የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአፋር ክልላዊ መንግሥት ረቂቅ የቤተሰብ ሕግ ላይ ከሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከተባበሩት መንግስሥታት ድርጅት ሥርዓተ ጾታ እኩልነት እና የሴቶች ማብቃት ተቋም (UN Women)፣ አምረፍ ኸልዝ አፍሪካ (Amref Health Africa)፣ ከሕፃናት አድን ድርጅት (Save the Children)፣ ከኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር እንዲሁም ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር በሰመራ ከተማ ሐምሌ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. የከፍተኛ ኃላፊዎች የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የውይይቱ ዓላማ በክልሉ ረቂቅ የቤተሰብ ሕግ የተካተቱና መግባባት ላይ መድረስ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችን ለይቶ በመወያየት ረቂቁን ማዳበር እና የሚጸድቅበትን ሁኔታ ማገዝ ነው። በዚህም መሠረት የጋብቻ ዕድሜ፣ በጋብቻ ላይ ጋብቻ፣ ከፍቺ በኋላ በብቸኝነት የመቆያ ጊዜ፣ እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር፣ አባትነትን በፍርድ ቤት ማሳወቅን እንዲሁም በጉዲፈቻ ዙርያ ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በተጨማሪም የሌሎች ክልሎች እና ሀገራት ልምዶች የተቃኙ ሲሆን ከሃይማኖትና ከባህል አኳያ የሚነሱ የተለያዩ አመለካከቶችና ትንታኔዎችም ተደምጠዋል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም የአፋር ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት አባላት፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የሸሪዓ ፍ/ቤት፣ የክልሉ የፍትሕ ቢሮ፣ የሴቶችና የማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ተወካዮች እና ከሌሎች ቁልፍ ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎቸ ተሳትፈዋል።
ተሳታፊዎች የቤተሰብ ሕጉ የሴቶች እና ሕፃናት መብቶችንና ደኅንነት ጽንሰ ሐሳቦችን የሚያዳብሩ በምሳሌነት የሚወሰዱ የማኀበረሰቡን እሴቶች ከግምት በማስገባት፣ በሂደቱ የሴቶችና ሕፃናት ሐሳብን እና ፍላጎትን በማካተት እንዲሁም በረቂቁ ውስጥ በዝምታ የታለፉ ወሳኝ ነጥቦችን በዝርዝር በማስቀመጥ ረቂቁ ሊሻሻል እንደሚገባ ገልጸዋል። ሕጉን የማርቀቅ ሂደቱም በርካታ ዓመታትን የፈጀ በመሆኑ በውይይት የተገኙ ገንቢ ሐሳቦችን በማካተት እና አስፈላጊ ማሻሻያዎችን በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጽደቅና በሥራ ላይ ማዋል አስፈላጊ ስለመሆኑ አጽንዖት ተሰጥቷል።
የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ የቤተሰብ ሕግ በሴቶች እና በሕፃናት የሰብአዊ መብቶች መከበር ላይ ያለውን አንድምታ እና አንዳንድ አከራካሪ በሆኑ ነጥቦች ላይ ሌሎች ሀገራት ያላቸውን ተሞክሮ አጋርተዋል፡፡ ኮሚሽነሯ የክልሉ ረቂቅ የቤተሰብ ሕግ የሴቶችና የሕፃናት መብቶችን በሚገባ ያካተተ፣ ከሕገ-መንግሥታዊ እና ከሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች መርሖች ጋር የተጣጣመ እንዲሁም የሴቶችንና የሕፃናትን ተሳታፊነት እና ሙሉ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ሆኖ መውጣት ይኖርበታል ብለዋል።