የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ፍርድ ቤቶች እና የፍትሕ ጽሕፈት ቤቶች ለአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ባላቸው ተደራሽነት ላይ ያተኮረ ባለ 31 ገጽ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል። የዚህ የክትትል መነሻ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የተመረጡ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከባቢያዊ ተደራሽነት ላይ ከግንቦት 23 እስከ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ተደርጎ የነበረው ክትትል ሲሆን፣ በዚህም የፍርድ ቤቶቹ ሕንጻዎችና ምድረ-ግቢዎች ያላቸው የከባቢያዊ ተደራሽነት ክፍተት የፍትሕ ሥርዓት ተደራሽነት መብትን ለማረጋገጥ ተግዳሮት መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

ኮሚሽኑ የክትትል ሥራውን በማስፋት የፍርድ ቤቶችና የፍትሕ ጽሕፈት ቤቶች ሁለንተናዊ ተደራሽነትን በተመለከተ በተመረጡ በአፋር፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሊ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙ የፍትሕ ተቋማት ከታኅሣሥ 17 እስከ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የፌዴራል ፍትሕ ተቋማት ላይ ከታኅሣሥ 24 እስከ ጥር 6 ቀን 2015 ዓ.ም. የሰብአዊ መብቶች ክትትል አከናውኗል። በሪፖርቱም የክትትሉ ግኝቶች፣ መልካም ጅማሮዎች እንዲሁም የፍትሕ ተቋማት ለአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ያላቸውን ተደራሽነት እና አካታችነት ለማሻሻል የሚያስችሉ ዝርዝር ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል።

ኢሰመኮ በክትትሉ አካል ጉዳተኛ ባለሞያዎችን ያካተተ ቡድን በማሰማራት ከአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን፣ ከፍርድ ቤቶችና ፍትሕ ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ ከአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ማኅበራት እንዲሁም የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር በተደረጉ ቃለ መጠይቆች፣ በአካል ምልከታ እና ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሰነዶች በማመሳከር መረጃዎችና ማስረጃዎችን ሰብስቧል። በክትትሉ በአጠቃላይ ከ177 ሰዎች ጋር ቃለ መጠይቅ ተደርጔል፤ ከእነዚህም መካከል 39 አካል ጉዳተኞች እና 20 አረጋውያን በቃለ መጠይቁ ተሳትፈዋል።

ክትትሉ የተደራሽነት መብትን አስመልክቶ በአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ላይ የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና ለአካል ጉዳተኞች የሚደረጉ የተመጣጣኝ/ምክንያታዊ ማመቻቸት (Reasonable Accommodation) እርምጃዎች ያሉበትን ደረጃ ለይቷል። በሪፖርቱ ከተቋማዊ ተደራሽነት አንጻር በችሎቶች የክርክር ወይም የምስክር ቃል የማሰማት ሂደቶች ላይ የጾታዊ ጥቃት ተጎጂ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን፣ ለአካል ጉዳተኛ ሕፃናትና ሴቶች፣ ለአእምሮ ሕሙማን ወይም የአእምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ባለጉዳዮች የጉዳት ዐይነታቸውን እንዲሁም ተደራራቢ የመብት ጥሰት ተጋላጭነታቸውን ታሳቢ ያደረገ ምቹ የሆነ የአሠራር ሥርዓት አለመኖሩ ተመላክቷል።

በተጨማሪም ክትትሉ ከተደረገባቸው 41 የፍትሕ ተቋማት ውስጥ 4ቱ ከአንድ ወለል በላይ ባላቸው ሕንጻዎች ላይ እንደሚገኙ፣ ወደ ውስጥ ለመግባት ራምፕ (የተሽከርካሪ ወንበር መወጣጫ) ያልተገነባላቸው እና አሳንሰር ያልተገጠመላቸው መሆኑ፤ ክትትል በተደረገባቸው ሁሉም ፍርድ ቤቶችና ፍትሕ ጽሕፈት ቤቶች መስማት ለተሳናቸው ባለጉዳዮች የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ እንዳልተመደበ እንዲሁም አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶቻቸውን ከማወቅ እና እንዲከበርላቸው ከመጠየቅ አንጻር የግንዛቤ ክፍተቶች መኖራቸው በሪፖርቱ ከተለዩ ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ናቸው።

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ ‘‘ክትትሉ በስድስት ክልሎች እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች እና የፍትሕ ጽሕፈት ቤቶች ላይ ቢከናወንም፣ የግኝቶቹን ምክረ ሐሳቦች አካል ጉዳተኞችና አረጋውያንን የሚያስተናግዱ የፍትሕ ተቋማት ሁሉ ሊተገብሯቸው እና የአካል ጉዳተኞችንና አረጋውያንን ፍትሕ የማግኘት መብት ሊያረጋግጡ ይገባል’’ ብለዋል።