የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. እስከ ሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም. በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊ እንዲሁም የቀድሞ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ላይ ትኩረት ያደረገ በወንጀል ተጠርጥረው ነጻነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች ዙሪያ ባከናወነው ብሔራዊ ምርመራ /National Inquiry/ የተለዩ ግኝቶችን እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን የያዘ ባለ 130 ገጽ ሪፖርት መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ይህንኑ ተከትሎ የብሔራዊ ምርመራውን ሪፖርት በማሰራጨት በምርመራው አጠቃላይ ሂደት፣ ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች አተገባበር ዙሪያ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች፣ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች ተወካዮች እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር ታኀሣሥ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል።
የውይይቱ ዓላማ በብሔራዊ ምርመራው ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ላይ በመወያየት በብሔራዊ ምርመራው ያልተካተቱ ጉዳዩችን ከተሳታፊዎች በመውሰድ በቀጣይ ነጻነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች እንዲጠበቁ ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡
በውይይት መድረኩ የብሔራዊ ምርመራው ዓላማ፣ አጠቃላይ ሂደት፣ ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ለተሳታፊዎች የቀረቡ ሲሆን፤ የብሔራዊ ምርመራው አካል የነበሩት አራቱ ግልጽ አቤቱታ መቀበያ መድረኮች የተካሄዱት ምንም ጉዳት ያለማድረስ መርሕ መሠረት መሆኑን፣ ተጎጂዎች እና ምስክሮች በመድረኩ በሰጡት ምስክርነት ምክንያት ለቂም-በቀል ጥቃት ወይም አጸፋዊ እርምጃዎች ወይም ድርጊቶች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ተገቢው ጥንቃቄና ዝግጅት በማድረግ፤ በተጎጂዎች እና ምስክሮች ላይ የሚፈጸሙ ወይም የሚሞከሩ የአካል ጉዳት፣ የትንኮሳ ወይም የማስፈራራት ድርጊቶችን የሚከታተል የድኅረ-ምርመራ ቡድን በማቋቋም ጭምር መሆኑ ተገልጿል።
የብሔራዊ ምርመራው ትኩረት ያደረገው ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ ያለውን ጊዜ ሲሆን ይኸውም በሀገር ደረጃ የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ መሠረት በማድረግ በመንግሥት የተሠሩ ተቋማዊ ለውጦችን እና እንደሀገር የተገቡ ቃል ኪዳኖች ትግበራን ለመለየትም ጭምር መሆኑ ተጠቁሟል። ብሔራዊ ምርመራው በዘጠኝ ክልሎች ለማከናወን ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ጥሰቱ በስፋት የታየባቸው ክልሎች፣ ያላቸውን የሕዝብ ብዛት እና የቆዳ ስፋት ከግምት በማስገባት በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሊ እንዲሁም በቀድሞ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ላይ ሊከናወን መቻሉ ተመላክቷል። በተጨማሪም በተደረገው ብሔራዊ ምርመራ አብዛኛዎቹ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የተፈጸሙት በግጭቶች፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና በስድስተኛው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ ዐውዶች ውስጥ በመሆናቸው በእንዲህ ዓይነት ወቅቶች ተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃዎች እንደሚያስፈልጉ ተነግሯል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የብሔራዊ ምርመራው ግኝቶች በየክልላቸው የሚገኙ ስልታዊ እና ተደጋጋሚ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በሚገባ ማሳየት የቻለ መሆኑን በመጥቀስ ለምክረ ሐሳቦቹ አፈጻጸም ትኩረት በመስጠት እንደሚሠሩ ገልጸዋል። በተጨማሪም በተሳታፊዎች የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን አፈጻጸም በተመለከተ በአፋጣኝ፣ በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ለመፈጸም የሚያስችል የድርጊት መርኃ ግብር ተዘጋጅቷል።
የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል ነጻነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሀገራዊ፣ ተቋማዊ እና በሁሉም ቦታዎች በስፋት የሚስተዋሉ በመሆናቸው የተለዩ ግኝቶችን እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን በመውሰድ ነጻነታቸውን ያጡ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች አስተማማኝ ጥበቃ የሚያገኙበትን፣ በአጥፊዎች ላይ ተጠያቂነት የሚረጋገጥበትን እንዲሁም ተጎጂዎች ካሳ የሚያገኙበትን ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ገልጸዋል።