የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በ6ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ወቅት ምርጫ ባልተካሄደባቸው የአፋር እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች፣ ድጋሚ ምርጫ እንዲደረግባቸው ውሳኔ በተሰጠባቸው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስቃን እና ማረቆ አካባቢዎች ውስጥ በሚገኙ 29 የምርጫ ክልሎች ውስጥ (ለ9 የተወካዮች ምክር ቤት እና ለ 26 የክልል ምክር ቤቶች) እና በሶማሊ ክልል የጅግጅጋ ከተማ የሚካሄዱትን የምርጫ ሂደቶች የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሚያደርግ መሆኑን አስታውቋል። ኢሰመኮ በተሻሻለው መቋቋምያ አዋጁ ቁጥር 210/2012 አንቀጽ 6(11) መሠረት በ2013 ዓ.ም. የተካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ እንዲሁም በቀድሞው ደቡብ ክልል ጥር 29 ቀን 2015 እና ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. የተደረጉት ሕዝበ ውሳኔዎች የሰብአዊ መብቶች ክትትል በማድረግ ሪፖርቱን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

የኢሰመኮ የምርጫ ወይም የሕዝበ ውሳኔ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ክትትል በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅት እና በድኅረ ምርጫ ወቅት የሚከናወን ሲሆን፣ ክትትሉ በዋናነት በእነዚህ ሂደቶች ወቅት ተፈጻሚ ሊሆኑ የሚገባቸውን የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች እና መርሖችን መሠረት የሚያደርግ ነው። ከአራቱም ክልሎች በተመረጡ ከ200 በላይ የምርጫ ጣቢያዎች የሚሰማሩ የኢሰመኮ የክትትል ባለሞያዎች በምርጫ ወቅት ከሚያደርጉት የመስክ ምልከታ በተጨማሪ መራጮችን፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችን፣ የፀጥታና የአስተዳደር አካላትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል እጩዎችን፣ ልዩ ልዩ ታዛቢዎችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማነጋገር መረጃ እና ማስረጃ የሚሰበስቡ ሲሆን፣ በተመሳሳይ መልኩ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚከናወነውን ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ አስመልክቶ የቅድመ ምርጫ ሂደት በተወሰኑ አካባቢዎች የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል። የኢሰመኮ የአቤቱታ መቀበያ ነጻ የስልክ መስመር 7307 በምርጫው ሂደት ወቅት የሚቀርቡለትን ቅሬታዎች እና ጥቆማዎችም የሚያስተናግድ ይሆናል።

በተጨማሪም ኢሰመኮ በ2013 እና በ2015 ዓ.ም. ያከናወናቸውን የሰብአዊ መብቶች ክትትሎች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲሁም ለሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል መንግሥት አካላት ያቀረባቸውን ምክረ ሐሳቦች በተመለከተ በተለያየ ወቅት ከምርጫ ቦርዱ እና ከባለድርሻዎች ጋር የውይይት መድረኮች ሲያካሂድ ቆይቷል። በተለይም በምርጫ ወቅት የሴቶችን ተሳትፎ በማጎልበት ረገድ ሊሻሻሉ የሚገቡ ጉዳዮችን እንዲሁም የምርጫ ቦርዱ፣ የመንግሥት አካላት እና የሲቪክ ማኅበረሰብ መተባበር ለአጠቃላይ የምርጫ ዑደቱ የሚኖረውን አስተዋጽዖ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ከመግባባት ተደርሷል። ኢሰመኮ በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ከተከናወነው ጠቅላላ ምርጫ አስቀድሞ ይፋ ያደረጋቸውን ባለ ስድስት ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳዎች የሚታወስ ነው።

በዚህም መሠረት የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች እና መርሖች በሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ተሳታፊ የሆኑ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግሥት አካላት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርችቶች እና የሚዲያ ተቋማት ሊያከብሯቸው፣ ሊፈጽሟችው እና ሊያስፈጽሟቸው የሚገባ መሆናቸውን በማስታወስ፣ በተለይም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ የሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን በምርጫው ሂደት የመሳተፍ መብት እንዲረጋገጥ አስፈላጊውን በማድረግ ረገድ እንዲሁም በሕግ የተደነገጉ የምርጫ ወቅት መመሪያዎችን በማክበር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ጥረት ሁሉ እንዲያደርጉ ኢሰመኮ ጥሪ አቅርቧል።

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል “የምርጫ ሂደት የበርካታ ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ የሚገለጽበት በመሆኑ የሁሉም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት የጋራ ትብብር የሚሻ ነው” ብለዋል። አክለውም በምርጫ ወቅት የሚነሱ ማንኛውም ዓይነት አቤቱታዎች እና ክርክሮችን የምርጫ ሕጉንና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ሕጎች ባከበረ መልኩ እንዲፈቱ ሁሉም ባለድርሻዎች ጥረታቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።