የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተሻሻለው መቋቋሚያ አዋጁ አንቀጽ 6 (11) መሠረት የተሰጠውን በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ክትትል የማድረግ ሥልጣን እና ኃላፊነት መነሻ በማድረግ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ማእከላዊ ኢትዮጵያ እና ሶማሊ ክልሎች በተደረገው የ6ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ‘‘ቀሪ’’ እና ድጋሚ ምርጫ ወቅት ያከናወነውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ግኝቶች የያዘ ­የመጀመሪያ ደረጃ (ቀዳሚ) ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሚያደርጉ 9 ሴቶች እና 22 ወንዶች በአጠቃላይ 31 ባለሙያዎችን አሰማርቶ የነበረ ሲሆን፤ ዛሬ ይፋ የተረደገው ቀዳሚ ሪፖርት በዋናነት ምርጫው በተካሄደባቸው ሁሉም ክልሎች ከተደራጁ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ተብለው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ መተከል ዞን፣ ጉባ ወረዳ ሥር የተደራጁትን 5 ልዩ የምርጫ ጣቢያዎችን ጨምሮ በተመረጡ 201 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተከናወነውን የድምጽ አሰጣጥ ሂደት የተመለከተ ነው። በዚህ ሪፖርት ያልተካተቱ ሌሎች የቅደመ ምርጫ፣ የምርጫ ዕለት እና የድኅረ ምርጫ ተግባራትን የተመለከቱ ግኝቶች የማጠናቀሩ ሂደት እንደተጠናቀቀ ይፋ የሚደረግ ይሆናል።

የኢሰመኮ የሴቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ በዕለቱ ተዘዋውረው የተመለከቷቸውን የምርጫ ጣቢያዎች በመጥቀስ፣ በቀጣይ ምርጫዎች የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኛ፣ ለአረጋውያን እንዲሁም ለሴት መራጮች ይበልጥ ምቹና ተደራሽ በሆኑ አካባቢዎች እንዲቋቋሙ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል። አክለውም የመራጮች መዝገብ ላይ የሚሞሉ እንደ ዕድሜ፣ አካል ጉዳተኝነት፣ የአካል ጉዳት ዐይነት የመሳሰሉ መረጃዎች የወጣቶች፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞችን የምርጫ ተሳትፎ መብት የተመለከቱ ፖሊሲዎችን ለመቅረጽ ግብዓት ሆነው የሚያገለግሉ በመሆናቸው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ለምርጫ አስፈጻሚዎች በመራጮች መረጃ አያያዝ ዙሪያ የሚሰጡ ሥልጠናዎችን እና ለዜጎች የሚሰጡ የመራጮች ትምህርቶችን እንዲያስፋፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ዝርዝር ሪፖርቱ ከዚህ በታች ተያይዟል፦

. . . 

ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በ4 ክልሎች የተካሄደው የ6ኛው ዙር ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ የሰብአዊ መብቶች ክትትል የመጀመሪያ ደረጃ (ቀዳሚ) ሪፖርት

መግቢያ

  1. የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በፌዴራል ሕገ መንግሥቱ መሠረት ነጻ የፌዴራል መንግሥት አካል ሆኖ በአዋጅ ቁጥር 210/1992 (በአዋጅ ቁጥር 1224/2012 እንደተሻሻለው) የተቋቋመና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆነ፣ ለሰብአዊ መብቶች መስፋፋት፣ መከበር እና ጥበቃ የሚሠራ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ነው፡፡ በተሻሻለው የኢሰመኮ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 6 (11) መሠረት ኢሰመኮ በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል የማድረግ ሥልጣን እና ኃላፊነት አለው፡፡
  2. የ6ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም.፣ በመስከረም ወር 2014 ዓ.ም. እና በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም. በ3 ዙሮች የተካሄደ ሲሆን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 547 መቀመጫዎች (የምርጫ ክልሎች) መካከል በ471 የምርጫ ክልሎች በዚሁ ወቅት ምርጫ ተካሂዶ ነበር፡፡ ቀሪዎቹ 76 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች በተለይ ከሰላምና ጸጥታ ጋር በተያያዘ ችግር ምርጫ ያልተካሄደባቸው በመሆኑ “ቀሪ ምርጫ” የሚደረግባቸው እንዲሁም በመራጮች ምዝገባ፣ በድምፅ አሰጣጥ እና ቆጠራ ሂደቶች ላይ በታዩ የአሠራር ክፍተቶች ምክንያት ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ውሳኔ የተላለፈባቸው ናቸው።
  3. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (ምርጫ ቦርድ) ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. አንስቶ በቀሪዎቹ የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ ለማካሄድ በማቀድ በመስከረም ወር 2014 ዓ.ም.፣ በታኀሣሥ ወር 2014 ዓ.ም.፣ በግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. እና በጥር ወር 2015 ዓ.ም. ዝግጅቱን ጀምሮ እንደነበረ ይታወሳል። ይኹንና፣ ምርጫው በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ መሻሻል ባለማሳየቱ እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅ ምክንያት ምርጫው ሳይከናወን ቆይቶ ነበር።
  4. በመጨረሻም መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ በተደረገው እና በልዩ ልዩ ምክንያቶች በተሻሻለው የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ከቀሪዎቹ የምርጫ ክልሎች መካከል በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በማእከላዊ ኢትዮጵያ እና በሶማሊ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 29 የምርጫ ክልሎች (ለ9 የተወካዮች ምክር ቤት እና ለ 26 የክልል ምክር ቤቶች መቀመጫዎች) የምርጫ ሂደቱ ዋና ዋና ተግባራት ተከናውነዋል። እነዚህም፦
    • የመራጮች ምዝገባ ከሚያዝያ 7 እስከ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም.፣
    • የእጩዎች ምዝገባ ከሚያዝያ 7 እስከ ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም.፣
    • የመራጮች ትምህርት (ለመራጮች ምዝገባ እና ለድምፅ መስጫ ዕለት) ከመጋቢት 30 እስከ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም.፣
    • የምረጡኝ ዘመቻ (ምርጫ ቅስቀሳ) ከሚያዝያ 7 እስከ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም.፣
    • ቅስቀሳ የማይደረግበት የጥሞና ጊዜ ከሰኔ 12 እስከ ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ እንዲሁም
    • የድምፅ መስጫ ሂደቱ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. የተከናወኑ ናቸው።
    • የምርጫ ዐይነቶች 
  5. በአፋር ክልል በ3 ዞኖች ሥር የሚገኙ 8 የወረዳ አስተዳደሮችን የሚሸፍነው ምርጫ የ6ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ‘ቀሪ ምርጫ ነው። በዞን 2 (ኪልበቲ ዞን) ስር የሚገኘው የዳሎል ምርጫ ክልል (ለክልል ምክር ቤት) ድጋሚ ምርጫ የሚደረግበት ነው።  
  6. በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያደረገው ሙሉ በሙሉ ቀሪ ምርጫ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በ3 ዞኖች ሥር የሚገኙ 17 ወረዳዎችን ሸፍኗል። በክልሉ ከተደራጁት የምርጫ ጣቢያዎች መካከል በመተከል ዞን፣ ጉባ እና ድባጤ ወረዳዎች 7 ልዩ ምርጫ ጣቢያዎች ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ተደራጅተዋል። 
  7. በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ሥር በሚገኘው ‘‘መስቃን እና ማረቆ 2’’ የምርጫ ክልል (ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤት) በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት በተለይም [በድምፅ መስጫ ዕለት በአብዛኛው ምርጫ ጣቢያ መራጮችን የሚያስገድድ የኃይል ተግባር የነበረ መሆኑ በማስረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ የድጋሚ ምርጫ እንዲከናወን በቦርዱ ውሳኔ የተሰጠበት ነው። በዚህ የምርጫ ክልል ድጋሚ ምርጫ ሲደረግ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።1 በዚህ የምርጫ ክልል ቀደም ሲል ከሚያዝያ 7 እስከ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ የመራጮች ምዝገባ ከተደረገባቸው 4 ምርጫ ጣቢያዎች በስተቀር በቀሪዎቹ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የመራጮች ምዝገባ እና ድምፅ አሰጣጥ ሂደት በተመሳሳይ ዕለት ተከናውኗል።  
  8. በተመሳሳይ በሶማሊ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ሥር በሚገኘው ‘‘ጅግጅጋ 2’’ የምርጫ ክልል (ለክልል ምክር ቤት) የተከናወነው ምርጫ በመስከረም 2014 ዓ.ም. ተደርጎ በነበረው ምርጫ ‘‘26 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ለአንድ ፓርቲ ድምፅ እንዲሰጥ [መደረጉ] በብዙ ምስክሮች በመረጋገጡ፣ 13 የምርጫ ጣቢያዎችን ታዛቢዎች መታዘብ አለመቻላቸው በመረጋገጡ [እና] ይህም ከውጤቱ ድምር ጋር ሲታይ ውጤት የሚቀይር መሆኑ ስለታመነበት’’2 ምርጫ ቦርድ ድጋሚ ምርጫ እንዲከናወንበት የወሰነበት ነው። በዚህ የምርጫ ክልል ላይም የመራጮች ምዝገባ እና ድምፅ አሰጣጥ ሂደት በተመሳሳይ ዕለት ተከናውኗል። 
    • የሰብአዊ መብቶች ክትትል
  9. ኢሰመኮ በምርጫ ወቅት የሚያከናውነው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ዓላማ በምርጫ ሂደት ያለውን የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታ መገምገም፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ስጋት ሲፈጠር ወይም ሲፈጸም ፈጣን የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ምክረ ሃሳብ ማቅረብና ክትትል ማድረግ እንዲሁም በምርጫ ሂደቱ የሚስተዋሉ መልካም ተሞክሮዎች እና ተግዳሮቶችን በመሰነድ ወደፊት በሚደረጉ ምርጫዎች የተሻለ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ባህል እንዲጎለብት አስተዋጽዖ ማድረግ ነው። 
  10. በዚህም መሠረት ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሚያደርጉ 31 ባለሙያዎችን (9 ሴቶች እና 22 ወንዶች) በተመረጡ አካባቢዎች አሠማርቷል። የኢሰመኮ ክትትል ባለሙያዎቹ የተሠማሩባቸውን አካባቢዎች እና የምርጫ ጣቢያዎች ለመለየት የተከተለው አሰራር የተቋሙን የበጀት እና የሰው ኃይል አቅም ታሳቢ በማድረግ፣ ለምርጫ ክትትል ተግባር ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን የተመጣጣኝ ትዝብት (proportional observation) እና ለተወሰነ ዓላማ የሚደረግ የናሙና ትዝብት (purposive sampling observation) ስልቶችን መሠረት ያደረገ ነው።  
  11. ከሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ምርጫው በተደረገባቸው አራቱም ክልሎች በሚገኙ አካባቢዎች የተሠማሩት የኢሰመኮ የክትትል ባለሙያዎች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ቃለ መጠይቆችን አድርገዋል፤ በተጨማሪም የመራጮች ትምህርት፣ የምርጫ ቅስቀሳ እና ቅስቀሳ የማይደረግባቸውን የጥሞና ቀናትን እንዲሁም በድምፅ መስጫው ዕለት የነበሩ ሁነቶችን በአካል በመገኘት ታዝበዋል። 
  12. ኢሰመኮ በቅድመ ምርጫ እና በድምፅ መስጫ ዕለት ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በጉባ ወረዳ ሥር ከተደራጁት ጣቢያዎች መካከል 5 ልዩ የምርጫ ጣቢያዎችን ጨምሮ በድምሩ 201 የምርጫ ጣቢያዎችን በክትትሉ ሸፍኗል።  
    • የክትትሉ ዋና ዋና ግኝቶች 
    • ቁልፍ እመርታዎች 
  13. በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫው ሳይደረግባቸው ከቀሩ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች በስተቀር ምርጫው በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች በተረጋጋ ሁኔታ እና አሳሳቢ የጸጥታ አደጋ እና ሥጋት ሳይደርስ መከናወኑ፤ 
  14. ምርጫ ቦርድ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በመራጭነት በመሳተፍ ሂደት ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ 7 ልዩ የምርጫ ጣቢያዎችን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ጉባ እና ድባጤ ወረዳዎች ያቋቋመ መሆኑ፤ 
  15. በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን፣ ማንቡክ ወረዳ ከድምፅ መስጫው ዕለት አንድ ቀን አስቀድሞ ተከስቶ ከነበረ የጸጥታ መደፍረስ ጋር በተገናኘ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ እስከ ረፋዱ 4 ሰዓት ድረስ ዘግይቶ ከጀመረባቸው የወረዳው አካባቢዎች በስተቀር፤ ኢሰመኮ ክትትል ባደረገባቸው አብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ በሰዓቱ የተጀመረና በሰዓቱ የተጠናቀቀ መሆኑ፤  
  16. የኢሰመኮ የክትትል ባለሙያዎች በተሰማሩባቸው ሁሉም አካባቢዎች በማንኛውም አካል ክልከላ ወይም መሰል እንቅፋት ሳያጋጥማቸው የክትትል ስራቸውን ማከናወን መቻላቸው፣ እንዲሁም 
  17. ምርጫ ቦርድ በተለይም በድምፅ መስጫው ዕለት ከኢሰመኮ ለተላኩለት አሳሳቢ ጉዳዮች ፈጣን ምላሽና የማስተካከያ እርምጃዎችን የወሰደ መሆኑ ናቸው፡፡ ለአብነት፦  
    • በመራጮች ላይ ጫና የሚያሳድሩ ወደ ምርጫ ጣቢያ የሚገቡ መራጮችን የመመዝገብ፣ የማነጋገር እና መሰል ተግባራት በታዩባቸው ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ድርጊቶቹን በፈጸሙ አካላት ላይ እርምጃ ተወስዶ ለቦርዱ እስከሚገለጽ ድረስ የምርጫ ሂደቱ በጊዜያዊነት እንዲቆም ተደርጎ የነበረ መሆኑ፣ በተለይም በመስቃን እና ማረቆ ምርጫ ክልል ውስጥ ስም እና መሰል ዝርዝር አድራሻ ባይኖራቸውም ማሕተምና ፎቶ ያለባቸው በርከት ያሉ መታወቂዎችን ያለ አግባብ ሲሰጡ የነበሩ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉና ምርጫውም እንዲቀጥል መደረጉ (ግለሰቡ ከሰዓታት በኋላ መለቀቃቸውን ኮሚሽኑ አረጋግጧል)፤ 
    • የመራጮች የነዋሪነት ማረጋገጫ ምስክርነት ቃል ፎርም እጥረት ማጋጠሙ ሪፖርት በተደረገባቸው ምርጫ ጣቢያዎች የተጓደለው ፎርም ተባዝቶ ለምርጫ ጣቢያዎቹ በፍጥነት እንዲደርስ በመደረጉ የቀበሌ መታወቂያ የሌላቸው ነዋሪዎች ነዋሪነታቸውን በምስክር እያስረዱ ለመምረጥ የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸቱ፤  
    • በምርጫ ጣቢያው አካባቢ ያለው ወረፋ ከመጠን በላይ የተጨናነቀ፣ መገፋፋትና ውጥረት ያለበት ነው በሚል ሪፖርት በቀረባባቸው ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የቦርዱ አስተባባሪዎች በቦታው ተገኝተው በማስተባበር መራጮች በአግባቡ ተሰልፈው እንዲመርጡ መደረጉ፤ 
    • ድምፅ ለመስጠት ባለው ወረፋ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ቅድሚያ እንዲያገኙ እየተደረገ አይደለም የሚል ቅሬታ በቀረበባቸው በተለይም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ቡለን መደበኛ እና ሺናሻ ልዩ ምርጫ ክልሎች ሥር ለሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች በቀረው ጊዜ ለሚመጡ ልዩ ድጋፍ ለሚሹ መራጮች ቅድሚያ እንዲሰጥ ቦርዱ ድጋሚ መመሪያ መስጠቱ እና ክትትል ማድረጉ ዋነኞቹ ናቸው። 
    • አሳሳቢ ክፍተቶች 
  18. ኢሰመኮ ክትትል ባደረገባቸው በአብዛኛዎቹ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ በምርጫ ጣቢያው ውስጥ ወይም በ500 ሜትር አቅራቢያ የደንብ ልብስ የለበሱ (አልፎ አልፎም የታጠቁ) የጸጥታ አካላት ታይተዋል። ምንም እንኳን የጸጥታ አካላቱ የምርጫ ጣቢያውን ጸጥታ በሚያደፈርሱ ሁኔታዎች ላይ የተሳተፉባቸው አሉታዊ አጋጣሚዎች በዕለቱ ባይመዘገቡም፤ በምርጫ ጣቢያው ኃላፊ በግልጽ ካልተፈቀደላቸው በስተቀር በምርጫ ጣቢያው 500 ሜትር አቅራቢያ መገኘት አልነበረባቸውም።  
  19. ክትትሉ በተከናወነባቸው የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ በሕግ ከተፈቀደላቸው ሰዎች (ከመራጮች፣ ከምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ከእጩ ወኪሎች፣ ከታዛቢዎችና ከቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት) ውጪ የሆኑ በተለይም የቀበሌ/ወረዳ አመራሮች እና የብልጽግና ፓርቲ አባላት በምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ መራጮች ላይ ጫና ሊያሳድሩ በሚችሉ መልኩ መራጮችን የመመዝገብ፣ የማነጋገርና የመሳሰሉ ድርጊቶች ላይ ሲሳትፉ ተስተውሏል። 
  20. በልዩ ልዩ ምክንያት በሕግ ከተፈቀዱ ቦታዎች ውጪ የሚደራጁ ምርጫ ጣቢያዎች ቁጥር ከቀደሙት ምርጫዎች አንጻር የቀነሱ እና የቦርዱም ጥረት ዕውቅና ሊሰጠው የሚገባው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በጅግጅጋ እና በመስቃን እና ማረቆ ምርጫ ክልሎች ላይ በግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች እና በአንድ የሃይማኖት ተቋም ትምህርት ቤት ውስጥ የተቋቋሙ 5 ምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን ኢሰመኮ ተመልክቷል። 
  21. የኢሰመኮ የክትትል ባለሙያዎች በተመለከቷቸው ምርጫ ጣቢያዎች ላይ በምርጫ ጣቢያ ደረጃ እንዲቋቋሙ የሚጠበቁት የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች አልተደራጁም። በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ ለሚነሳ ማንኛውም ዐይነት አቤቱታ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምላሽ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።  
  22. የድጋሚ ምርጫ በሚከናወንበት የመስቃን እና ማረቆ ምርጫ ክልል ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳና የድጋፍ ሰልፍ ማካሄዱን የኢሰመኮ የክትትል ባለሙያዎች ታዝበዋል። 
በምስሉ ላይ የሚታዩት በድምፅ መስጫው ዕለት ለኢሰመኮ ሪፖርት የተደረጉና በሰዎች በምርጫ የመሳተፍ መብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ አሳሳቢ ሁኔታዎች ናቸው። አሳሳቢ ሁኔታዎቹ ለምርጫ ቦርድ ሪፖርት የተደረጉ ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ በቦርዱ ፈጣን ምላሽ ያገኙና ማስተካከያ የተደረገባቸው ጉዳዮች ናቸው።  

ማጠቃለያ እና ምክረ ሐሳብ 

በአጠቃላይ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. የተከናወነው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት የጸጥታ አደጋ እና ሥጋት ሳይደርስ፣ ሰዎች ከመራጭነት ባሻገር በተመራጭነት፣ በምርጫ አስፈጻሚነት፣ በታዛቢነትና በመሳሰሉት ወሳኝ ተግባራት በሕዝባዊ ሂደቶች ላይ የመሳተፍ መብታቸውን ተግባራዊ ያደረጉበት መሆኑ ታይቷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሂደቱ የታዩ የምርጫ አስተዳደር ክፍተቶችን ለማስተካከል የሚወሰዱ የሕግ እና የአሠራር ማሻሻያዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ የመንግሥት አስተዳደር እና የጸጥታ አካላት በተለይም በድምጽ መስጫ ዕለት የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ በቂ የግንዛቤ ሥራ እንዲያከናውን እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ተገቢውን የእርምት እርምጃ እንዲወስድ እና ቅድሚያ እንዲያገኙ በምርጫ አዋጁ ጥበቃ ለተደረገላቸው አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ ነፍሰ ጡሮች እና ሌሎች ድጋፍ የሚሹ መራጮች በወጥነት ቅድሚያ እንዲያገኙ ለምርጫ አስፈጻሚዎች የሚሰጣቸውን ስልጠናዎች እንዲያስፋፋ ኢሰመኮ ምክረ ሐሳቡን ያቀርባል። በተጨማሪም፣ ቦርዱ ከሚመለከታቸው የክልል እና የፌዴራል መንግሥት አካላት ጋር በመተባበር ምርጫው በተከናወነባቸው አካባቢዎች ከምርጫ ውጤት መታወቅ ጋር በተገናኘ ሊፈጠሩ የሚችሉ የጸጥታ ሥጋቶች ካሉ አስቀድሞ ለመከላከል የሚረዱ እርምጃዎችን እንዲወስድ ያስፈልጋል።  


[1] https://www.facebook.com/permalink.php?story_fbid=1049769142472021&id=414693405979601

[2] https://www.facebook.com/permalink.php?story_fbid=1049769142472021&id=414693405979601