የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከጥቅምት እስከ ታኅሣሥ ወር 2017 ዓ.ም. በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ እንዲሁም በሴቶች መብቶች፣ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች፣ በአረጋውያን መብቶች፣ በተጠርጣሪዎች እና በሕግ ታራሚዎች መብቶች ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን እና የአሰልጣኞች ስልጠናዎችን ለወጣቶች፣ ለማረሚያ ቤት ፖሊሶች፣ ለፖሊስ አባላት እና ሥራ ኃላፊዎች፣ ለአረጋውያን፣ ለሲቪል ማኅበራት እና ለመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች ሰጥቷል፡፡

ኢሰመኮ ከሰላም፣ አብሮነት እና መቻቻል አንጻር የወጣቶችን ሚና ለማሳደግ ያለመ የሰብአዊ መብቶች ስልጠና በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተለያዩ የወጣት ማኅበራት ለተውጣጡ 32 ወጣት አመራሮች እና አባላት በቡታጂራ ከተማ ከኅዳር 9 እስከ 13 ቀን 2017. ዓ.ም ሰጥቷል። በሌላ በኩል ኢሰመኮ ዮዝ አዌርነስ ኤንድ ማይንድሴት ግሮውዝ (Youth Awareness and Mindset Growth -YAMG) ከተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ጋር በመተባበር በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ ፅንሰ ሐሳብ፣ ሂደቶችና አላባዎች ዙርያ ወጣቶች በቂ ዕውቀት እንዲያገኙ እና በሂደቱ ለመሳተፍ ተነሳሽነት እንዲያዳብሩ በጅማ ከተማ ከጥቅምት 25 እስከ 29 ቀን 2017 ዓ.ም. የአሰልጣኞች ስልጠና አካሂዷል። በስልጠናው ከወልቂጤ፣ ከዋቻሞ፣ ከጅማ፣ ከቦንጋ እና ከወራቤ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ 30 የዩኒቨርሲቲ ሰላም ፎረምና የተማሪዎች መማክርት አመራሮችና አባላት ተሳትፈዋል። በተመሳሳይ ከአዲስ አበባ እና ከቢሾፍቱ ከተሞች ለተውጣጡ 33 የወጣት ማኅበራት አመራሮች እና አባላት ከታኅሣሥ 21 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. የአሰልጣኞች ስልጠና በቢሾፍቱ ከተማ ተሰጥቷል። ስልጠናዎቹ የሌሎች ሀገራት የሽግግር ፍትሕ ተሞክሮዎች የቀረቡበት ሲሆን የወጣቶችን ጉልህ ሚና ለማሳደግ የሚረዱ ተግባራዊ ልምምዶች የተካተቱበት ነው።

በተመሳሳይ ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ፅንሰ ሐሳብ እና የሽግግር ፍትሕ ምንነትን በተመለከተ በራሱ እና ከፕሮጀክት ኤክስፒዲየት ጀስቲስ (Project Expedite Justice) ጋር በመተባበር ከትግራይ ክልል 25፣ ከአማራ ክልል 26 እና ከሲዳማ ክልል 35 ለተውጣጡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ሠራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች ከታኅሣሥ 1 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዳማና በሃዋሳ ከተማ ስልጠና አካሂዷል። በስልጠናው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሽግግር ፍትሕ ዐውድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የመከታተል፣ ሰንዶ የመያዝ እና የመወትወት ክህሎትን እንዲያዳብሩ ዕድል ፈጥሯል።

በተጨማሪም ኢሰመኮ ለፖሊስ እና ለማረሚያ ቤት አባላት በተጠርጣሪዎች እና በታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ዙሪያ ስልጠና ሰጥቷል። ከጥቅምት 25 እስከ 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ለተወጣጡ 28 የፖሊስ አባላት በቢሾፍቱ ከተማ፣ ከኅዳር 16 እስከ 20 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ለተወጣጡ 34 የፖሊስ መካከለኛ አመራሮች በአሶሳ ከተማ እንዲሁም ከታኅሣሥ 14 እስከ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ከደቡብ ምዕራብ ክልል (ከቤንች ሸኮ እና ሸካ ዞኖች) ለተውጣጡ የፖሊስ አባላት እና የሥራ ኃላፊዎች ስልጠናዎችን ሰጥቷል፡፡ በስልጠናዎቹም ፖሊሶች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በሚያውሉበት፣ የወንጀል ምርመራ በሚያደርጉበት እንዲሁም የኃይልና የጦር መሣሪያ በሚጠቀሙ ጊዜ ተግባራዊ ሊያደርጓቸው የሚገቡ መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎች ላይ በጥልቀት ተወያይተዋል። በተመሳሳይ በአፋር ክልል ከሚገኙ 6 ማረሚያ ቤቶች የተውጣጡ 35 አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ከደቡብ ምዕራብ ክልል ማረሚያ ቤቶች የተውጣጡ 32 የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት ከኅዳር 9 እስከ 20 ቀን 2017 ዓ.ም. በሚሌ እና ቦንጋ ከተሞች የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ ዕውቀታቸውን፣ አመለካከታቸውን እና ክህሎታቸውን ለመገንባት የሚያግዝ ስልጠና ወስደዋል።

ኢሰመኮ ባለፉት 3 ወራት የአረጋውያን ሰብአዊ መብቶች እንዲሁም መብቶቹን ለማስከበርና ለማስፋፋት የሚያስችሉ ክህሎቶችን በተመለከተ ከኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ማኅበር፣ ከደቡብ ምዕራብ ክልል እና ከጅማ ከተማ አረጋውያን ማኅበራት ለተወጣጡ 61 አረጋውያን እና አመራሮች በተለያዩ ጊዜያት በአዳማ እና በጅማ ከተሞች ስልጠናዎችን ሰጥቷል። በስልጠናው አረጋውያን ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ለሚመለከተው አካል ሪፖርት እና አቤቱታ ለማቅረብ እንዲሁም ውትወታ ለማድረግ የሚያስችሏቸውን ክህሎቶች ለማዳበር እንዲችሉ ተግባራዊ ልምምድ አድርገዋል። በተመሳሳይ ኢሰመኮ የሴቶችን መብቶች በተመለከተ በአዳማ፣ በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ ከተሞች ከሚንቀሳቀሱ ኢ-መደበኛ ከሆኑ አደረጃጀቶች ለተወጣጡ 35 ተሳታፊዎች ከታኅሣሥ 7 እስከ 11 ቀን 2017 ዓ.ም. ለ5 ተከታታይ ቀናት በአዳማ ከተማ የአሰልጣኞች ስልጠናው ሰጥቷል። የዚህ ስልጠና ዋና ዓላማ ስለሴቶች መብቶች ዕውቀት ማስጨበጥ፣ አመለካከትን ማጎልበት እንዲሁም ተሳታፊዎች ያገኙትን ዕውቀትና አመለካከት ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ማስቻል ነው፡፡ በሌላ በኩል ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አገልግሎት ከሚሰጡ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ለተውጣጡ 30 የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ከኅዳር 23 እስከ 27 ቀን 2017 ዓ.ም. በአርባ ምንጭ ከተማ ስልጠና ተሰጥቷል። ስልጠናው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በቅድመ መፈናቀል፣ በመፈናቀል እና በድኅረ መፈናቀል ወቅት በዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፎች ላይ ስላሏቸው መብቶች፣ ከሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጋር በተያያዘ የመንግሥት ግዴታዎች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ኃላፊነትን በተመለከተ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ ነው። ተሳታፊዎች በስልጠናው ያገኙትን የሰብአዊ መብቶች ዕውቀት፣ አመለካከት እና ክህሎት በመጠቀም ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ ያላቸውን ተነሳሽነት ገልጸዋል፡፡ 

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር መቅደስ ታደለ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት እና ስልጠና መርኃ ግብር የመብቶች ባለቤቶችን እና ባለግዴታዎችን የሰብአዊ መብቶች ዕውቀት፣ ክህሎት እና አመለካከት በማጎልበት የሰብአዊ መብቶች ባህልን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል። አያይዘውም የስልጠና ተሳታፊዎች የቀሰሙትን የሰብአዊ መብቶች ዕውቀትና ክህሎት በሥራ በመተርጎምና ለሌሎች ባልደረቦቻቸው ምሳሌ በመሆን ሰብአዊ መብቶችን በማስፋፋት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ አሳስበዋል።