚሽኑ ጉዳዩን ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር መፍታት እንደሚቻል በማመን ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቦ ቆይቷል። 

ሆኖም መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በቡድን ሆነው የመጡ ሰዎች ወደ ኢሰመኮ ጋምቤላ ጽሕፈት ቤት በመሄድ የተለያዩ የጥፋት ድርጊቶችን የፈጸሙ ሲሆን፣ በኢሰመኮ ባልደረቦች ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ አድርሰዋል። እንዲሁም በከተማዋ የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ሥራዎችን በሚያከናውኑ ሌሎች ድርጅቶች ላይ ተመሳሳይ ጥፋት አድርሰው ድርጅቶቹ “ከከተማው ለቅቀው እንዲወጡ” አስፈራርተዋል። 

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ኮሚሽኑ በሕገ መንግሥት የተቋቋመ ፌዴራል የብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋም መሆኑንና የኮሚሽኑ ሠራተኞችም በአዋጅ የልዩ መብት ጥበቃ የሚደረግላቸው መሆኑን አስታውሰው፣ “ኮሚሽኑ የክትትል እና የምርመራ ሥራውን በሚያከናውንበት ወቅት የተለያዩ ተግዳሮቶች የሚገጥሙት ቢሆንም፤ ይህንን ዐይነት በብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋም እና ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና በክልሉ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ምልከታ የሚጥል በመሆኑ የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት ተባብረው በአፋጣኝ እንዲያስቆሙ ኮሚሽኑ በጥብቅ ያሳስባል” ብለዋል። ከሰኔ 7 እስከ ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጎጂዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች አሁንም ሟቾች የተቀበሩበትን ቦታ ለማወቅ እና ፍትሕ ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ በመሆናቸው የኮሚሽኑ ምክረ ሃሳቦች በአፋጣኝ እንዲተገበሩ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በድጋሚ አስታውሰዋል።