ጥገኝነት የመጠየቅ መብት ማለት ምን ማለት ነው?
ጥገኝነት የመጠየቅ መብት ማለት ከግጭት ወይም አደጋ የሚያመልጡ ሰዎች በሌላ ሀገር ከለላ የሚያገኙበት ሥነ ሥርዓት ነው። ሰዎች ለጥገኝነት ሲያመለክቱ በዘራቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በብሔራቸው፣ በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ወይም በአንድ የተወሰነ ማኅበራዊ ቡድን ውስጥ አባል በመሆናቸው ምክንያት የሚፈጸም ጥቃት ስለሚያስፈራቸው ጥበቃ እንዲደረግላቸው ነው። ከለላ ለማግኘትም ወደ ሀገራቸው ቢመለሱ በእርግጥ ወይም በተጨባጭ ሊደርስባቸው የሚችል ማሳደድ፣ ማሠቃየት፣ መንገላታት ስለመኖሩ ማሳየት አለባቸው።
ጥገኝነት የመጠየቅ መብት የሕግ መሠረቶች ምንድን ናቸው?
ዓለም አቀፍ እና ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፎች ተጨባጭ ከሆነ ጥቃት/ጭቆና ጥበቃ ለማግኘት ጥገኝነት የመጠየቅ መብትን እና ሂደቶችን ይደነግጋሉ። ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ (Universal Declaration of Human Rights) አንቀጽ 14 ከጥቃት/ጭቆና ሸሽቶ በሌሎች ሀገሮች ጥገኝነት የመጠየቅ መብትን እውቅና ሰጥቷል። ማን እንደ ስደተኛ እንደሚቆጠር እና ሀገራት ለጥገኝነት ጠያቂዎች ከለላ ለመስጠት ያለባቸውን ግዴታዎች ከመዘርዘር አኳያ እ.ኤ.አ. በ1951 የወጣው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ስምምነት እና እ.ኤ.አ. በ1967 የስደተኞች ሁኔታን ለመደንገግ የወጣው ፕሮቶኮል ጥገኝነትን ለተመለከቱ ሕጎች መሠረት በመሆን ያገለግላሉ። በዚህም መሠረት ስደተኛ የሚለው ቃል፡-
“በዘሩ፣ በኃይማኖቱ፣ በዜግነቱ፣ የአንድ ማኅበራዊ ቡድን አባል በመሆኑ ወይም በፖለቲካ አመለካከቱ ምክንያት በእርግጥ ወይም በተጨባጭ ማሳደድ ወይም አደጋ ወይም እንግልት ወይም ሥቃይ ይደርስብኛል ብሎ በመስጋቱ ምክንያት ከዜግነት ሀገሩ የተሰደደና በእነዚሁ ክስተቶች ምክንያት የዜግነት ሀገሩን ጥበቃ ለማግኘት ያልቻለ ወይም ያልፈለገ እንደሆነ፤” የሚል ትርጓሜ ተሰጥቶታል።
እነዚህ ስምምነቶች ስደተኞች በሕይወታቸው ወይም በነጻነታቸው ላይ ከባድ አደጋ ወደሚያጋጥማቸው ሀገራት እንዳይመለሱ ዋስትና በመስጠት ለጥገኝነት ጠያቂዎች አያያዝ ዓለም አቀፋዊ መርሖችንም ደንግገዋል።
በአህጉር ደረጃ የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀጽ 12(3) እና እ.ኤ.አ. በ1969 የስደተኞችን ልዩ ገጽታዎች ለማስተዳደር የጸደቀው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የስደተኞች ስምምነት ጥገኝነት የመጠየቅ እና የማግኘት መብትን በጉልህ የሚደነግግ ከመሆኑ ባሻገር ከጥበቃ ጋር የተያያዙ በርካታ ቁልፍ ድንጋጌዎችን ያስቀምጣል።
ኢትዮጵያ ከላይ የተጠቀሱትን ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ሰነዶች አጽድቃለች። በተጨማሪም የኢትዮጵያን የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች አያያዝ እና ጥበቃ የሕግ ማዕቀፍን የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1110/2019 ደንግጓል። አዋጁ ጥገኝነት የመጠየቅ መብትን የሚያረጋግጥ ሲሆን ከጥቃት የሚሸሹ ደግሞ ጥበቃ እና ድጋፍ እንዲያገኙ ዋስትና ይሰጣል። አዋጁ ጥገኝነት ለመጠየቅ ልዩ ሥነ ሥርዓቶችንም አካቷል። የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጥበቃ ለመስጠት ራሱን የቻለ የፌዴራል መንግሥት አካል ሆኖ የተቋቋመ ተቋም ነው። በአዋጁ በተደነገገው መሠረት ጥገኝነት ጠያቂዎችና ስደተኞች በሕጉ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል።
የጥገኝነት ጠያቂዎች መብቶች ምንድን ናቸው?
ጥገኝነት ጠያቂዎች የደኅንነት፣ ከጥቃት የመጠበቅ እና በተቀባይ ሀገር ሕጋዊ እውቅና ማግኘትን ጨምሮ አስፈላጊ አገልግሎቶችን ማለትም የጤና፣ የትምህርት እና የሕግ ድጋፍ አገልግሎት የማግኘት መብት፤ እንዲሁም የመሥራት፣ የመታወቂያ እና የጉዞ ሰነድ የማግኘት፣ ፍትሕ የማግኘት እና የመንቀሳቀስ መብትን እና ሌሎች በርካታ መብቶች አሏቸው። በተጨማሪም ጥገኝነት ጠያቂዎች የቤተሰብ አንድነት፣ ከዘፈቀደ እስራት የመጠበቅ፣ የስደተኝነት ሁኔታቸው የሚወሰንበት ፍትሐዊ እና ግልጽ አሠራር የማግኘት፣ እንዲሁም በተቀባይ ሀገር የመቆየት እና ተገድዶ ከመመለስ የመጠበቅ መብት አላቸው።
ተገድዶ ያለመመለስ መርሕ በኢትዮጵያ የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ ዕውቅና የተሰጠው ሲሆን ጥገኝነት ጠያቂዎች እና ስደተኞች ጥቃት ሊደርስባቸው ከሚችል፣ ማሰቃየት ወይም ሌላ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሊደርስባቸው ወደሚችሉበት ወደ ትውልድ ሀገራቸው እንዳይባረሩ ወይም በግድ እንዳይመለሱ ከለላ ይሰጣል። ነገር ግን ተገድዶ ያለመመለስ ፍጹም የሆነ መርሕ አይደለም። በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ስምምነት አንቀጽ 33 (2) እና በስደተኖች ጉዳይ አዋጅ አንቀጽ 11 ላይ እንደተደነገገው ጥገኝነት ጠያቂ ወይም ስደተኛ ለብሔራዊ ደኅንነት አደገኛ ስለመሆኑ አሳማኝ ምክንያቶች ካሉ ወይም በማኅበረሰብ ላይ አደጋ የሚጥል በመሆኑ ምክንያት በከባድ ወንጀል በመከሰስ የመጨረሻ ጥፋትና ፍርድ ከተፈረደበት ተገድዶ ያለመመለስ መርሕ ጥቅም ላይ ሊውል አይችልም።
ኢትዮጵያ ውስጥ ጥገኝነት ለማግኘት የት ጥያቄ ማቅረብ ይቻላል?
በስደተኞች ጉዳይ አዋጁ ላይ እንደተገለጸው ጥገኝነት ጠያቂ ማለት በሀገሪቱ ድንበር ወይም በሌላ በማንኛውም የመግቢያ ቦታ ሆኖ የስደተኝነት እውቅና እንዲሰጠው የሚጠይቅ መሆኑን ያስታወቀ ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ በስደተኛነት በሀገሪቱ ውስጥ ለመቆየትና እውቅና ለማግኘት አመልክቶ የባለሥልጣኑን ውሳኔ የሚጠብቅ ማንኛውም ሰው ወይም ቡድን ነው። ጥገኝነት ጠያቂዎች (ግለሰብም ሆነ ቡድን) በሀገሪቱ ድንበሮች ላይ ወይም ሌላ ማንኛውም የመግቢያ ቦታ ላይ ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ ከገቡ በኋላ በአቅራቢያቸው ላለው የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ቢሮ፣ ቅርንጫፍ ቢሮው ወይም ፖሊስ ጣቢያ ማመልከት ይችላሉ።
የኢትዮጵያ ስደተኞች ጉዳይ አዋጅ የግለሰብም ሆነ የቡድን የስደተኞች ሁኔታ (the prima facie procedure) የሚወሰንበት አሠራርን በግልጽ ዕውቅና የሚሰጥ ነው። የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት በአዋጁ ላይ በተደነገገው መሠረት የስደተኛነት መስፈርቶችን የሚያሟሉ ማናቸውንም ሰዎች እውቅና የመስጠት ሥልጣን አለው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ጥገኝነት መጠየቅ ምን ሂደትን ያካትታል?
ጥገኝነት የማግኘት ሂደት የጥገኝነት ጠያቂዎችን ሰብአዊ መብቶች ማክበር አለበት። ሂደቱ ጥቃትን፣ ኃይል የተቀላቀለባቸው ወይም ጉዳት የሚያስከትሉ ድርጊቶችን የሚሸሹ ግለሰቦች በብሔራዊ እና በዓለም አቀፍ ሕጎች በተደነገገው መሠረት ጥበቃ ማድረግ እና ጥገኝነት የመጠየቅ ፍላጎታቸውን ማረጋገጥ አለበት። ተቀባይ ሀገር የጥገኝነት ጠያቂዎችን ደኅንነት፣ ክብር እና ሰብአዊ አያያዝ በሂደቱ ሁሉ የመጠበቅ ግዴታ አለበት። በተጨማሪም ጥገኝነት ጠያቂዎች የስደተኝነት ሁኔታቸው ሲወሰን ፍትሐዊ እና ግልጽ አሠራር የማግኘት መብት አላቸው።
በስደተኞች አዋጁ ላይ በተደነገገው መሠረት ሂደቱ ሦስት ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው ደረጃ ለባለስልጣኑ ማመልከት ነው። ማመልከቻው በድንበር (በድንበር ቁጥጥር ማእከሎች በኩል) ወይም በፖሊስ ጣቢያዎች (ድንበሮችን ከተሻገሩ በኋላ) ወይም በስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ቢሮዎች ውስጥ ሊከናወን ይችላል። ሁለተኛው ደረጃ የምዘና እና ውሳኔ አሰጣጥን ያካትታል። የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ማመልከቻውን በመመርመር ውሳኔ ይሰጣል። ውሳኔው የስደተኝነት እውቅና መስጠት ወይም መከልከል ሊሆን ይችላል። ሦስተኛው ሂደት ይግባኝ የማለት መብት ነው። የቀረበው ማመልከቻ በስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ተቀባይነት ባላገኘ ጊዜ አመልካቹ ውሳኔው በደረሰው በስድሳ ቀናት ውስጥ ይግባኝ ወደ ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ሊያቀርብ ይችላል። የጉባኤው ውሳኔ የመጨረሻ ቢሆንም ውሳኔው የሕግ ስሕተት አለበት ተብሎ ሲታመን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ ሊታይ ይቻላል። ከላይ እንደተገለጸው ማንኛውም የስደተኝነት እውቅና ለማግኘት ያመለከተ ሰው ጥገኝነት በሚጠይቅበት ሀገር የመቆየት መብት አለው። ስለዚህ ግለሰቡ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት በማመልከቻው ላይ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ወይም ማመልከቻው ካልተሳካ፣ ይግባኝ የመጠየቅ መብቱን እስከ መጨረሻው እስኪጠቀም ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ የመቆየት መብት አለው።